Wednesday, 13 January 2021 19:27

በእግሩ ድንጋይ ያሰረ ሰው ይሮጣል?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

የግብፅ ሕገ-መንግሥትና ድርድሩ
                             

            የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበትና ግንባታው መጀመሩን ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም በይፋ በገለጡበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የታደልን ሕዝብ ብንሆን ኖሮ ግድቡን ሶስቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በጋራ በሠራነው ነበር የሚል መንፈስ ያለውን ሀሳብ መግለጻቸውን አስታውሳለሁ።
የግድቡ ሥራ እንደተጀመረ የግብፅ የሕዝብ ለሕዝብ ልኡካን ገስግሰው አዲስ አበባ ገቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግድቡ በሁለቱ አገሮች ላይ የከፋ ጉዳት እንደማያደርስ በማስተማመን በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንደሚቻል በመግለጥ በር ከፈቱ።
የሶስቱ አገሮች ሙያተኞች የሚገኙበት ዓለም አቀፍ የሙያተኞች ቡድን ተቋቁሞ፣ ስለ ግድቡ የሚያስረዱ 150 ሰነዶች ቀርበው እንዲመረመሩና እንዲጠኑ ተደረገ። ሙያተኞቹ  ሰነዶቹን በግልፅ መርምረው ይጎድላል የሚሉትን ሀሳብ አቅርበው ከስምምነት ተደርሶ ስምምነቱም ተፈረመ። ግብፆች እነሱን ወክሎ ስምምነቱን የፈረመውን ሰው ወደ እስር ቤት መወርወራቸው ሳይጠቀስ አይታለፍም።
ኢትዮጵያ አንድ አይነት አስገዳጅ ስምምነት ሳትፈርም ግድቡን መሙላት የለባትም  የሚሉት ሁለቱ አገሮች፣ በተለይም ከሕዳሴው ግድብ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የሮዘሪ ግድብ አደጋ ላይ ይወድቃል ብላ የምትሰጋው ሱዳን፣ ቀደም ሲል በጠቀሰኩት ሰነድ አደጋ እንደማይገጥማት የተረጋገጠላት መሆኗና እሷም አምና መቀበሏ የሚዘነጋ አይደለም። የአሁኑ የሱዳን ጩኸት እየበረታ የመጣው ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት ወደ አደባባይ አውጥታ ለአለም ባለማሳወቋ ነው እንጂ  በቂ ምክንያት ኖሯት አይደለም፡፡
የውኃና መስኖ ኢነርጂ ሚኒስቴር በቅርብ በሰጠው መግለጫ፤ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለአስራ ዘጠኝ ጊዜ ለድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጡን ማስታወቁ ይታወሳል። ሃያኛው የድርድር ጊዜ የተደናቀፈው የአፍሪካ ኅብረት ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን  በመነሻ ሀሳብነት ሲቆሙለት ግብፅ ባለመቀበሏ መሆኑ ታውቋል። ተከታዩ ደግሞ ሱዳን ለመገኘት ባለመፍቀዷ ተቋርጧል። መቼ ሊቀጥል እንደሚችል እስከ አሁን የታወቀ ነገር የለም።
“ኢትዮጵያ የውኃ ክፍፍል ጥያቄ እያነሳች ነው” በሚል ምክንያት ቀደም ሲል ከድርድሩ ራሷን ማግለሏን አስታውቃ የነበረችው ሱዳን፤ ተመልሳ ከድርድሩ መራቋ ሊያስገርም አይችልም፡፡ ሱዳንና ግብፅ አንዱ ፊታውራሪ ሌላው ደጀን በመሆን ኢትዮጵያን በመውረርና ሰላም በመንሳት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም፣ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየጣሩ መሆኑም ነጋሪ የማያስፈልገው ደረቅ እውነት ነው። ለጊዜው የመረጡት መንገድ ይሄ ነው።
የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል.ሲሲ፣ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የተሠራው የግብፅ ሕገ መንግሥት ይሁነኝ ብሎ አንድ አንቀጽ በመመደብ፣ የግብፅ መንግሥት በአባይ ላይ ያላትን መብት እንደሚያስከብር ደንግጓል።
ግብፅ  በአባይ ውኃ ላይ  ያላት እነሱ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት ብለው የሚገልጡት እ.ኤ.አ በ1929 እንግሊዝ ሱዳንን ወክላ ከግብፅ ጋር፣ በ1959 ደግሞ ግብፅና ሱዳን የተዋዋሉትን ውል መሆኑ የታወቀ ነው። ይህ ሕግ በግብፅ ሕገ-መንግሥት እስካለና እስከተጠበቀ ድረስም ግብፅ አንድም አይነት ሃሳብ ትቀበላለች ወይም ትስማማለች ተብሎ አይጠበቅም። በእግሩ ላይ ድንጋይ ያሰረ ሰው ይሮጣል ወይ? ያልኩትም ለዚሁ ነው። ይህን ውል ደግሞ ኢትዮጵያ ትቀበላለች ተብሎ አይታሰብም።
ውሉን ፈፅሞ እንደማትቀበለው ኢትዮጵያ ደጋግማ የገለፀች ሲሆን በተግባርም አሳይታለች። ኢትዮጵያ የተከዜን ግድብ የገደበችውና ታላቁን የሕዳሴ ግድብን የጀመረችው፣ ከላይ የተጠቀሱት ስምምነቶች ለግብፅ የሰጧትን “የወሳኝነት” (Veto Power) ስልጣን ከመሬት እረግጣ  በማለፍ ነው።
ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ እየተደራደረች ያለችው ይህን መብት በመጣስ የእራሷን በውኃዋ የመጠቀም መብቷን በማስቀጠል ነው። የውኃና መስኖ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፤  ኢትዮጵያ ምንጊዜም ቢሆን ይህን መብቷን ለማንም አሳልፋ ለመስጠት እንደማትፈልግ አረጋግጠዋል።
ይህ ማለት ደግም የግብጽ ሕገ-መንግሥት፣ ለግብፅ መንግሥት የሰጠው ኃላፊነትና ግዴታ  አይሠራም  ማለት ነው። በሕዳሴው  ዙሪያ ኢትዮጵያና ግብፅ ከአንድ ስምምነት ይደርሱ ዘንድ አስቀድሞ የግብፅ ሕገ-መንግሥት መሻሻል ወይም መለወጥ አለበት ማለት ነው። ይህን የቤት ስራ ኢትዮጵያ ለግብጽ በአደባባይ ልትሰጣት ይገባል።
ኢትዮጵያ፣ የግብፅ ሕገ-መንግሥት በህዳሴው ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንቅፋት መሆኑን ማሳወቅ አለባት። እነሱ ኢትዮጵያ የሌለችበትን መቶ ዓመት ሊደፍን የተቃረበ ስምምነት እየጠቀሱ ጉዳዩን በዝርዝር የማያውቁትን ሰዎች ልብ ሲያሸፍቱ፣ ኢትዮጵያ ሃያ ዓመት እንኳን ያልደፈነውን የግብፅ ሕገ-መንግሥት ለማብጠልጠልና ለማጋለጥ መስነፍ የለባትም፡፡
እንደ እኔ፤ እንደ እኔ፤ ኢትዮጵያ የግብፅን ሕገ-መንግሥት አዲስ የመደራደሪያ ጥያቄ አድርጋ ከሁሉ በፊት ማንሳት፣ ለአለምም ማሳወቅ አለባት። ግብፅ በሕገ-መንግሥት ምክንያት ለእውነተኛ ድርድር አለመዘጋጀቷን መንገር ደግሞ ለነገ ሊባል አይገባውም።



Read 2231 times