Monday, 11 January 2021 00:00

የመንግስትን ትኩረት የሚሻው የሪል ስቴት ጉዳይ!

Written by  በየነ ሞገስ
Rate this item
(1 Vote)

መኖሪያ ቤት የሰው ልጅ ከሚያስፈልጉት መሰረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በዚያው መጠን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትም ይጨምራል፡፡ ትክክለኛው መረጃ ባይኖረኝም ባደረግሁት አጭር ዳሰሳ፤ ተቀጣሪ ሆነው የሚሰሩ ሰራተኞች ከሃምሳ ከመቶ በላይ  ገቢያቸውን ለቤት ኪራይ እንደሚያውሉ ይገመታል። በአከራይና በተከራይ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ጠንከር ያለ ህግ ስለሌለ፤ በሁለቱ ወገኖች ያለው ግንኙነትም ውጣ ውረድ የበዛበት ነው፡፡ አከራይ ተጨማሪ ገንዘብ የሚያገኝ ከመሰለው የዓመታት ተከራዩን ውጣ ከማለት አያመነታም፡፡ የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ይከበራል በተባለበትና ከውጭም ብዛት ያላቸው ዳያስፖራዎች ይመጣሉ ተብሎ በተገመተበት ጊዜ፤ በተከራዮች ላይ የደረሰውን ሰቆቃ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሰምተነዋል። በሌላም በኩል፤ ተከራዮችም የተከራዩትን ቤት በስነስርዓት ስለማይዙት ችግሩ ቀላል አይደለም፡፡ ይሄም ሲባል ሁሉም አከራይና ተከራይ እንደዚህ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
የማህበረሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍና በስራውም ለመጠቀም ሲሉ በቤት/አፓርትማ ልማት ወይም ግንባታ ላይ ‹ሪል ስቴት›  የተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ በቤት እጦት የተሰቃዩ ወገኖች ያላቸውን ጥሪት ሰብስበው ወይም ከባንክም ሆነ ከሌላ ምንጭ ተበድረው የቤት ባለቤት ለመሆን ከእነዚሁ ድርጅቶች ጋር ውል የሚፈራረሙት ይህንኑ ችግራቸውን ለማስወገድ መሆኑ እሙን ነው፡፡
በሪል ስቴት ወይም በአፓርትማ ግንባታ የተሰማሩ ድርጅቶች በሚያማልል ማስታወቂያና በፎቶ ሾፕ በተደገፉ ምስሎች፤ የቤት ኪራይ ያስመረራቸውን ቀልብ ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ከነዚሁ አካላት ጋር ውል የተዋዋሉ በውሉ መሰረት የመጀመሪያውን ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ተከታዩንም እያሉ በሚያደርጉት ውትወታ፣ ቤታቸው የሚደርስላቸው እየመሰላቸው ክፍያቸውን ይከፍላሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውንና ሊኖር የሚችለውን የእራሴን ገጠመኝ በማስከተል ትክክለኛ ሁኔታውን ልግለፅ፡፡ ለጊዜው የሪል ስቴቱን ስም አልጠቀሰውም
ሪል ስቴቱ በሚያሰራው ሕንጻ ላይ፣ 3ኛ ፎቅ የቤት ቁጥሩ - የሆነ አፓርትማ ለማስገንባት ከድርጅቱ ጋር ጥር 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ውል መሰረትን፡፡ አጠቃላይ ክፍያውንም ከከፈልን ቆይቻለሁ፡፡ በተፈራረምነው ውል ውስጥ ከተጠቀሱት አንቀጾች የሚከተሉት ይገኙበታል፤
አንቀጽ 3.6፡ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ መገጣጠሚያዎችና መብራቶች በድርጅቱ ስታንደርድና የግል ቆጣሪ ይገባል፣ እንዲሁም የዲሽ ገመድና የስልክ መስመር ይዘረጋል፡፡
3.14፡ ሊፍት፣ ጄነረተር፣ ፓምፕና ሬዘርቫየር አለው፡፡
በአንቀጽ 5 የቤቱን ርክክብ በተመለከተ ‹ሻጩ ቤቱን አጠናቅቆ ሠርቶ በመጨረስ ሐምሌና ነሐሴን ሳይጨምር በ24 ወራት ጊዜ ውስጥ ለገዢ ያስረክባል….
የሚሉ የሻጭ ግዴታዎች ተጠቅሰዋል። 12ኛ ዓመቱን ለመድፈን ቀናት የቀሩት ስምምነት እስካሁን ተሟልቶ ለመኖሪያ ሊሆን በሚችል ገጽታ ላይ አይገኝም፡፡ እኔማ ቤቱን ለማስረከብ የተጠቀሰውን የሃያ አራት ወራት ጊዜ ‹ምናልባት ሃያ አራት ዓመት ለማለት ይሆን› እያልኩ እንደገና ውሉን ለማንበብ ተገድጃለሁ፡፡ የግንባታው ሂደት ከወሰደው ረጅም ጊዜ አንጻር ፣ችግራችንም ያንኑ ያህል የተራዘመ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በአሁን ወቅት ዋናውና ትልቁ ችግር የመብራት አለመኖር ነው፡፡ ሊፍቱ በሚሰራበት ሁኔታ አልተገጠመም፡፡ አጠቃላይ ከሁኔታውን ስንገመግመው፤ ሊፍቱ እንኳን ‹ጽድቁ ቀርቶ ….› የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ነው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ቢያንስ በሳምንት አንዴ እንደማደርገው የግንባታው ኃላፊ ቢሮ ሄጄ ነበር፡፡ ቀደም ብላ ከኃላፊው ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የምትገኝ ወይዘሮ ያለባትን ችግር ትገልጽ ነበር፡፡ እቤቷ በጠለፋ የገባላት መብራት ከሚሰራበት የማይሰራበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ በትምህርት ላይ የምትገኘው ልጇ እቤት እንደደረሰች የመጀመሪያ ጥያቄዋ ‹መብራት አለ?› የሚል ነው፡፡ ይህም የልጇ ጥያቄ እናትን ያሰቅቃታል። የመብራቱን መኖር የምትፈልገው ወጣቷ ለጥናት ሲሆን፤ ከሌለም ያላት ምርጫ ዘመድ ጋ ሄዶ ማደር ነው፡፡
አሁንም ይህ ድርጅት የሚያሰራቸው አፓርትማዎች  ስላሉ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ ማስታወቂያ ያወጣል፡፡ ነገሩ ገረመኝና በማስታወቂያው ላይ በሚገኝ ስልክ ደውዬ ‹ከማስታወቂያ ይልቅ ተግባር ይናገራል፤ ስለዚህ የጀመራችሁትን ሳታጠናቅቁ ማስታወቂያ መናገሩ ምን ትርጉም ይኖረዋል?› የሚል አስተያየት ሰነዘርኩላቸው፡፡ ይቀበሉት አይቀበሉት ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን የመሰለ ተግባር ላይ የተሰማሩ፣ “የአክሰስ መንፈስ” የተጠናወታቸው ሪል ስቴቶች እንዳሉ በቅርብ ከማውቃቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡
ይህን ጽሁፍ እንዳቀርብ ያስገደደኝ መሰረታዊ ምክንያት፤ ‹ብልህ ከሌላው ስህተት ይማራል› እንዲሉ፣ ወገኖቼ ከእኔ ገጠመኝ ትምህርት በመውሰድ፤ በጅምር ያለ ወይም ያላለቀ አፓርትማ ወይም ቤት ከመግዛታችሁ በፊት ነገሮችን በጽሞና እንድታስቡበት ተሞክሮዬን ለማጋራት ነው፡፡ መንግሥትም ይህን በመሰለው ግዢና ሽያጭ ላይ በተሰማሩ ወገኖች ላይ የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም ሊያስከብር የሚችል ጠንከር ያለ ህግና መመሪያ እንዲያወጣ ለማሳሰብና ለማንቃት  ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ፀሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

Read 2063 times