Thursday, 14 January 2021 11:42

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ቁም ነገሮችን ጊዜያቸው ካለፈ በኋላ ወደ ቀልድነት እየቀየርን እንዝናናባቸዋለን። ትናንት ግን የልብ ትርታዎቻችን መለኪያዎች ነበሩ።
በ1997 ዓ.ም በተደረገው ህዝባዊ ምርጫ ሰሞን የሆነ ነው።… የሰፈራችን ሰው ስብሰባ ተጠራና ግልብጥ ብሎ ወጣ። ያኔ ለተሰብሳቢዎች አበል አይከፍልም። ስብሰባ መሄድና አለመሄድ የባለቤቱ ፍላጎትና  ጉዳይ ነበር።
ስብሰባው እንደ ተጀመረ የመድረኩ መሪ አጀንዳውን አስተዋውቆ የመግቢያ ንግግር አደረገ። በወቅቱ ሁኔታ ላይም አስተያየትና ጥያቄ ማቅረብ እንደሚቻል አስታወቀ። ለጥያቄ እጅ ያወጣ ሰው ግን አልነበረም።
“ጥያቄ የላችሁም?” ሲል በድጋሚ ጠየቀ።
ማንም ምንም አላለም… ፀጥ።
በሁኔታው የተጨነቀው ሰብሳቢም …….
“በጊዜ ጨርሰን ብንሄድ አይሻልም?” በማለት ልመና መሳይ ጥያቄ ለሶስተኛ ጊዜ አቀረበ።
“ይሻላል”
“ታዲያ በቀረበው አጀንዳ ላይ ጥያቄ ወይ አስተያየት--”
… አንድ ሰው እጁን አውጥቶ…
“ጥያቄ አለኝ”
“እሽ ቀጥል” ተባለ።
“የመጀመሪያው አጀንዳ “የቅንጅት መሪዎች ይፈቱልን” በሚል መተካት አለበት; የሚል ጥያቄ አቀረበ።...     አዳራሹ በሃይለኛ ጭብጨባም ተቀወጠ።
“ሌላ ጥያቄ?”
ዝም።
 “የሁላችሁም ጥያቄ ይሄ ብቻ ነው?”
  “አዎን”… አለ… ተሰብሳቢው አንድ ላይ።
የመድረክ መሪው አጠገቡ ከተቀመጡት ጓዶቹ ጋር ተመካከረና…
“ከጥቂት ደቂቃዎች ዕረፍት በኋላ እንቀጥላለን” ብሎ ስብሰባውን አቋረጠ።
ከእረፍት መልስ ተሰብሳቢው ቦታውን እንደያዘ አወያዩ…
“ሌላ ጥያቄ የላችሁም?” ለማለት አፉን ከመክፈቱ ሁሉም ሰው እጁን አወጣ።
… ምን ተፈጠረ?... እንመለስበታለን።
*   *   *
ወዳጄ፡- ታላቁ ኢማኑኤል ካንት በባለ ትላልቅ ጥራዝ መጻሕፍቶቹም ሆነ በመጣጥፎቹ ካሰፈራቸው ታላላቅ ቁም ነገሮች  ውስጥ ምክንያታዊ የአስተሳሰብ ኩነቶችና አተገባበራቸው፣ ሞራልና ስነ-ምግባር፣ እግዜርና ሃይማኖት፣ ፖለቲካና ሰላም ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል። ሌሎቹን የሃሳብ ዘርፎች ወደ ጎን ትተን፣ ስለ ዕውቀትና ነፃነት ከሌሎች በተለየ የአቀራረብ ስልት ሃሳቡን የገለጸበትን አንድ ሁለት ምሳሌዎች ለዛሬ ባጭሩ እንመልከት፡፡ በነገራችን ላይ ከሱ በኋላ ለመጡት፤ ሃሳባውያን ሊቃውንት (German ideologists) ለሚባሉት እንደ ሾፐን ሀወርና ሄግል ዓይነት ሰዎች  ለስነ ሀሳብ ወይም አይዶሎጂ አፈጣጠር መነሻነት ምክንያት የሆነ ፈላስፋ እንደሆነ አያሌ ፀሀፍት መስክረውለታል፡፡ የሰውየውን መጽሀፍቶች በአንድ ወጥ ንባብ ለመረዳት እንደሚያስቸግርም ተፅፏል፡፡ ለምሳሌ ዕውቀት፤ የተፈጥሮ ችሮታና የአእምሮ ስትራክቸር እንጂ በስሜት ህዋሳቶቻችን በኩል እንደዋዛ የምናደራጀው ፋኩሊቲ እንዳልሆነ ያብራራበትን ክሪቲክ ኦቭ ፒዩር ሪዝን (critique of pure reason) የተባለ መፅሐፉን ኸርዝ የተባለው ጓደኛው እንዲያነበው አውሶት የጠበቀውን ውጤት (feedback) ባለማግኘቱ  መበሳጨቱም ይነገራል። ወዳጁ ኸርዝ የመፅሐፉን ግማሽ ካነበበ በኋላ…..” ከጨረስኩት የማብድ ይመስለኛል” በማለት ነበር የመለሰለት፡፡
ወዳጄ፡- በካንት አስተሳሰብ የሌለንን ነገር “ልከኛ” አደርጎ ማቅረብ ዓይን ያወጣ ኢ-ፍትሀዊነት ነው፡፡ “አለ” የሚባል ነገር በርግጥ “ካለ” ደግሞ መኖሩ ብቻ ውበት ነው፡፡ (existence by itself is a Perfection, a being can exist without being just) ይለናል… ፈላስፋው። ለምሳሌ ቀለም ቀቢ አንድ ግድግዳ ከማስዋቡ በፊት ግድግዳው ቀለም ሲቀባ ምን እንደሚመስል አስቀድሞ ያውቀዋል፡፡ ሰውየው ሀሳቡን ቀይሮ ግድግዳው  ቀለም ባይቀባ አስቀድሞ የነበረው የሰውየው ዕውቀት “ምንም” ነበር ማለት አይደለም፡፡ ግድግዳው ከተቀባ ግን ዕውቀቱ ወደ ምርትነት ተቀይሯል፡፡ ወይም የተቀባ ግድግዳ “አለ” ማለት እንጂ “ያልተቀባ” ግድግዳ አልነበረም ማለት አይደለም በማለት…… የድርጊት ነፃነት ከነፃ ሀሳብ ለመመንጨቱ ማረጋገጫው፣ ከፍላጎት  አስገዳጅነት መላቀቁ እንደሆነም አበክሮ ይሞግታል፡፡
ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲጋራ ለማቆም ወስነሃል እንበል ይለናል፡-ታዲያ አብሮህ ያልነበረ ጓደኛህ ሲያገኝህ መዘዝ አድርጎ ይጋብዝሀል። የሀሳብህ ወይም የድርጊትህ ትክክለኛነት የሚመዘነው ሲጋራውን ተቀብለህ ካጨስክ ወይም አልፈልግም ብለህ ከተውክ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዛሬ የተውከውን ነገ ልትቀበል ወይም ዛሬ የተቀበልከውን ነገ እምቢ ልትል ትችላለህ፡፡ የሁለተኛ ዕድል አጋጣሚ አለመኖሩ እንጂ ራስን ማጥፋትን ጨምሮ ማንኛውም ውሳኔ ቋሚ አይደለም። ነፃነት የእውቀት እንጂ የፍላጎት እስረኛ ለመሆኑ ማረጋገጫ አልተገኘም ባይ ነው። በሱ እምነት እርግጠኛነት ያለው ሂሳብ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
ወዳጃችን ካንት የተወለደው እ.ኤ.አ. በ1724 ዓ.ም በቀድሞ ፕሩሽያ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ኬንስበርግ በምትባል ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ስራውም በዚያችው ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርስቲ በግል ማስተማር ነበር፡፡
አንድ ፀሀፊ እንዳለው፤ የሰውየው የኑሮ ዘይቤ እንደ መደበኛ ግስ (Regular verb) ውሉን የማያዛንፍ ሂደት ነበረው፡፡ ከመኝታው ይነሳል፣ ቡና ይጠጣል፣ይፅፋል፣ ያስተምራል፡፡
ከምግብ በኋላ ከዘራውን ይዞ በሊንደን ትሪስ ጎዳና ይንሸራሸራል፡፡ ለንደን ትሪስ (Linden trees) እስከ ዛሬ ድረስ የፈላስፋው መንገድ በመባል ይታወቃል። ካንት አላገባም። ሰማንያ ዓመታትን በብቸኝነት አሳልፏል።
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ከዕረፍት መልስ የመድረኩ መሪ ለተሰብሳቢዎቹ…
“ጥያቄ ካለ አሁንም እንቀበላለን” ከማለቱ ቅድም አሻፈረኝ ያለው ተሰብሳቢ በሙሉ እጁን እንዳወጣ ተነጋግረን ነበር ያቆምነው። ከዛ ሲቀጥል፡- ግራ የተጋባው አወያይ ዕድሉን ለአንድ ሰው ሰጠ። ሰውዬው ግን ከእረፍት በኋላ ባለው ጊዜ የመጀመሪያም የመጨረሻም ተናጋሪ ሆነ። ምክንያቱም ሁሉም ተሰብሳቢ ሊጠይቅ እጁን ያወጣበትን ጥያቄ ነበር የጠየቀው፡…
“ከእረፍት በፊት ጥያቄ ያቀረበው ሰው የት ሄደ?”… የሚል።
ሠላም!

Read 1744 times