Thursday, 14 January 2021 11:47

አድማስ ትውስታ ቦቅቧቃው Coward of the County

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 (የኬኒ ሮጀርስ የዘፈን ግጥም እንደ አጭር ልብወለድ)


              ሰው ሁሉ “ቦቅቧቃው” ይለዋል። እሱ ግን አንድም ቀን እንኳ አንገቱን ቀና አድርጎ አይደለሁም ብሎ ለማስተባበል ሞክሮ አያውቅም። እናቱ ያወጣችለት ስም ቶሚ ነው። የመንደሩ ሰው ግን “ቦቅቧቃው” በሚል የቅፅል ስም ይጠራዋል። እኔ መቼም የሰፈሩ  ሰው ለቶሚ የሰጠው ግምት ትክክል አለመሆኑ ይታወቀኛል።
አባቱ እስር ቤት ውስጥ ሲሞት እሱ ገና የአስር ዓመት ልጅ ነበር። የወንድሜ ልጅ ነውና ከዚያ ወዲህ በአደራ ቶሚን የማሳድገው እኔ ነኝ። ወንድሜ በአልጋ ጣር ላይ ሳለ፣ ለቶሚ የነገረው ነገር አሁንም ትዝ ይለኛል።
“ልጄ ሆይ፤ የእኔ ኑሮ እነሆ አበቃ፣ የአንተ ግን ገና መጀመሩ ነው። ስለዚህ ቃል ግባልኝ። መከራን መሸሽ ከቻልክ ሽሸው። ማምለጥ እየቻልክ ቆመህ አትጠብቀው፣ አንደኛውን ጉንጭህን ሲመቱህ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም። በዚህ ዕድሜህ መቼም ይህንን መረዳት አያቅትህም። አየህ ልጄ፤ ሰው ለመሆን የግድ  መታገል፣ የግድ  መጋፈጥ የለብህም፡፡"
ሁሉም ሰው የምትሆነውን ሴት ማፍቀሩ ያለ ነገር ነው። ቶሚም ቤኪን በጣም ያፈቅራታል። በእቅፏ ውስጥ በገባ ጊዜም ወንድ መሆኑን ማረጋገጥ አላስፈለገውም፡፡
አንድ ቀን የጋትሊን መንደር ልጆች ሶስት ሆነው እየተፈራረቁ ቤኪን ይሰድቧታል። ይባስም ብለው ይደበድቧታል - ጠግበዋል።
ቶሚ በሥራ ገበታው ላይ ነበር። ድንገት ድምጽ ሰምቶ ብቅ ብሎ ቢያስተውል የሱዋ ቤኪ ናት። ተደብድባለች፣ ታለቅሳለች። የተቀዳደደ ቀሚሷና የተመሰቃቀለ ሁኔታዋ ሩህሩህ ልቡ ከሚችለው በላይ አሰቃቂ ሆነበት።
ወደ ቤት ተመልሶ ገባ። ድንገት ዞሮ ከእሳቱ ማንደጃ ቦታ ላይ የነበረውን ያባቱን ፎቶግራፍ አየ። አነሳው። እያለቀሰም ተመለከተው። በእንባው ፊቱ እስኪታጠብ ድረስ ሲያስተውለው ከቆየ በኋላ በመጨረሻዋ እስትንፋሱ የመከረው ምክር ዳግም ጆሮው ላይ ደወለበት።
“…አንደኛውን ጉንጭህን ቢመቱህ እንኳ ሌላኛውን ጉንጭህን ብትሰጥ ደካማ ነህ ማለት አይደለም… አየህ ልጄ ሰው ለመሆን የግድ መታገል የለብህም።"
ቶሚ ቆጣ ብሎ ወደ ቡና ቤቱ መጣ። የጋትሊን ልጆችም በማንጓጠጥ ሳቁበት። ከመሃላቸውም አንዱ ተነሳና ወለሉን ማህል ለማህል አቋርጦ ወደሱ መጣ። ቶሚ ከዚያ ቦታ ዘወር እንደ ማለት ቃጥቶት ነበር።
“እዩት ይሄን ቦቅቧቃ ፈርቶ ሲሸሽ ተመልከቱ እንግዲህ…” ለከፋቸውንና ስድባቸውን ቀጠሉ። አላገጡበት።
ይሄኔ ቶሚ ትዕግስቱ ተሟጦ አለቀ። ደረቱን በሀሞተ- ሙሉነት ነፍቶ፣  በሩን በግዙፍ  ሰውነቱ ሞልቶ ቆመ። ማን ወንድ ይለፈው! ይሄኔ አካባቢው ሁሉ ፀጥ እርጭ አለ። ከዝምታው ጥልቀት የተነሳ እስፒል እንኳ ብትወድቅ ትሰማ ነበር። ሃያ ዓመት ሙሉ በችግር እየማቀቀ፣ እየዳኸ ያሳለፈው ሕይወቱ፣ በቡሽ እንደተከደነ ጠርሙስ ልቡ ውስጥ በጥንቃቄ ታሽጓል።
ድንገት ያ የልቡ ማሸጊያ ቡሽ ከመቅፅበት ተፈናጥሮ ተከፈተ። እልሁና ቁጣው እንደ ሻምፓኝ ገነፈለ። መቼ ገባ ሳይባል ተወንጭፎ ጠብ ውስጥ ጥልቅ አለ። ያለ የሌለ ጉልበቱን ሳይቆጥብ ይሰነዝርባቸው ጀመር። እያንዳንዳቸውን በቡጢ ማንጋጭል- ማንጋጭሊያቸውን እያለ እየቦቀሰ ዘረራቸው። አንድም የጋትሊን ልጅ ፊቱ ቆሞ አይታይም። ሁሏም ተራ በተራ ምሷን ቀመሰች።
የመጨረሻውን ልጅ መትቶ ሲጥል፣
“ይሄኛው ለቤኪዬ ማስታወሻ ይሁን; አለና ቡና ቤቱን በኩራት ለቅቆ ወጣ።
ወዲያው እንዲህ ሲል ሰማሁት፣
“አባባ አንተ ያጠፋኸውን ዓይነት ጥፋት እንዳልደግም ቃል አስገብተኸኝ ነበር። እነሆ መከራን የቻልኩትን ያህል ሸሸሁ። ከእንግዲህ እኔን ደካማ ነው ብለህ እንዳታስብ። ቀኜን ሲመቱኝም በፍፁም ግራዬን አልሰጠሁም። እንግዲህ አባባ፣ ሰው ሆኖ አንዳንድ ጊዜ መታገልና መጋፈጥ እንደሚያስፈልግ አሁን እንደገባህ በፅኑ ተስፋ አደርጋለሁ።”

Read 1802 times