Thursday, 14 January 2021 11:54

የተቃዋሚ ፓርቲ ብዛት፣ ለብልፅግና ፓርቲ፣ ሲሳይ ነው ወይስ አበሳ ወይስ ሲሳይ?

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

“ተቃዋሚ ፓርቲ” እንደ አሸን ሲፈለፈል፣ ለገዢው ፓርቲ ከባድ ፈተና እንደሚጋርጥበት ባያከራክርም፤ ምቹ መንገድም ይሆንለታል።
በአብዛኛው ግን፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ብዛት፣ ለገዢው ፓርቲ የመከራ ብዛት ነው። እየተፈራረቁና እየተረባረቡ፣ የጎን ውጋት ይሆኑበታል። አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ ተዳክሞ ድምፁ ሲጠፋ፣ ወይም አደብ ሲገዛ፣ ሌሎች በእጥፍ እየተባዙ፣ እጥፍ እየጮሁ ይመጡበታል። መፋጠጥና መላተም ይበረክታል። ገዢው ፓርቲ፣ ከአንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ሲነታረክ፣ ሌላኛውን ተቃዋሚ ፓርቲ ሲያሳድድ፣…. በጉዳይ ብዛት ይጨናነቃል።
በእርግጥ፣ ንትርክ የማያሳስባቸው፣ መቆራቆስ የማያስጨንቃቸው መኖራቸው አያጠራጥርም። መፋጠጥና መናቆር የሚመቻቸው ፖለቲከኞች፣ በሁሉም ፓርቲዎች ውስጥ አሉ። እንዲያውም ያጋግሉታል - ቁምነገር የሰሩ ይመስል። ግን ምን ዋጋ አለው?
ለሁሉም ፓርቲ ኪሳራ ነው - በተለይ ደግሞ ለገዢው ፓርቲ። ለምን? አሃ፣ ገዢው ፓርቲ፣ የመንግስት ስራ አለበታ! ውዝግብና ንትርክ እንደስራ እየተቆጠረ፣ አንድ ሁለት ነውጠኛ ተቃዋሚዎችን ልክ ማስገባትም፣ ትልቅ ትርፍ የሚያስገኝ ስኬት እየመሰለ፣ ገዢውን ፓርቲ ያዘናጋዋል። ትኩረቱ ይበታተናል።
እናም፣ በየቦታው፣ እዚህና እዚያ የተለኮሱ እሳቶችን ለማጥፋት ሲዋከብ፣ ገዢው ፓርቲ፣ ቁም ነገር መስራት ያቅተዋል። መቅኖ ቢስ ይሆናል። እንኳን ለቁምነገር ይቅርና፣ ለአንዲት ትንፋሽም የእፎይታ ጊዜ ያጣል።
ምናለፋችሁ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ እርባታ፣ ለገዢ ፓርቲ አበሳ ነው። ሰላም ይርቀዋል። ሰላም ሲጠፋ ደግሞ፣ የአገርና የዜጎች መከራ ይከብዳል።  
ግን ደግሞ፣ የፓርቲ እርባታ፣ ለገዢው ፓርቲ፣ ሲሳይ የሚሆንለት ጊዜ አለ። ምርጫ ላይ፣ ገዢውን ፓርቲ ሊጠቅም ይችላል። ከአንድ ተቀናቃኝ ፓርቲ ጋር ወይም ከሁለት ብርቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መወዳደርና ማሸነፍ፣ ለገዢ ፓርቲ ከባድ ትግል ነው። ተቃዋሚዎች ሲበዙና ሲባዙስ? ያኔ፣ ተቃዋሚዎች እርስ በእርስ ሲራኮቱ፣ ገዢው ፓርቲ በአነስተኛ የድጋፍ ደምጽ ብቻ፣ አሸናፊ የመሆን እድል ያገኛል።
በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች፣ የገዢው ፓርቲ የምርጫ ፈተና የሚቃለልለት፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዛት አማካኝነት ነው። 5 ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በየፊናቸው 15% የመራጭ ድምጽ ቢያገኙ፣ ገዢው ፓርቲ በ25% ድምፅ ብቻ ማሸነፍ ይችላል።
በእርግጥ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለበዙ፣ “በሁሉም ቦታ ብዙ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ይኖራሉ” ማለት አይደለም። በየጥጉ በየመንደሩ ተበታትነው፣ በየፊናቸው የመንደር ገናና የሚሆኑ አሉ። አንድ ሸለቆ ውስጥ አንድ ፓርቲ፣ አንድ አምባ ላይ ሌላ ፓርቲ ይነግሳል።  ይሄ፣ ለገዢው ፓርቲ፣ አበሳ እንጂ፣  ሲሳይ አይደለም። በዚህ ስሌት፣ መቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በየሸለቆውና በየአምባው፣ በየፊናቸው አንድ አንድ ቦታ ላይ አነጣጥረው፣ አንድ አንድ ጥግ ይዘው ለማሸነፍ መሞከር ይችላሉ። ያው፣ የፖለቲካ ቅርጫ፣ “የቅንጥብጣቢ ፖለቲካ” ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ተመቻችተናል። በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ተሸንፈናልኮ።
አገራችን፣ እዚህና እዚያ በሚበታትን ስንጥቅጥቅ ፖለቲካ ተጥለቅልቃ የለ? በጭፍን እየደገፉ ወይም እየተቃወሙ፣ በቲፎዞ ስሜት የመጮኽና በዘር የመቧደን በሽታዎች፣ ከዳር እስከ ዳር ተዛምተው መላ አገሪቱን መርዘዋል። ታዲያ፣ 80 ብሄር ብሄረሰብ ተብሎ፣ በየቦታው 80 ፓርቲ ቢግተለተል ይደንቃል? በዘር ተቧድኖ፣ በየመንደሩ ደርዘን ለመግነን፣ በየሰፈሩ ፓርቲ ቢፈለፈል ምን ይገርማል? ግን በዚህ እንደማያበቃ አይተነዋል። ፈተናው ለገዢው ፓርቲ ብቻ አይደለም። ለሁሉም ፓርቲዎች ነው መከራው።
በዘር ለማቧደን፣ “የኦሮሞ ፓርቲ፣ የአማራ ደርጅት፣ የትግራይ ፓርቲ፣ የሶማሌ ድርጅት”…. እያለ የተቋቋመ ፓርቲ፣ አንዱን ጥግ ለብቻው ይዞ፣ ለብቻው መግነን የሚችል ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን፣ ለእያንዳንዱ የመንደር ፓርቲ፣ በየመንደሩና በየጥጉ፣ የሰፈር ተቀናቃኞች ይመጡበታል። ምን ይሄ ብቻ?
የጎሳና የዞን፣ የአውራጃና የወረዳ ዘረኝነትንም በማጣቀስ፣ ከአንዱ አምባ አጠገብ አነስ ያለ አምባ ቀንሰው ለመውሰድ፣ ከአንዱ መንደር ውስጥም ትንሽ ሰፈር ቆርሰው ለመካፈል የሚመኙ ፓርቲዎች፣ እንደጉድ ሲፈለፈሉ አይተናል። በዘረኝነትና በጭፍን እምነት በሽታ ሳቢያ የሚፈጠር መዘዝ፣ በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ የሚመጣ ጣጣ፣ ማብቂያ የለውም። የፓርቲ እርባታውም አይቋረጥም።

ከመቶ በታች ፓርቲ? ስንት ስንት ሊያደርሰን? አይበቃም
ከመቶ ምናምን ፓርቲ ውስጥ፣ ዛሬ ሀያው ቢፈርሱ ወይም ቢሰረዙ፣ የፓርቲ ቁጥር ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። ከሃያ በላይ አዲስ ፓርቲዎች እንደመጡና ሌሎችም በፍጥነት እየተፈለፈሉ እንደሆነ በዚያው ቀን ትሰማላችሁ። አስገራሚ ነው። “አይዟችሁ! የፓርቲ ቁጥር አይቀንስም” የሚል መፅናኛ ሰምተን፣ “እፎይ” ስንል ይታያችሁ። “የፓርቲ ቁጥር ቀነሰ? እድገታችን አሽቆለቀለ? የፓርቲዎች ቁጥር ከመቶ በታች ከወረደ ምን ሊውጠን ነው?” በሚል ጭንቀት እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር ሰው ካለ፣ ቅንጣት ታክል ማሰብ የለበትም። ቅንጣት ታክል እያሰበ አይደለም ቢባል ይሻላል እንጂ።  ደርዘን ፓርቲዎች ሲጠፉ፣ የአገራችን የፓርቲዎች ቁጥር ግን፣ እያደገ እየተመነደገ ይሄዳል። “ተዓምር ነው” ያስብላል። የፓርቲ እርባታ፣ የአገር ስኬት ቢሆን ኖሮ፤ በመቶኛ እየተሰላ፣ በ`double digit` አድገናል፣ “ሬከርድ” ሰብረናል እያልን እንዘምርለት እንጨፍርለት ነበር። ፌሽታችን ይሆን ነበር።
 ክፋቱ ግን፣ የፓርቲ ብዛት፣ የአገር ስኬት አይሆን፤ ም የውድቀት ቁልቁት ነው። ለምን? በአንድ በኩል ውድቀት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ባሰ ውድቀት ያወዳል። ውድቀትም ቁልቁለትም ነው። በአሳዛኝ ውድቀት ላይ፣ አደገኛ ቁልቁለት ሲጨመርበት አስቡት።
አደገኛነቱ ብዙ አይነት ነው።
 ስንጥቅጥቅ ፖለቲካ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በድጋሚ እየተሰነጠቀ፣ ለሁለት እየተከፈለው፣ ለአራት እየተቆረሰ፣ በሌላ ዙር ወደ ስምንት ቅንጥብጣቢ እየተበጣጠሰ አገርን የሚያፍረከርክ የህልውና አደጋ ይሆናል። ይህም ብቻ አይደለም።
በየቦታው በደርዘን በደርዘን የተፈለፈሉና አምባውን ለመቆጣጠር፤ በዘር የተቧደኑ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ ምን ይስሩ? መፎካከሪያቸው ምን እንደሆነ አስቡት። ጥላቻን በማጦዝ እንዲጨበጨብላቸው ሽሚያ ይገጥማሉ። ዘረኝነትን በማግለብለብም ከተቀናቃኛቸው ለመብለጥ ይተናነቃሉ።  አገሬውን የማንደድ እሽቅድድም ይሆናል- የፓርቲዎች ፉክክር።
ይህም ብቻ አይደለም።
 በፓርቲ ብዛትና በፖለቲከኞች ጩኸት የተጨናነቀ አገር ውስጥ፣ ብዙ አድማጭና ተመልካች በቀላሉ አይገኝም። ከፓርቲዎች ትርምስ መሀል፣ ጎልቶ መታየትና ሰሚ ማግኘት ከባድ ነው። በዚህም ምክንያት፣ ጉድ የሚያሰኝ ነገር ለመፍጠር የሚሽቀዳደሙ ይበረከታሉ ከእስከዛሬው የከፋ አንዳች ነገር የመናገር ወይም ከእስከ ዛሬው የባሰ ነገር የማድረግ ፉክክር ይፈጠራል። አንዱ ፖለቲከኛ  ስድብና ውንጀላ በማዝጎድጎድ፣ ታዋቂነትን ለማግኘት ይሞክራል። ሌላ ፖለቲከኛ  ደግሞ፣ ከዚህ የባሰና የበለጠ ለመሆን ይሟሟታል። ከስድብና ከውንጀላ ወደ ዛቻና ዘመቻ በመሸጋገር ዙሩን ያከረዋል።Read 3656 times