Print this page
Saturday, 16 January 2021 10:37

በወጡበት የቀሩት የህወኃት መሥራቾች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 በ1967 ትግራይን ከጭቆና ነጻ አወጣለሁ ብሎ በደደቢት በረሃ የተመሰረተው ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) በመመስረት 11 ግለሰቦች በቀዳሚነት ስማቸው ይነሳል፡፡
ከ11ዱ ደግሞ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው ቀደም ሲል በ1967 ደርግ ስልጣን እንደያዘ በሦስተኛ ቀኑ ማለትም መስከረም 4 ቀን 1967 ዓ.ም “ማህበረ ገስገስቲ ብሔር ትግራይ (ማገብት)”ን የመሰረቱት ኋላም ህወሃትን እንደ መሰረቱ የሚነገርላቸው አለምሰገድ መንገሻ፣ አምሃ ፀሃዬ (አባይ) አረጋዊ በርሔ (በሪሁ)፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም)፣ ፋንታሁን ዘርአፅዩን (ግደይ)፣ ሙሉጌታ ሃጎስ (አሰፋ) እና ዘሩ ገሰሰ (አጋዚ) ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ከእነዚሁ ተጠቃሽ የህወኃት አስኳሎች አንዳንዶቹ ተፈጥሯዊ ሞትን ሲሞቱ፣ ጥቂቶች ከህወሃት በተቃራኒ የፖለቲካ መስመር ውስጥ ዛሬም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ማለትም አባይ ፀሃዬና ስዩም መስፍን ደግሞ ከ46 ዓመት በፊት ወደ ነበሩበት የአማፂነት ዘመናቸው ተመልሰው “ታሪክ” ለመስራት በረሃ ገብተው ሳይቀናቸው ቀርተዋል፤ ታሪክ ሆነዋል፡፡
አባይ ፀሃዬ ማናቸው?
በአክሱም ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በአክሱም የተማሩ ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመቀሌ ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባለበት በ1970ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴን ተቀላቀሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የትግራይ ተወላጅ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበርን ከመሰረቱት አንዱ ናቸው - አባይ ፀሀይ፡፡
በኋላም ከጥቂት ጓዶቻቸው ጋር ወደ በረሀ በመውረድ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይን (ህወኃት) የመሰረቱት አባይ ፀሀዬ፤ በ1967 ዓ.ም ወደ አስመራ በማቅናት ከኤርትራ ህዝብ ነፃነት ግንባር ለትግራይ ታጣቂዎች የሚሰጥን ወታደራዊ ስልጠና ወስደዋል፡፡ በወቅቱ ሥልጠናውን ከአባይ  ፀሀዬ ጋር ከወሰዱ የህወኃት አባላት መካከል መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ይገኙበታል።
በህወሃት ትግል ወስጥ እያሉም በ1977 አወዛጋቢውን የማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማህሌት) በመመስረትም ድርሻቸው የጎላ ነው፡፡
በ1983 ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ ስልጣን ሲቆጣጠር፣ አባይ ፀሀዬ የመጀመሪያው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር በመሆን የተሾሙ ሲሆን የበለጠ ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሰው ግን በሙስና ከሚታሙበት የስኳር ኮርፖሬሽን ዳይሬክተርነታቸው ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ከስኳር ፋብሪካዎች ምስረታ ጋር በተያያዘ ከ70 ሚሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ መባከኑ ይታወቃል፡፡
ከአዲስ አበባ ፊንፊኔ ዙሪያ ማስተር ፕላን ተቋውሞ ጋር ተያይዞ  “ልክ እናስገባቸዋለን” በሚል ዛቻ አዘል ንግግራቸው ጥርስ እንደተነከሰባቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ፣ መቀሌ ከመሸጉ ከህወኃት ባለስልጣናት ጋር መቀሌ መሽገው ቆይተዋል። ከህወኃት መስራቾች አንዱ የሆኑት አባይ ፀሀዬ፤ ድርጅታቸው በከፈተው ጦርነት ተሸንፎ እሳቸውም ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተወሰደ እርምጃ ተገድለዋል፡፡
አቶ ስዩም መስፍን ማን ናቸው?
እ.ኤ.አ በ1949 ጥር ወር በአዲግራት ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትግራይና በአዲስ አበባ ተከታተሉ፡፡ ወደ ባህርዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲቲዩት በመግባት ስልጠና የወሰዱት አቶ ስዩም፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲንም ተቀላቀሉ፤ ነገር ግን ትምህርታቸውን ሳያገባድዱ ለትግል ወደ በርሃ ወርደዋል፡፡
ህወኃትን በ1967 ከመሰረቱት አንጋፋ መሪዎች አንዱ የሆኑት ስዩም መስፍን፤ ማሌሊትን በመመስረት ረገድ ከትግል ጓዳቸው አባይ ፀሀይ ጋር ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
በህወሃት የትጥቅ ትግል ዘመን በዋናነት በስለላ ተግባር ላይ  ተሰማርተው እንደነበር የሚነገርላቸው ስዩም፤ ደርግ ወድቆ በ1983 ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ፣ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ለ20 ዓመታትም በዚሁ ስልጣናቸው ዘልቀዋል፡፡
ስዩም መስፍን በተለይም “ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነች” በሚለውና የአልጀርሱን የስምምነት ውሳኔ አዛብቶ ለኢትዮጵያውያን ከማቅረብ ጋር  ስማቸው ተደጋግሞ ሲነሳ የቆየ ሲሆን በኋለኛው የስልጣን ዘመናቸውም በቻይና የኢትዮጵያ አምባሰደር ሆነው ተሾመዋል።
የኢጋድ ሊቀ መንበር በነበሩበት ወቅት የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የአሸማጋይነት ሚና የነበራቸው አቶ ስዩም የደቡብ ሱዳንን ችግር አወሳስበዋል በሚል በደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ይነቀፋሉ።
አቶ ስዩም መስፍን የሶስት ወንዶችና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ሲሆኑ መንግስት በትግራይ በወሰደው የህግ የማስከበር እርምጃ ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም ተገድለዋል።


Read 12608 times