Saturday, 16 January 2021 11:07

ከ”ፖለቲካ በቃኝ” ወደ “ፖለቲካ ናፈቀኝ”

Written by  ጤርጢዮስ ዘ - ቫቲካን
Rate this item
(2 votes)

በእነዚህ ሰሞናት የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ለሚዲያ ፍጆታ በዋሉበት ርዕሰ ጉዳይ በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ ሆነዋል። “ፖለቲካ በቃኝ” ብለው የነበሩት ሰው ዳግመኛ በፖለቲከኝነት ናፍቆት እየተፈተኑ መኾኑንም አሳብቆባቸዋል። ፈተናው ከሰው ደካማ ፍጡርነት አንጻር ብዙ ባያስደንቅም የተከተሉት የፖለቲካ መስመር ግና ያንኑ በሴረኝነትና  ከፋፋይነት የታጀለውን የቀድሞ ዘመን ፖለቲካ መኾኑ በእጅጉ ያሳዝናል።
ከሁለት አሠርት ዓመታት በፊት አቶ ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸውና አሥራ ስምንት ዓመት ተፈርዶባቸው ዘብጥያ መውረዳቸው የሚታወስ ሲኾን፤ አሥራ ሁለት ዓመታትን በእሥር ቤት አሳልፈው በአመክሮ ከተለቀቁም አሥራ ሁለት ዓመት ገደማ ይሆናቸዋል። ታምራት በነዚህ ሁሉ ዓመታት ድምጻቸው ሳይሰማ ቆይቶ በለውጡ ወራት ወደ ሀገር ቤት መለስ ቀለስ እያሉ ከባቢውን መሰለል ከጀመሩ በኋላ ይመስለኛል የ“ፖለቲከኝነት” ናፍቆቱ  የመጣባቸው።
የእኚህን ሰው የሕይወት ጉዞ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፣  በወንጌል  ቃል  አምነው ወደ ሃይማኖቱ ጎራ ከመቀላቀላቸው በፊት ኮሚኒስት እና “ኢ-አማኒ” እንደነበሩ በገዛ  አንደበታቸው ሲመሰክሩ ሰምተናቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስን “ጌታዬና አምላኬ” ብለው የተቀበሉት ከወህኒ ቤት ለህክምና በተላኩበት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ሲኾን፣ “የለም” ሲሉት የነበረው አምላክ ህላዌውን የገለጠላቸው በህክምና ትረዳቸው በነበረች ነርስ ጋባዥነት፣ ከአንዲት ትንሽዬ ትራክት ላይ ባነበቡት ቃል አማካኝነት ነው። በቃሉ ውስጥ የተለየ መለኮታዊ አብርሆት ስላገኙም በጉልበታቸው ተንበርክከው ሽንፈታቸውን ለመግለጽ  አላንገራገሩም ነበር። ከእሥር  ከተፈቱ በኋላ ዋና ጉዳዬ ብለው የያዙትም ስለዚሁ ድንቅ ተዓምር  መመስከርን ነበር።
በነዚያ ሰሞናት በእንግድነት በተጋበዙባቸው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መድረኮች ላይ በቆሙበት ጊዜ ሁሉ ትናንትና ዛሬያቸውን እያነጻጸሩ በእንባ የታጀበ ምስክርነት ሲሰጡ የሰማ ሰው ደግሞ እግዚአብሔር እንዲያ አይነቱን ሰው የራሱ ገንዘብ ባደረገበት አሠራር መገረም አይቀርለትም። በእርግጥም ደግሞ  የእግዚአብሔር እውቀትና ጥበብ ድንቅ፣ ፍርድና ምህረቱም የማይመረመር ነውና ለእርሳቸውና በስደት ይኖር ለነበረ ቤተሰባቸው ያደረገውን ተመሳሳይ ተዓምር ሰምቶ አለመደነቅ አይቻልም። እኔም የአቶ ታምራት ላይኔን ምስክርነት ሰምተው እጃቸውን በአፋቸው ላይ ከጫኑ ተገራሚዎች መካከል አንዱ ነበርኩ።
የዛሬን አያድርገውና በወቅቱ አንድ የሚዲያ ተቋም ስለ ቀጣዩ  የፖለቲካ ሕይወታቸው በጠየቃቸው ጊዜ፣ አቶ ታምራት ላይኔ  የሰጡት ቆፍጠን ያለ ምላሽ “ፖለቲካ በቃኝ” የሚል እንደነበርም አስታውሳለሁ። እኔም ራሴ የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ከእርሳቸው ጋር ቃለ ምልልስ የማድረግ ዕድል አግኝቼ ስለነበር፣ የአቶ ታምራት ላይኔ ይኸው አቋም መለወጡን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ፍንጭ አላየሁም። ይልቁንም ሐዋርያው ጳውሎስ፦” በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” እንዳለው፤ ልባቸው የሰማዩ መዝገባቸው ባለበት እንደኾነና በምድርም ወደ ወንጌል አገልግሎት ያዘነበለ ሕይወት እንዳላቸው ነበር የተገነዘብኩት።
አንድ ሰዓት ከ55 ደቂቃ በፈጀው ቃለ ምልልሳችን አቶ ታምራት ላይኔ በፖለቲካው ደጃፍ ያለፉ እስከማይመስለኝ ድረስ ለመንፈሳዊው ጉዳይ የሚሰጡት ቦታ ትልቅ የነበረ ሲኾን በተደጋጋሚ ትናንትናቸውን የኪሳራ መንገድ አድርገው በቁጭት ስሜት ሲገልጹም አዳምጫለሁ። በወቅቱ ከዚህ ቁጭታቸው ጋር የሚዛመድ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አስታውሻቸውም ነበር።  “እስራኤል ሆይ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ አለኝ። እኔ ግን፤ በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጕልበቴን ፈጀሁ፤ ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው፥ አልሁ (ኢሳ.49፥3-4)” የሚለውን  ማለቴ ነው።
የአቶ ታምራት ላይኔ ሰሞነኛው አከሳሰት ግና ቀደም ባሉት ጊዜያት አድሮባቸው የነበረውን  ቁጭት የዘነጋ ይመስላል። “ፖለቲካ በቃኝ” ማለት ብቻ ሳይኾን ያንን ዘመን የኪሳራ አድርገው የቆጠሩት ሰው ለዳግም ክስረት ወደዚያው መንደርደራቸውንም ገፍተውበታል። የክስረቱ መገለጫ ግና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማድረግ መሻታቸው ዓይደለም፤ የመረጡት የፖለቲካ መስመር ለሀገር አንድነት የማይበጅ ከፋፋይ  በመኾኑ እንጂ።  አቶ ታምራት ላይኔ ዳግመኛ ወደ ፖለቲካው ዓለም ብቅ ሲሉ  አንደበታቸውን ያሟሹት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን አመራር በማንኳሰስና የመንግሥታቸውን ተግባራት በማጣጣል  መኾኑም  የበርካቶች መነጋገሪያ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።  
በግሌ አቶ ታምራት ላይኔ “ፖለቲካ በቃኝ” ስላሉ ብቻ አሁን ላይ ሀገራቸው ያለችበትን ሁኔታ እያዩና እየሰሙ አርፈው ይቀመጡ አልልም።  በዘረኝነት ፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ላለች ሀገር  የመፍትሔ አካል የሚኾኑበት በርካታ አማራጮች ስላሉም አንዳች ተሳትፎ  ቢኖራቸው  ደስታውን አልችለውም ነበር። ይሁንና ቀደም ባሉት ጊዜያትም ኾነ ሰሞኑን “አባይ” በተሰኘ ሚዲያ ላይ  ያዳመጥኩት  ቃለ ምልልሳቸው ተቃራኒውን እንዳስብ ነው ያደረገኝ።  አቶ ታምራት እንደ ሰላም ወንጌል አገልጋይነታቸው የተጣላን የማስታረቅ ሚና ሊወስዱ ሲጠበቅባቸው ጭራሽ የጠቡ አባባሽ ኾነው መከሰታቸውም ግርታን ፈጥሮብኛል።
ሁላችንም ብንኾን ዕለት ተዕለት በምንሰማውና በምናየው የወገኖቻችን  ሞትና  መፈናቀል  ልባችን  በሚደማበት  ሁኔታ ውስጥ መኖራችን የዓደባባይ ምስጢር ነው።  ዛሬም ድረስ ፈልገው ባላመጡት ማንነትን እየታደኑ በግፍ የሚገደሉ፤ በግሬደር  ታፍሰው በጅምላ  የሚቀበሩ  ንጹሐን ዜጎች  አሉና መንግሥት  ተጠቂዎችን ለመታደግ ቁርጠኛ እርምጃ እንዲወስድ  የፍትሕ ያለ ብሎ መጮህ ፣  በሰላማዊ መንገድ  ተጽዕኖ ማሳደር ተገቢነት ያለው ተግባር ነው።
አቶ ታምራት ላይኔ ግና ጉዳዩን  በሀገራችን ሥር እየሰደደ ከመጣው  የብሔር  ፖለቲካ  ቀውስ  አንጻር  ተመልክተው  መገምገም፣ መቃወም፣   ማሄስ  ሲገባቸው፤ ለአንድ ሃይማኖትና ብሔር ተቆርቋሪ መስለው የቀረቡበት መንገድም ኾነ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአንድ  ብሔር  ልዕልና  እየሠሩ እንዳለ  አድርገው ማቅረባቸው  ሕዝብን  ከሕዝብ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት  የሚለይ  በመኾኑ ያስደነግጣል። መሬቱ ላይ የሚታዩ የባለጊዜነት ስሜቶች ቢኖሩም  በማስተዋል መንፈስ ተበልጠው የሚሰክኑበትን መላ መሻት እንጂ እሳቱ ላይ ቤንዚን እንደ ማርከፍከፍ ያለን  አቀራረብ  እንደ አቶ ታምራት ላይኔ ካለ መንፈሳዊ  ሰው  አልጠበቅሁም ነበር።
አቶ ታምራት ከእሥራ ከተፈቱ በኋላ “ከአጠገባቸው ገለል ሊያደርጉኝ ሲሹ ነው ሴራ ጎንጉነው ዘብጥያ የወረወሩኝ” ላሏቸው “የባልንጀራ ጠላቶቻቸው” ከሰጡት  ይቅርታ የተነሳ “ቂምና ጥላቻዬ ብን ብሎ ጠፍቷል”  ሲሉን የነበሩት ሰውዬ፤  በእነርሱ ላይ ቂም መቋጠር የተሳነው ልባቸው እንደምን ቅርብ ጊዜ ባወቁት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ላይ አንዳች ቂም የቋጠሩ መስለው ሊከሰቱ ቻሉ የሚል ጥያቄም አጭሮብኛል።  የሚባለው እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልኾንም፣ ሰውዬው በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ላይ ያላቸውን ቅዋሜ አጠንክረው የመግፋታቸው ዋና ሰበብ፣ ከእርሳቸው ሽተውት የነበረውን የአማካሪነት ቦታ በመነፈጋቸው የመጣ እንደኾነ ሲነገር ደጋግሜ ሰምቻለሁ።
የአባይ ሚዲያው ጋዜጠኛ፣ አቶ ታምራት ላይኔ፣ በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለአንዳች የሥልጣን ቦታ ታጭተው እንደኾነ በግልጽና በስም ጠቅሰው እንዲነግሩት ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት የተድበሰበሰ ምላሽና “አካፋውን አካፋ የምልበት አንድ ቀን ይመጣል” በሚል መግለጻቸውም  ወደዚሁ ጥርጣሬ ይገፋል። እንደ አሁኑ አያያዛቸው  አቶ ታምራት ሽተውት የተነፈጉት ቦታ አማካሪነት ከነበረም እንኳንም ተነፈጉ ያሰኛል። ጠልፎ መጣልና ሸፍጥ በማያጣው የቀድሞ ዘመን የትግል ጓዶቻቸው ስልት፣ በአሁን ሰዓት ብናገረው ብዙ ሰሚና ደጋፊ ያስገኝልኛል ብለው የመዘዙት የዘረኝነት ካርታም ቢኾን ዒላማው ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን የማጥቃት ይመስላል።
አቶ ታምራት ላይኔ  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የታያቸው ግድፈት  የአመራር  ቢኾንማ፤ በ2002 ዓ.ም ከእሥር ከተፈቱ በኋላ ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን በታላቅ ጭካኔና ከፋፋይ ፖለቲካ ሲገዙ የነበሩት የቀድሞ ባልንጀሮቻቸውን የመቃወም ሰፊ ዕድል ነበራቸው።  በዚህ  ሰዓት የከፊሎቹን ሞት፤ የከፊሎቹን በሕግ ቁጥጥር ሥር የመዋል ዜና እየሰማን ያለነው የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው  በሥልጣን መንበራቸው ላይ  ተሰይመው ባሉበት  ወቅት አንድም ቀን የተቃውሞ ድምፅ አሰምተው አያውቁም። አብረው የቀመሩት የዘውጌ ብሔረተኝነት ጦስ በሀገሪቱ ውስጥ የፈጠረውን ምስቅልቅል ቢያውቁም፣ ስለዚያ ትንፍሽ ሲሉም አልሰማናቸውም።
ይልቁንም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው የአገዛዝ  ዘመን ባበቃበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በገደምዳሜም ቢኾን ለእነርሱ ያሳዩት ውግንና የሚመስል ስሜት ያስተዛዝባል።  “ጦርነቱን የጀመረው ማነው?” የሚለው ጥያቄ በራሳቸው በጦርነት ጀማሪዎቹ አንደበት ተገልጾ ሳለ፣ አቶ ታምራት ላይኔ ጉዳዩ በገለልተኛ አካል እንዲጣራላቸው ያላቸውን ፍላጎት የማንጸባረቃቸው ዓላማ ምን እንደኾነም አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው።
ሰውዬው በቅርቡ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፣ መንግሥት የወሰደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም እንደገቡበት ጦርነት አድርገው ነው የሚናገሩት። ከሁሉም፣ ከሁሉም ግን በሰሞነኛው የ”አባይ ሚዲያ” ቃለ ምልልሳቸው ፤”ለውጡ መክሸፉን ያስተዋልኩት ከጅማሬው አንድና ሁለት ወር በኋላ ነው” ማለታቸው ሁኔታውን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል።
ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ስለ ሕዝቧ የተደመረ አብሮነት መዘመር በተጀመበት ወራት ለአቶ ታምራት ላይኔ የለውጡ ክሽፈት የታያቸው መኾኑ ከምን አይነት ዕይታ የመነጨ እንደኾነ ለመገመት ቢከብድም፤ ብዙ ደጋፊ እንጂ ብዙ ማሰብ የማይጠይቀውን አክቲቪዝም መቀላቀላቸውን ግን  ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ዐቢይ ጠል ከኾኑቱ አክቲቪስቶች በርካቶቹም ተመሳሳይ ባህርይ ያላቸው ሲኾኑ የሚበዙቱም ከለውጡ በኋላ በድል አጥቢያ አርበኛ የተከሰቱ በመኾናቸው የትዝብታችን ማረፊያዎች ናቸው።
ነገሩ በእርግጥም ጭፍን ጥላቻ ቢኾን ነው እንጂ አቶ ታምራት ላይኔ “ለውጡ መክሸፉን ተረዳሁ” ባሉባቸው ሁለት ወራቶች ውስጥ “ይህችስ የእግዚአብሔር ጣት ናት!” የሚያሰኙና እንደ መለኮታዊ ተዓምር የሚቆጠሩ በርካታ ኩነቶች ተስተውለዋል። ይህንንም ሃይማኖተኞቹ ብቻ ሳይኾኑ ፖለቲከኞቹም በአደባባይ ሲመሠክሩ ተደምጠዋል። አቶ ታምራትም ቢኾኑ “በሆድ ይፍጀው”  የተውትን የተበዳይነት ዶሴ ከደበቁበት አውጥተው በየሚዲያው መተንፈስ የቻሉት ይኸው ለውጥ ባመጣላቸው እድል ተጠቅመው ነው።
እነዚያ የለውጥ ጅማሮ ቀናት፣ ሳምንታትና ወራት (የአቶ ታምራት ላይኔ የቀድሞ የትግል ጓዶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን  ቢሮና መኖሪያ  ተቆጣጥረው፣ አስገቢና አስወጪ በኾኑበት ጊዜ እንኳ)  ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ  በስጋትና በጭንቀት ውስጥ ለነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ልብን በተስፋ የሚሞሉ ዘለግና በርከት ያሉ አነቃቂ ንግግሮች ያደረጉበት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ይሆናሉ ተብለው የማይገመቱ የፖለቲካ እርምጃዎችን የወሰዱበት፤ በርካታ ልብን የሚነኩ ድርጊቶችን ያከናወኑበትና  ከፍተኛ  የሕዝብ ድጋፍ ያገኙባቸው ናቸው። አቶ ታምራት ላይኔ “የለውጡን መክሸፍ ተረዳሁ” ያሉበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መቶ ቀናት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ስለመኾኑም ብዙዎቹ ሚዲያዎች ጽፈውትና ዘግበውት ተመልክተናል።  
አንድዬ ከፈተናው ጋር መውጫውን ቀዳዳም እያበጀልን እስካሁንም ሀገራችን ባልተጠናቀቀ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዳለች እናውቃለን። ብዙ እሾህና አሜኬላ በበዛበት  በዚህ ሂደት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጣልቃ ገብነት ያየንባቸው አጋጣሚዎችም ብዙ ናቸው ። “እግዜርን ፖለቲካችን ውስጥ ምን ዶለው?” የሚሉ ወገኖች ለእርሱ ውለታ ዕውቅና ላለመስጠት ሆነ ብለው ዓይናቸውን ቢጨፍኑም፣ ዛሬም ድረስ ለማመን የሚያስቸግሩ የታዳጊነት ሥራውን እያየንና እየሰማን ነው።
“ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተጨቁነው የሚኖሩበት እሥር ቤት ናት” ይሉ የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና ባልንጀሮቻቸው፣ በወቅቱ “አለ” ያሉትን የብሔር ጭቆና ማስወገድ የሚቻለው የብሔር ትግል በማድረግ እንደኾነ አምነው ነበር፣ ነፍጥ አንግበው ወደ ትግል የገቡት። ይኹንና ያኔ መስሏቸው የጀመሩት ትግል ዛሬ ላይ በተግባር ተፈትኖ መውደቁን የሚያመላክቱ በርካታ ምልክቶችን እያየን ነው። “የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት” የተሰኘው ፍካሬ የወለደው የብሔር ፌደራሊዝም  አወቃቀር፣  በሀገር አንድነትና በዜጎች አብሮነት ላይ የጋረጠው ከባድና ውስብስብ አደጋም ቀላል ዓይደለም።
የብሔር ፖለቲካ ከአጀማመሩ አንስቶ ችግር ያለበት መኾኑ  ቢታወቅም፣ የሠላሳ ዓመቱ የቤተ ሙከራ ውጤትም የፖለቲካውን አስከፊ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት የሺዎችን በግፍ መታረድ፣ የሚሊዮኖችን ከኖሩበት ቀዬ መፈናቀል አስከትሏል። ዛሬም ድረስ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው የትኛውም ክልል በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይኖሩ፣ ሀብት ንብረት እንዳያፈሩ እንቅፋት ፈጥሯል። ሁሉም ሀገሬ ነው ብለው ቀድመው መኖር የጀመሩትም ሕይወታቸው ለአደጋ፣ ያፈሩቱ ሀብትና ንብረትም ለውድመትና ለቃጠሎ ተዳርጓል። እንዲህ ዓይነቱ ፖለቲካ ለጎጥ ማንነት እንጂ ለጠቅላላው የሰው ልጅ ክብር የሌለው  በመኾኑ  በእርግጥም በተግባር ተፈትኖ ወድቋል።
እናም አቶ ታምራት ላይኔና የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸው፣ እንዲህ ባለ አስቀያሚ የጎጥ ፖለቲካ፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ የከፋፈሏትን ሀገር ዳግመኛ ወደ አንድነቷ ለመመለስ እየደከሙ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለማብጠልጠል ምንም ዓይነት የሞራል ብቃት እንደሌላቸው መናገር የሚገባ ይመስለኛል። “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የቅንነት ፖለቲካን የዐቢይ አህመድን ያህል የደፈረ ሰው አልነበረም” በሚለው የአንድ ጸሐፊ  አባባልም እስማማለሁ።

Read 4648 times