Sunday, 17 January 2021 00:00

የአፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየም በአንኮበር

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

    የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአፄ ምኒልክ ቤተ-መንግስት ሆኖ ሲያገለግል የቆየው የአንኮበር ቤተ-መንግስት፤ ከሰሜን ሸዋ ዞን ዋና መቀመጫ ደብረ ብርሃን ከተማ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። አካባቢው ብዙ ታሪክና ቅርስን የያዘ ነው። የፈረንሳይና ሌሎች አገሮች የመጀመሪያዎቹ ኤምባሲዎች የተከፈቱት በዚሁ በአንኮበር ቤተ-መንግስት አቅራቢያ ነበር።
የግብር አከፋፈል፣ ስልክና ሌሎችም ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ስራ የጀመሩት በአንኮበር ቤተ-መንግስት በአፄ ምኒልክ የሸዋ ንጉስነት ዘመን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል። ይህ ብዙ ሊነገርለት የሚገባው አካባቢ በመሰረተ ልማት ደረጃ በእጅጉ ወደ ኋላ ቀርቶ ቆይቷል።
የሰሜን ሸዋና የአካባቢውን ባህል፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ የግብርና መሳሪያና ሌሎች መገለጫዎቹን በአንድ አደራጅቶ የሚያሳይበት ሙዚየምም አልነበረውም። ይሁን እንጂ ግንባታውና አደረጃጀቱ ከ3 ዓመታት በላይ የፈጀው “የአፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሙዚየም” ባለፈው እሁድ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ተመርቆ ስራ ጀምሯል። ሙዚየሙ ከአንኮበር ቤተ-መንግስት ማዶ ላይ በሚገኝ ሌላ ተራራ ላይ የተገነባ ሲሆን ከጀርባው ከንጉስ ሳህለ ስላሴ ጀምሮ የነበሩትን ማሪያም፣ መድኃኒያለምና ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስያናት ተገን አድርጎ፣ ፊት ለፊቱን ወዳለው ሌላው አንኮበር አካባቢ ሜዳ አዙሮና ቀኝ ጎኑን ለአንኮበር ቤተ-መንግስት ሰጥቶ ነው የተገነባው።
የዚህ ሙዚየም ኪነ-ህንፃ ዲዛይን የቀድሞውን የአዲሰ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዲዛይን መንፈስ የተላበሰ ሲሆን የአርክቴክቸራል ዲዛይኑን የሰሩት በኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃ ታሪክ ደማቅ አሻራ ያሳረፉትና እያሳረፉ ያሉት እውቁ አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ እንደሆኑ በሰሜን ሸዋ ዞን፣  ባህልና ቱሪዝም መምሪያ፣ የቅርስ ኮንሰርቬተር አቶ ሚኪያስ ቴዎድሮስ ይናገራሉ። አርክቴክቱ ዲዛይኑን ተጠበውና ተጨንቀው፣ ለሰሜን ሸዋ ታሪክና ባህል የሚመጥን አድርገው፣ ያለ ምንም ክፍያ መስራታቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ወልደፃዲቅ፣ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት መኳንንቴ፣ የአንኮበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ፈቅይበሉን ጨምሮ የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተወከሉና ሌሎችም በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ግንባታው በአንኮበር ወረዳ መንግስት ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነውና ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት የተነገረለት ይኸው ሙዚየም፤ በተከፈተ ዕለት በአዳራሹ  ለእይታ ከበቁት መካከል በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ እና በጀርመን የባህል ማዕከል (ገተ) ትብብር ከፈረንሳይ አገር ተሰብስበው በውድ ዋጋ የመጡ የፎቶግራፍና የስዕል ስብሰቦች ይገኙበታል። እነዚህ ስዕሎችና ፎቶግራፎች በተለይም የ19ኛውን ክፍለ ዘመን አለባበስ፣ የነገስታቱን አኗኗር፣ የአፄ ምኒልክ ፖርትሬት ፎቶዎችንና የዘመኑን ድባብ አጉልተው የሚያሳዩ እንደሆነም ተገልጿል።
በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ሙዚየም ለጊዜው እነዚህን ስዕሎች፣ ፎቶግራፎችና ያልተለበሰ ካባ ለእይታ ያቅርብ እንጂ ወደፊት በሙዚየሙ በርካታ የሰሜን ሸዋን ባህል፣ አለባበስ፣ የመመገቢያና የግብርና መሳሪያዎች፣ ህዝቡ ሰርግና ሀዘንን የሚገልፅባቸው መንገዶችና በርካታ ቁሳቁሶች ወደ ሙዚየሙ ገብተውና ተደራጅተው ለጉብኝት ክፍት እንደሚሆኑ ነው አቶ ሚኪያስ ቴዎድሮስ የገለጹት። ወደ ሙዚየሙ ይገባሉ ከተባሉት ውስጥ ብዙ የነገስታትና የንግስታት ዘውዶች፣ የብራና መፅሐፍት፣ መስቀሎችና አንባሮች፣ የግብርና መሳሪያዎች፣ በየዘመኑ  ነገስታት የፃፏቸውና የተቀበሏቸው ደብዳቤዎች፣ ውሎችና ባህላዊ አልባሳት ይገኙበታል፡፡
በአሁን ወቅት ለሰሜን ሸዋ ህዝብ ስለ ሙዚየሙና ስለ ቅርስ ጥበቃ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወኑን ተከትሎ፣ ከአያት ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሷቸውንና በክብር ያስቀመጧቸውን ቅርሶች ለሙዚየሙ ለማበርከት ህዝቡ ቃል እየገባ ሲሆን ከነዚህ መካከል አንድ የአካባቢው አርሶ አደር፣ ከአያቶቻቸው ከወረሷቸው 3 የጥንት ጐራዴዎች መካከል አንዱን ለልጃቸው አስቀርተው፣ ሁለቱን ለሙዚየሙ እንደሚያስረክቡ ቃል መግባታቸውን አቶ ሚኪያስ ጠቅሰዋል፡፡
ከደብረ ብርሃን አንኮበር ድረስ የሚወስደው መንገድ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለጎብኚዎች ቅርብና ምቹ ስለሚሆን አካባቢው ከሙዚየሙና ከአንኮበር ቤተ-መንግስት ጎብኚዎች ገቢ ያገኛል ተብሏል።
ሙዚየሙ በሚደራጅበት ጊዜ ሰዓሊያን፣ አኒሜተሮች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ አንትሮፖሎጂስቶች፣ የፌደራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ሰዎች፣ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ውስጥ የሚሰሩ የቅርስ ኮንሰርቬተሮችና በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን የሙዚየሙን የግንባታ ስራ በማማከርም በኩል የዞኑ ባህል ቱሪዝም መምሪያ ባለሙያዎች ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተገልጿል።

Read 1480 times