Saturday, 16 January 2021 11:56

በዘንድሮ ጥምቀት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

  ኮልፌ ሞቅ ያለች ገበያ ብትሆንም ጥምቀት ደግሞ ይብስባታል፡፡ እንደ ሰው ሁሉ አይኖችዋን ቦግ አድርጋ ፈገግታ እየረጨች የምታስተናግድ ነው የሚመስለው። ……መንገዶችዋ ጠብበው፣ ገበያው ደርቶ፣ ለአንድ መስመር ብቻ የተወቻቸው ጎዳናዎቿ፤ ለጥምቀት ጭራሽ መፈናፈኛ ያጣሉ፡፡ ወትሮ ልከኛ ሰው የሚይዙት ካፌዎች፣ ቡና ቤቶች፣ ጁስ ቤቶች ሳይቀሩ ጢም ብለው ይሞላሉ፡፡
እኔና ጓደኛዬ እንደ ወትሮው ፉል ሳይሆን የባህል ቤት ገብተን፣ ስፔሻል ዱለታችንን ከጎረስን በኋላ ከሰፈር ሸሸን፡፡ “የራሳችንን ሰፈር ታቦት ማውጣት አለብን!” ብሎ ጥቂት የሞገተኝ ወዳጄ፤ ብዙ አልተከራከረኝም። “ሁሉም የራሳችን ነው!” ብዬ ባንዴ አፉን አዘጋሁት፡፡
ከዚያ ወደ ጦር ሀይሎች ሔደን….እነዚያን ሸጋ ሸጋ ቢራ ቤቶች ጎበኘን፡፡ እኔ ግን “ዐውደ ዓመቱን በአልኮል መጠጥ ባናከብረው ምናለበት!?” በሚል ትንሽ ጥያቄ አቀረብኩና  መልሼ ወደ ጠርሙሴ ገባሁ፡፡
ወዳጄ ሳሙኤል የሰሞኑን ነገር ይዞ “ይህን በዐል ለየት የሚያደርገው”….  ብሎ ሲጀምር፤
“በል እረፍ በዓላችንን ፖለቲካ አታድርገው” ብዬ አፉን አልኩት፡፡
“ማለቴ ፖለቲካ ሳይሆን… ሴኪዩሪቲ ነው….” አለኝ፡፡
“እኛ አማኞች እንጂ ተንታኝ አይደለንም፤ ቀኑ የክርስቶስ ጥምቀት ማስታወሻ እንጂ …ጁንታ  ምናምን የሚባልበት አይደለም!”
“ቢሆንም……”
“እግዜርን ፖለቲካ ማስነካት….ለምን እንደምንወድ…..”ብዬ በስጨት ስልበት፤
“እሺ በቃ ተወው!” አለና ቢራውን ጭልጥ አደረገ፡፡
“ሰውዬ… ቀስ በል!”
“ዱለት የበላኸው ለዚህ አይደል!….በበላ አንጀትህ ገና ጂን፣ ውስኪ….” ብሎ መላጣውን መዳበስ ሲጀምር፣መቁረጡን አመንኩ፡፡ ሊጠጣ ነው ማለት ነው፡፡ ከጠጣ ደግሞ አያቆምም፡፡ ካላቆመ ደግሞ ወሬው ፖለቲካ ይሆናል ወይም የሀገር መዝሙር!
“እንዲያውም ዛሬ ሙሉ በሙሉ ጋባዥ እኔ ነኝ፤ ….ይሄ ጥምቀት ለእኛ ልዩ ነው፡፡ በሰላም… በነፃነት…. በድል!”
“ሰውዬ እረፍ! ከጋበዝከኝ ዝም ብለህ ጋብዘኝ!”
አስተናጋጇን ጠቀሳት፤ አጭሩን - ሚኒ ወደ ታች ሳብ እያደረገች መጣች፤ ቀይ ትልልቅ ዓይኖች ያሏት ውብ ናት፡፡ ውበቷ ግን ….
“ሀበሻ ድገሚኝ…ቀዝቃዛ!”
“እሺ!” ፈገግ ብላ
“አንቺም አንድ ጠጪ የደስ ደስ!”
“ህ?”
“የደስ ደስ!”
ግር እንዳላት “እኔ ቢራ አልጠጣም!....”
“እንደ ዝክር ጠላ ቁጠሪው….የሀገራችን ፌሽታ ነው!”
“ልክ ነው ጁንታው ተመታ!” አለ- አንድ ጥግ ላይ ሞቅ ብሎት፣ ዓይኖቹ የድልህ አሎሎ የመሰሉ ጠጪ፡፡
“አመሰግናለሁ!”
ሳሙኤል ወደ እኔ መለስ ብሎ ሊያዋራኝ ሲሞክር፣ እኔ ስለ መፃሀፍት አወራሁለት፡፡
“ተዋቸው… የኛን ሀገር መፃህፍት!”
“የኛ ሀገር አላልኩህም!”
“የቱም አያስፈልግም፣ እዚህ ሀገር መፃህፍት ማንበብ፤ የመስቀል ደመራ ሆነህ መንደድ ነው….ለሌሎች ሆያ ሆዬ አንተ ትነዳለህ….. እየሞቁህ ይስቃሉ፤ ይልቅ ዛሬ ልዩ ጥምቀት ስለሆነ ጠጣ!"
ቀኑን  በሞቅታ ሊያሳልፍ እንደፈለገ ስለገባኝ ተሰናብቼው ወደ ሌላ ጓደኛዬ ጋ ሔጄ ዋልኩ፡፡ በልክ ተጫወትን፤ በዓሉን አስመስለን ዋልን፡፡ በኋላ  ራይድ ጠርቶ፣ ፒያሳ አቢሲኒያ ተያይዘን ሄድን፡፡
ወደ ጓዳ ገብተን፤እየተጫወትን ከመሸ በኋላ ልክ አስራ ሁለት ሰዓት ሲል ወጣን። ትንሽ በእግራችን መጓዝ ፈልገን ስለነበር በሀብተ ጊዮርጊስ በኩል አድርገን ወደ አውቶቡስ ተራ ስንሄድ፣ አንዲት ልጅ ከኋላ ጠራችን፡፡ ሁለታችንም ዘወር አልን፤የገጠር ልጅ እንደሆነች አለባበሷና ንግግሯ ያስታውቃል፡፡
“ተፈራ ሕንፃ የት ነው?” ስትለን ወደ ኋላ ዞረን ልናያት ስንል፣ ከጎዳናው ዳርና ዳር ያሉ ወጣቶች ዐይናቸውን አፍጥጠው ይጠብቋታል፡፡ በሩቅ አሳይተናት ለመመለስ አልፈለግንም፡፡
“አድርሰናት እንምጣ!” አልኩት፡፡
 ደግነቱ ወዲያው ስልክ ተደወለላት፡፡
“ሰዎች ጠይቄ እየመጣሁ ነው” አለችና ስልኳ ተቋረጠ፡፡
“አይዞሽ እናደርስሻለን…”
“አስቸገርኳችሁ!”
“ሌላ ጊዜ ብቻሽን እዚህ አካባቢ አትምጪ! ...እነዚህ ድኩላ ያየ ነብር ይመስል ያፈጠጡት ሁሉ አንቺን የከጀሉ ናቸው…..፡፡”
“አይ መኪናው አሳልፎ ጥሎኝ ነው….”
“ቢሆንም በዓመት በዓል ቀን… ያውም በጥምቀት ከባድ ነው!”
“እውነት ነው!”
አብሮኝ የነበረው ጓደኛዬ እንደ መታከት ቢልም፣ ጨክነን ልናደርሳት ግድ እንደሆነ በቀስታ ነገርኩት፡፡
“ሰዎች ሌላ ነገር ያስባሉ!” አለኝ
“እኛ የምናስበውን እናውቃለን፤ ተዋቸው….. ልጅቷን ብቻ እናድን!” አልኩት
መንገዱ በከፊል ጭር ብሏል፤ የመጠጥ ቤቶች ዘፈንና ድምፅ ግን አካባቢውን ሁሉ ውጦታል፡፡
በጨዋታና አንዳንዴም ልጅቷን በመምከር መንገዱ ተገፋልን፡፡
“ከዚህ እንመለስ!” አለ ጓደኛዬ፡፡
“ለምን? ....ካለቻት ሴትዮ ጋር እናገናኛት!”
“በቃ ተፈራ ህንፃ ብላለች እኮ!” ብሎ ሊበሽቅ ዳዳው፡፡
“ግድ የለህም፤ ብናገናኛቸው ህሊናችን ያርፋል!”
በዚህ መሀል ልጅቷ እቦታው ስትደርስ፣ ሀሳባችንን አድምጣ ስልክ ካዋራች በኋላ፤ “በቃ ሂዱ!”
“ኧረ እናገናኝሽ!” አልኩ እኔ፡፡
“በቃ አመሰግናለሁ!” ነቃ አለች፡፡
ጥቂት ወደፊት እንደገፋን አንዳች ነገር ወደ ኋላ እንድመለከት አደረገኝ፡፡ የጥበቃ ሰራተኞቹ አስገብተው፣ እንግዳ ተቀባይ መስለው አንድ ነገር እንዳያደርጓት ብዬ ስጋት ገብቶኝ ነበር፡፡
በጀርባዬ በኩል ሳያት ጀርባዋ ላይ ጥምጥም ያሉ እጆች አየሁ፡፡ ተቃቀፉ፤ተሳሳሙ፡፡ እንዳለችው ግን ሴት አልነበረችም፡፡ ወጠምሻ ጎረምሳ ነው፡፡
“አየህ አይደል!” አለኝ፤ጓደኛዬ፡፡
“ምናልባት ከገጠር የመጣች የቤት ሰራተኛ ሆና… ያገሯ ልጅ ወይም…..”
እየተሳሳቅን  ተመለስን፡፡

Read 1507 times