Print this page
Sunday, 17 January 2021 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

        "ለተሻለ ነገ ህዝባችንን ማስተማር፣ ማንቃትና ማደራጀት የወቅቱ ወሳኝ ነገር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ሊተገበር የሚገባ የዕድገትና የብልፅግና መንገድ ነው። ለመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥራት ላለው ትምህርት ቅድሚያ መስጠትን ዓላማ ከማድረግ ችላ ሊሉ አይገባም፡፡"
 
                ወደ ሀገራችን በተመለሰች የሃሳብ ቀልድ እንጀምር፡-
ሁለት የተለያዩ ዕምነት አራማጆችና አንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪ መሽቶባቸው፣ወደ አንድ የገጠር ማረፊያ ጎራ ብለው መኝታ ለመከራየት ይጠይቃሉ፡- ባለቤቱም፡-
ሁለት ክፍሎች እንዳሉት በመግለፅ አንደኛው ውስጥ ሁለት አገልጋዮች ሲኖሩ፣ ሁለተኛው ግን ለሁለት የቤቱ እንስሳት ማደሪያ እንደሆነ አስረዳቸው። ሰዎቹም አማራጭ ባለመኖሩ አንደኛው ከእንስሶቹ ጋር እንዲያድር ተስማሙ። ወዲያውም አንዱ በፍቃደኝነት በሁለተኛው ክፍል ለማደር ተሰናብቷቸው እንደሄደ፣ የተቀሩት አልጋቸው ውስጥ ገቡ። ሰውየው ግን ብዙም ሳይቆይ ተመልሶ በሩን መደብደብ ጀመረ። ከፈቱለትና፤
“ምነው?” ሲሉት
“ከአሳማ ጋር ለማደር ሃይማኖቴ አይፈቅድም” አላቸው።
በዚህን ጊዜ ሌላኛው እኔ እቀይርሃለሁ ብሎት ወደሚቀጥለው ክፍል ሄደ። እሱም እንደ መጀመሪያው ተመልሶ በራቸውን አንኳኳ። ሲከፍቱለት፤
“ውሻ ባለበት መተኛት አይቻለኝም” አላቸው።
 በመጨረሻም ፖለቲከኛው ሄደ። አፍታም ሳይቆይ ግን የመኝታ ቤታቸው በር በሃይል ተበረገደ። ሰውየው አልነበረም።… ማን ይመስላችኋል?...
*   *   *
ልጅ እያለሁ ከዕለታት በአንዱ ቀን “ንዝህላል” የሚያሰኝ ጥፋት ሰራሁ። አባቴ ካወቀ እንደምቀጣ ስለማውቅ ለምሳ ወደ ቤት አልገባሁም። የሆዴን በሆዴ ይዤ ከጓደኞቼ ጋር ኳስ ስጫወት…
“ተመዝገ” በማለት ጠራኝ ባርቺኒ። ሰውየው ካንድም ሁለት ጊዜ እጄን ይዞ ላባቴ በማስረከብ በጥፋቴ ተቀጥቻለሁ። ስገረፍ እንኳ ፈጥኖ አያገላግለኝም። ዓይኖቹ ውስጥ ግን ሁሌም ደግነት እመለከት ነበር። አያድርስ እንጂ ባርቺኒ ለአባቴ ሲል ከመሞት ወይም ከመግደል ወደ ኋላ የሚመለስ አልነበረም። አንዳንዴ ቀስ ብዬ “ሻንቂላ” እያልኩ እሰድበዋለሁ። እየሰደብኩት መሆኑን ቢያውቅም ለወላጆቼ አይናገርም።… ቢናገር ኖሮ … ወዬልኝ ነበር!
“ተመዝገ”… እንደገና ተጣራ።
“አቤት”
“ና… ወርቁ ና”… ወርቁ ይጠራሃል ማለቱ ነው። ጥፋቴ ተነቅቶብኛል ልገረፍ ነው።… ወደ አያቴ ቤት ሩጫዬን ለቀቅሁ። የአጥርዋ በር ጋ ከመድረሴ ባርቺኒ  ተከትሎ ለቀም አደረገኝ።
አያቴ ደጃፏ ላይ የሚቸረቸር ከሰል እየመደበች ነበር። ክክ የሰለቻቸው የሃያ አምስተኛ ብርጌድ ጦር ሰራዊት አባላት በዱቤ እየጻፉ የሚቀለቡበት ውቴልም ነበራት።… ያኔ የስጋ ወጥ አርባ ሳንቲም ነው። የጦር ካምፑ ዋና በርና የአያቴ ደጃፍ ትይዩ ናቸው። በመሃላቸው ታላቁ የሳር ሰፈር ጎዳና አለ።  ቁና ቁና እየተነፈስኩ፡-
“አኮ!” ብዬ ተጣራሁ። አያቴ ቀና ብላ…
“ቢወጣ ምን ሆንክ?” አለች በመደንገጥ።
“አባዬ ሊገርፈኝ ነው” አልኳት። እየተነጫነጨች…
“ቆይ አብረን እንሄዳለን” አለች። እጇን ተለቃልቃ፣ ነጠላዋን አንጠልጥላ ስትወጣ ባርቺኒና እኔ ቤት ደርሰናል። አባቴ ባንድ እጁ አለንጋ፣ በአንድ እጁ የተቀደደውን መጽሐፍ ይዞ…
“ይህን ያደረገ ማነው?” ብሎ ሲደነፋ ባርቺኒ ለመጀመሪያ ጊዜ… “ተው ወርቁ … ተው” ብሎ ገላገለኝ እንጂ አያቴ እስክትደርስ መጠብጠቤ አይቀርም ነበር። የዛን ቀን ባርቺኒ ለምን ከአለንጋ እንዳስጣለኝ የገባኝ ካደኩ በኋላ ነው። የአባቴን መጽሐፍት እየደበቅሁ እንደማነብ ያውቃል። ሆን ብዬ እንዳልቀደድኩት ተረድቷል። መማርና ማንበብ ለሱ ትልቀ ነገር ነበር።
ባርቺኒ ወቲኒ የተወለደውና ያደገው ማጂ አውራጃ ተብሎ ሲጠራ በነበረው የአገራችን ክፍል፣ የሱርማ ማህበረሰቦች ከሚኖሩባቸው መንደሮች ባንደኛው ውስጥ ነው። ከናቱ ጋር አንድ ጎጆ የሚጋራው ባርቺኒ፤ እዛው አካባቢ ከሚኖረው ታላቅ ወንድሙ ጋር አንድ ቀን በመጠጥ ግፊት ጦር ተማዘዙ። ወንድምየው ሞተ፣  ባርቺኒ ታሰረ።
ወዳጄ፡- የማወራልህ በስልሳዎቹ የሆነውን እውነተኛ ታሪክ ነው። የባርቺኒ እናት ያኔ የአውራጃው ፍ/ቤት ዳኛ ወደነበረው አባቴ ዘንድ በመመላለስ “አንደኛው ልጄ አንዴ ሞቷል፣ የሞተ አይመለስም። ሁለተኛው ልጄ በመታሰሩ ጧሪ አጥቻለሁ። መንግስት ጉዳቴንና ደካማነቴን አይቶ ቀሪው ልጄን በምህረት ይፍታልኝ" በማለት አለቀሱ። ጉዳዩን መርምሮ በህግ የመወሰን ስልጣን ደግሞ የከፍተኛ ፍ/ቤት ነው። ስለዚህ ተዘዋዋሪ ችሎት ወደ ቦታው እስኪመጣ መጠበቅ ወይም ባርቺኒ ወደ ጅማ መሄድ ነበረበት። በሴትየዋ ሃዘን የተነካው አባቴ፤ በአጋጣሚ ወደ አጋሮ በመዛወሩ፣ በሚመለከታቸው ሃላፊዎችና የአካባቢ ሽማግሌዎች በተሰናዳ ቃለ ጉባኤ አባሪነት፣ ሃላፊነቱን ወስዶ፣ ባርቺኒን ያለ አጃቢ ወደ ጅማ ይዞት መጣ። ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም የናኛውን አቤቱታ ያገናዘበ ሰነድ፣ ጥፋቱ የወንድምየው መሆኑን የህግ ምስክሮች ያረጋገጡበት መዝገብና ተያያዥ ነገሮች ተመርምረው ባርቺኒ በነፃ ተለቀቀና አብሮን መኖር ጀመረ። ባርቺኒ ከማጂ ሲመጣ የለበሰው የአባቴን ካፖርት ሲሆን በተረፈ መላ መላውን ነበር። አልተገረዘም። ሁለት ዓመት አብረን ስንኖር የውስጥ ልብስ መልበስ የጀመረው ከብዙ ወራቶች በኋላ ነው። ገላውን መሸፈን አይመቸውም።
አባቴ አጋሮ በመስራት ላይ እያለ ወደ ጅማ በመመላለስ ከቤተሰብ ጋር የሚቆየው እሁድና ቅዳሜን ብቻ ነው። የአጋሮ መንገድ ከቤታችን አጠገብ በመሆኑ ሲመጣ የሚቀበለውና ሲሄድ የሚሸኘው ባርቺኒ ነው። ባርቺኒ አማርኛ ለመልመድ ምንም ያህል ጊዜ አልፈጀበትም።
አንድ አዘቦት ቀን ምክንያቱን በማላስታውሰው ነገር ባርቺኒና እናቴ ተጣሉ።
“አንቺ መጥፎ፣ ወርቁ  ጥሩ” አለና ጎዳናውን ተከትሎ በእግሩ ወደ አጋሮ (44 ኪ.ሜ) ሸመጠጠ፡፡ ….እናቴና ጎረቤታችን ቢለምኑትም አሻፈረኝ አለ፡፡ አርብ ምሽት ከአባቴ ጋር ተመለሱና አስታረቃቸው፡፡
ባርቺኒ ወደ እናቱ መሄድ ነበረበት፡፡ አባቴ የማጂ ሰዎች ጅማ ሲመጡ የሚያርፉበት ቦታ ባርቺኒን ወስዶ አስተዋወቀውና አንዳንዴ እየሄዱ አብሯቸው ጠጅ ይጠጣሉ፡፡ ባርቺኒ ተሰናብቶን ወደ ሀገሩ ስንሸኘው፣ የአባቴና የሱ ዓይኖች ላይ እንባዎች አይቻለሁ፡፡ ከማናችንም  በላይ ሁለቱ ሰዎች ይዋደዳሉ፡፡
ከጥቂት ወራት በኋላ አንድ ቀን እቤት  ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ሳነብ ባርቺኒ ተመልሶ መጣ፡፡
“ምነው?”ስለው
“ደህና ናችሁ? አለኝ እየሳቀ፡፡
“ደህና ነን”
“አማማ የለችም?”
“የለችም”
“ወርቁ ስራ ኖ”
“አዎ”
“ና” አለኝና ወደ ገበያ ይዞኝ ሄደ፡፡ መንገድ ላይ፤
“ለምን መጣህ? አናትህ ደህና አይደደሉም?” ብዬ ጠየቅሁት
“እናቴ ጋ አልሄድኩም” አለኝ፡፡
“ምነው?”
“ለምን?”
“ቦንጋ የገጠር መንገድ ስራ ላይ ተቀጥሬ ስሰራ ቆይቼ መምጣቴ ነው፡፡ ዛሬ ነው ወደ ማጂ የምሄደው” አለኝ
“ታዲያ ለምን ወደ ኋላ ተመለስክ፤ በዛው አትሄድም?;..... ፀጉሬን እያሻሸ ፈገግ ብሎ ዝም አለ፡፡
ገበያ ገብተን አንድ በግ ገዛ፡፡ እየነዳን በመምጣት ላይ ሳለን፣ ሰፈር መዳረሻችን ላይ ቆም ብሎ ከኪሱ የተጨማደደ ፖስታ አውጥቶ “ይሄን ለወርቁ ስጥ፤ ይሄኛው ደግሞ ላንተ ነው" ብሎ አንድ ብር ሰጥቶኝ፣ ግንባሬን ስሞ ወደ ጅማ አቀና፡፡
….አጎቴ ባርቺኒ ምሽት ላይ ቤተሰቦቼ የሆነውን ሲሰሙ አለቀሱ፤ አባቴ ፖስታውን ከፍቶ ሲያነብ “ወርቁ አመሰግናለሁ፣ እናቴ ትመርቅሀለች፤ በዚህ ገንዘብ ለተመስገን ልብስ ግዛ” የሚል ፅሁፍና ሰላሳ ብር ውስጡ ነበር፡፡ ለካስ ባርቺኒ ወቲኒ ተመልሶ ወደ ጅማ የመጣው፣ ማንበብና መፃፍ ያስተማርኩበትን ውለታ ለመክፈል አስቦ ነው፡፡
ወዳጄ፡- ባርቺኒን ሳስብ አሁን በቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባቢ የሚኖሩበትን ወገኖች አስባለሁ፤ አለማወቃቸውን ተጠቅመው በነዚህ ምስኪን ዜጎች ላይ ሁዋላ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰብ በመጫን፣ ከወንድሞቻቸው ጋር በማጋጨት፣ ወደ ስልጣን  ለመምጣት መሞከር ያሳዝናል። ለተሻለ ነገ ህዝባችንን ማስተማር፣ ማንቃትና ማደራጀት የወቅቱ ወሳኝ ነገር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ሊተገበር የሚገባ የዕድገትና የብልፅግና መንገድ ነው። ለመጪው ምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥራት ላለው ትምህርት ቅድሚያ መስጠትን ዓላማ ከማድረግ  ችላ ሊሉ አይገባም፡፡…”መሞቴ ካልቀረ የተማረ ይግደለኝ” ይላል አበሻ!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሶስተኛው ሰውዬ ወደ እንስሶቹ ክፍል ሲገባ ውሻውና አሳማው በድንጋጤ ነፍሳቸውን ለማዳን ነበር፣ ወደ ሰዎቹ ክፍል በመሮጥ በሩን በርግደው የገቡት።
ሠላም!

Read 1960 times