Saturday, 16 January 2021 12:19

በክርክርና ውይይት የማሸነፊያ ስልቶች ውጤታማ የሆነ ተአማኒነትን እንዴት መፍጠር ይቻላል?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   የተአማኒነት አቀራረብ
ጥንታዊያን ግሪኮችና ሮማያዊያን ንግግር ዐዋቂዎች፤ አንድ ክርክር ይበልጥ አሳማኝ የሚሆነው አድማጭ በተናጋሪው ላይ እምነት ሲኖረው ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እንደ አርስጣጣሊስ (Aristotle) እምነት፤ አንዲህ ዓይነት ነገር የሚኖረው በተናጋሪው የቀደመ ዝና ሳይሆን በወቅቱ የሚቀርበው በራሱ በንግግሩ ውስጥ በባለው አሳማኝ ፍሬ ነገር ነው፡፡ የተናጋሪው ባህሪና የሚያቀርበው ነገር፣ የተናጋሪው የአነጋገር ቃና፣ የቃላት ምርጫ፣ ምክንያቶችን በአግባቡ መደርደሩ፣ የተለያዩ አማራጮች አመለካከቶችን ሲያቀርብ የሚያሳየው ሥርዓትን የተከተለ ሁኔታ በአድማጮቹ ዘንድ የተአማኒነት ሰብዕና እንዲፈጠር ያደርገዋል፡፡ አንድ ፀሀፊ ወይም ተናጋሪ ተአማኒነትን የሚፈጥርባቸው ሶስት መንገዶች አሉ፡፡ የእርስዎ መንገድ ከእነዚህ አንዱ ከሆነ የሚከተሉትን አስተያየቶች ተግባራዊ ያድርጉ፡፡
በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ ዕውቀት ይኑርዎት፡፡
ሚዛናዊ ይሁኑ፡፡
ሀ.ተደራሾች ጋር የሚያገናኝዎትን ድልድይ ይገንቡ፡፡
እያንዳንዳቸውን በአጭሩ እንመልከት
ሀ. በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ እውቀት ይኑረዎ።
ታማኝነትን የማግኛ የመጀመሪያው መንገድ ታማኝ መሆን ነው፤ ይህም ማለት ጠንካራ መሰረት ያለው ዕውቀት ይዞ መከራከር፣ በቂ ምሳሌዎች፣ የግል ተሞክሮዎችን፤ አህዛዊ መረጃዎችንና ሌሎች ለጉዳዩ አስፈላጊ የሆኑ ጠቃሚና ተጨባጭ መረጃዎችን ማቅረብ መቻል ማለት ነው። የቤት ሥራዎትን ከሰሩ በእርግጠኝነት የአብዛኛዎቹን ተደራሲያን (audiences) ትኩረት ይስባሉ፡፡
ለ ሚዛናዊ ይሁኑ?
በሚያቀርቡት ርዕስ ላይ ዕውቀት ያለዎት ከመሆን በተጨማሪ ለአማራጭ አመለካከቶችም ሚዛናዊነትንና ትህትናን በተግባር ማሳየት አለብዎት፡፡ ይህ የሚሆንበትም ምክንያት እውነተኛ ክርክር ሊከሰት ከሚችልባቸው አቀራረቦች አንዱ፣ ሰዎች ከሌላው ሀሳብ ጋር ያላቸውን ልዩነት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሲገለፁ ብቻ ነው፡፡ የሌላውን ወገን ሀሳብና የቀረቡትን አማራጭ ነጥቦች የተረዱና የተገነዘቡ መሆንዎን በተግባር ካሳዩ፣ የእርስዎ ተአማኒነት የበለጠ ይጠናከራል፡፡ በእርግጥ ተቃራኒ አመለካከትን በአግባቡ ሊያጣጥሉ የሚችሉበት ጊዜ ይኖራል፡፡ እነዚህን ጊዜያት ግን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በአብዛኛው የሚከሰቱትም ተደራሲዎችን ስለ አመለካከትዎ በቅድሚያ ዝንባሌ እንዲያሳዩ መልዕክት ሲያስተላፍልፉ ነው። በአጠቃላይ ለአማራጭ አመለካከቶች ድጋፍና ክብር ማሳየት ከሁሉም የበለጠ ስልት ነው፡፡
ሐ. ከተደራሲዎች ጋር የሚያገናኙትን ድልድይ ይገንቡ።
ክርክርዎን በጋራ በሆኑ እሴቶችና ታሳቢዎች ላይ እንዲመሰረት በማድረግ መልካም ፈቃደኝነትዎን በተግባር ካሳዩ እምነት የሚጣልብዎትን በተደራሲያኑ ዘንድ የተደራሲውን አመለካከት የሚያከብሩ ሰው መሆንዎን የሚያሳይ ገፅታን ይገነባሉ፡፡
እምነታችንና ስሜታችንን እንዴት ማቅረብ ይቻላል?
አንድን ነገር መገንዘብ ማለት ስለዚያ ነገር የሚሰማንን ስሜት መረዳት በመሆኑ ስሜትን ገላጭ አቀራረብ የግድ ምክንያታዊ ባይሆንም አመክንዮ ያልሆነን ነገር የማወቅ ዕድል ሊሰጠን ይችላል፡፡ ስሜትን ገላጭ አቀራረብ አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ሲያቀርብ፣ በዚያ ጉዳይ ውስጥ ስለ አለው ጥልቅ ነገር እንድናይ ይረዳናል፡፡ ለዚህም  ነው ብዙ ጊዜ ክርክሮች፣ ታሪኮችን በመጠቀም የአንድ ችግር እውነታ በስሜታችን አማካይነት እንድናይ፣እንዲሰማንና ጎምዛዛም ቢሆን እንድናጣጥም  የሚያደርጉን፡፡
ሰሜትን ገላጭ አቀራረቦች ሕጋዊ የማይሆኑት አንድን ጉዳይ ግልጽ ከማደረግ ይልቅ ግራ የሚያጋባ ሲያደርጉት ነው። ፀሐፊዎች ወይም ተናገሪዎች የለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ስሜት ገላጭ የሆኑ አቀራረቦችን መፍጠር ይችላሉ፡፡ እነዚህም ተጨባጭ ቋንቋ፤ ልዩ ምሳሌዎችና ማነፃፀሪያ ነገሮች፣ ትረካዎች፣ ደርብ ትርጉም ያላቸው ቃላት፣ ዘይቤያዊ አነጋገርና ተመሳሳይ ማመሳከሪያዎች ናቸው፡፡
(በሲሳይ አሰፋ ተሰማ ከተዘጋጀውና “በክርክር እና በውይይት የማሸነፊያ ስልቶች” በሚል ርዕስ ከበቃው መጽሃፍ የተቀነጨበ)Read 2332 times