Saturday, 23 January 2021 11:14

3ቱ የአገራችን የህልውና አደጋዎች፣ የምርጫ አጀንዳዎች!

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

 ቁጥር 1. የህልውና አደጋዎች፤የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ጨምሮ፣” የማንነት ጥያቄ”፣ “የብዝሀንነት”ና ሌሎች የዘረኝነት ቅኝቶች…..
ቁጥር 2 የህልውና አደጋዎች፣…የተቃወሰ የድህነት ኢኮኖሚ፣ የተናጋ የችጋር ኑሮ የወጣቶች (የተመራቂዎች) ስራ አጥነት፣ ኢንዱስትሪ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት እጦት፣ የመንግሰት ፕሮጀክቶች  ብክነት ቁጥር 3 የህልውና አደጋስ የትኛው ነው?


                     በኮምቦልቻ አቅጣጫ፣ ግማሽ ድረስ የተጠናቀቀው የባቡር መስመር፣ ለሁለት ዓመት ስራ ያልጀመረው፣ በምን ምክንያት ነው በሉ። በኤሌክትሪክ እጦት ሳቢያ ነው፤ ለአገልግሎት ያልበቃው። ብዙ ቢሊዮን ብር የወጣበት የባቡር ሃዲድ፣ ያለ አገልግሎት ስራ ሲፈታ፣ ኪሳራው ቀላል እንዳልሆነ አስቡት። ይህም ብቻ አይደለም ችግሩ። ቀሪው የባቡር መስመር ግንባታ፣ እየተጓተተ ተጨማሪ ኪሳራዎችን ያስከትላል። ለምን? በኤሌክትሪክ እጦት ሳቢያ።
በርካታ ቢሊዮን ብር የፈሰሰባቸው ዘይት ማምረቻ ፋብሪካዎችስ? በሙሉ አቅማቸው መስራት አይችሉም። በቂ የቅባት እህል ወይም ሌላ ግብአት የለም። ከውጭ ማስመጣት የግድ ቢሆንም፣ የውጭ ምንዛሬ ደግሞ ችግር ነው። ግን ምን ዋጋ አለው? ይሄ ሁሉ ችግር ቢወገድ እንኳ፣ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅም ዘይት ሊያመርቱ አይችሉም። ግዙፉ የቡሬ ዘይት ማምረቻ ተቋምን ተመልከቱ። በሩብ ያህል አቅም ብቻ ነው የሚሰራው። ለምን? በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት።
በአዲስ አበባ የተገነባው ትልቁ የዳቦ ፋብሪካም፣ በኤሌክትሪክ ችግር ተይዟል። ለነገሩ፣ የስንዴ ዱቄትም በቀላሉ አይገኝም። በመከራ ነው። ዘግይቶም ሆነ በጥቂቱ ዱቄት ሲመጣም ግን፣ የፋብሪካው ስራ ይቃናል ማለት አይደለም። ዱቄት ከተቦካ በኋላ፣ ኤሌክትሪክ ይቋረታል። ተቦክቶ ምን ይሁን? የተጋገረው ብዙ ሺ ዳቦስ፣ ሊጥ ሆኖ ይቅር? የነዳጅ ጀኔሬተር መጠቀም ደግሞ፣ ወጪው አይቀመስም።
ለዚያውስ፣ ዳቦውን፣ መንግስት ከዓመታት በፊት በወሰነው የዋጋ ተመን ለመሸጥ? በጭራሽ አያዋጣም። ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ኤሌክትሪኩ በየሰዓቱ ይቋረጣል፤ አንዳንዴም በየደቂቃው ይቆራረጣል። ሲብስበትም፣ ቀኑን ሙሉ ይጠፋል። በማግስቱም ሳይመጣ ይቀራል።
በዚህ አያያዝ፣ ለስንት ጊዜ መራመድ ይቻላል? የፓስታና የማካሮኒ ፋብሪካዎችም፣ በኤሌክትሪክ እጥረት ሳቢያ፣ ከእለት እለት፣ ከዓመት ዓመት ለተመሳሳይ ኪሳራ ይዳረጋሉ።
ምን ይሄ ብቻ! ብዙ ቢሊዮን ብር የወጣባቸው “የኢንዱስትሪ ፓርኮች” አሉላችሁ። በአብዛኛው፣ በኤሌክትሪክ እጦትና በኤሌክትሪክ እጥረት ሳቢያ፣ ለፍሬ አልበቁም። ሃብት ግን ፈስሶባቸዋል። ወጪ እንጂ ገቢ አላሳዩም - ከአንድ ሁለቱ በስተቀር።
በየክልሉና በየከተማው፣ አነስተኛ ተቋማትን ለማሳደግ፣ የስራ እድሎችንም ለመፍጠር ይጠቅማሉ ተባሉ ማዕከላትም፤ ከችግር አላመለጡም። በርካታ ማዕከላት፣ ያለ ኤሌክትሪክ ደንዝዘው ቀርተዋል። የኤሌክትሪክ መስመር ቢያገኙ እንኳ፣ አለፈላቸው ማለት አይደለም። ኤሌክትሪኩ በየቀኑ ሃያ ጊዜ እየተቆራረጠ፣ በዚህም ሳቢያ ስራቸው እየተዳከመ፣ ከእንፉቅቅ መገላገልና ዳዴ ማለት አቅቷቸዋል።
ምናለፋችሁ! የኤሌክትሪክ እጦትና እጥረት፣ ከበርካታ ዓመታት ድህነት ጋር የተቆራኘ ነባር ችግር ስለሆነ፣ ያልተነካና ያልተቸገረ አካባቢ የለም። የአገር የኢኮኖሚ ደረጃንና የኑሮ ሁኔታን፣ ድህነትንና ብልፅግናን በቀላሉ ለመለካት የሚፈልግ ሰው፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦትንና ፍጆታን መለካት ይችላል። የዘንድሮ ወይም የአምና፣ የ5 ዓመት ወይም የ10 ዓመት ችግር አይደለም።  የኤሌክትሪክ እጥረት፣ እድሜው፣ እንደ አገሪቱ ድህነት፣ ረዥም ነው። ተመልሶም ኢኮሚኖን ያዳክማል፤ ኑሮን ያጎሳቁላል።
በየከተማው፣ ኤሌክትሪክ እየጠፋ፣ የእልፍ አእላፍ መተዳደሪያ ስራ ምንኛ እንደሚስተጓጎልና እንደሚበላሽ አስቡት። ከባንክ እስከ ፀጉር አስተካካይ፣ ከውሃ አገልግሎት እስከ ክሊኒክ፣ የኪሳራው መጠንና የጉዳቱ አይነት፣ ለህልቆ መሳፍርት ያስቸግራል።
እንግዲህ ይታያችሁ። አገራችንን ተብትበው መከራዋን ከሚያበዙ፣ 3 አደገኛ ችግሮች መካከል አንዱ፣ “የኑሮ ችግር” ነው - “የኢኮኖሚ ድቀት”። ከባድ ድህነት አለ፣ የበርካታ ሚሊዮን ወጣቶች ስራ አጥነት አለ። ይህን የሚያባብሱ፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ይታከሉበታል። በዚያ ላይ፣ የመንግስት ፕሮጀክቶች የሃብት ብክነት ጨምሩበት። ይህም አልበቃ ብሎ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያዳክም የተንዛዛ መሰናክልና ቁጥጥር ሞልቷል። እየተዘወተረ የመጣው አውዳሚ ስርዓት አልበኝነትና አመፅም አለ። ….
ይሄ ሁሉ ተደምሮ፣… የኑሮ (የኢኮኖሚ) ችግር፣ የአገር ህልውናንም ለጥፋት የሚያጋልጥ አደጋ ሆኗል። እና ምን ተሻለ?
ኑሮን የማሻሻል፣ ኢኮኖሚን የማሳደግና የስራ እድሎችን በብዛት የመክፈት ተስፋ፣ ያለ ኢንዱስትሪ፣ ያለ እልፍ አእላፍ ፋብሪካዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ ሊታሰብ አይችልም። ኢንዱስትሪም ያለ ኤሌክትሪክ፣ የፋብሪካዎች ምርትም ያለ ትራንስፖርት፣ እውን ሊሆን አይችልም።
በአጭሩ፣ እንደ ኢንዱስትሪና እንደ ፋብሪካ፣ …. ኤሌክትሪክም፣ ለኢትዮጵያ፣ የህልውና ጉዳይ ነው። ይሄ፣ ሚስጥር አይደለም።
ቁጥር 1 የህልውና አደጋ?
“የብሔር ብሔረሰብ ፓለቲካ” እና ተዛማጅ የዘረኝነት አስተሳሰቦች፣ የሰዎችን ሕይወትና የአገርን ህልውና የሚያጠፉ ቁጥር 1 አደጋዎች እንደሆኑ፣ ገና ድሮ ሊታወቅ ይችል ነበር። ይህንም፣ ከዓመታት በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ፅሁፎችን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል። ዛሬ ግን፣ አደጋውን በእውን እያየነው ነው። የዘረኝነት አስተሳሰቦችና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ቀንደኛ የሕይወትና የሕልውና አደጋዎች እንደሆኑ፣ በየእለቱ እያየን አይደል?
ቁጥር 2 የህልውና አደጋስ?
የተቃወሰ የድህነት ኢኮኖሚና የተናጋ የችጋር ኑሮ፣ እንደድሮ የመከራ ጭነት ብቻ አይደሉም። በዛሬው ዘመን፣ የሕልውና አደጋ ሆነዋል። የብዙ ሚሊዮን ወጣቶችና የተመራቂዎች ስራ አጥነትን ብቻ ማየት ይበቃል።
የስራ እድልና የኢኮኖሚ እድገት ደግሞ፣ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ትልልቅና ባለብዙ ሕዝብ አገሮች ውስጥ፣ ያለ ኢንዱስትሪ፣ ተስፋ የላቸውም።
….በሌላ አነጋገር፣ የኢንዱስትሪ፣ የፋብሪካና የኤሌክትሪክ እጦት፣ ከዚህም ጋር የተያያዙ የሃብት ብክነቶችና ተዛማጅ እጥረቶች፣ የአገራችን ቁጥር 2 የህልውና አደጋዎች ናቸው።
ለወደፊት የህልውና አደጋ ይሆናሉ ማለቴ አይደለም። አደጋቸውንማ እያየነው ነው። ስንትና ስንት ጥፋት ደረሰ? አገሪቱ ወደ ለየለትና መመለሻ ወደ ሌለው ትርምስ፣ ወደ እንጦሮጦስ፣ ስንቴ አፋፍ ላይ ደርሳ፣ ስንቴ ለጥቂት ተረፈች?
ቁጥር 3 የህልውና አደጋስ ምንድን ነው?
ጥያቄው እዚህ ላይ ነው።  የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና የኢንዱስትሪ እጦት…. ሁለቱ አደጋዎች ቀላል አይደሉም። ሕልውናን የሚያጠፉ አደጋዎች ናቸው። ታዲያ፣ …
ታዲያ፣ በየእለቱ የሚደርሰውን የጥፋት መዓት፣ የየእለቱን የድህነት ኑሮ የጣዘበው ሰው፣ የስራ አጥ ወጣቶችን ብዛት የሚያይ ሰው፣ አገሪቷ ቋፍ ላይ መሆኗንም በተደጋጋሚ በእውን የተመለከተ ሰው፣ በዘረኝነት ይጫወታል?
ሰዎችን በብሔር ብሔረሰብ የሚያቧድኑ አስተሳሰቦች ላይ ለመራቀቅና ለመቀናጣት ያምረዋል? የብሔር ማንነትና ብዝሃነት እያለ ለመደስኮር ይሽቀዳደማል? “ካልቸራል ሪሌቲቪዝም”፣ “ኤቲኒክ ሪሌቲቪዝም” እያለ፣ ያንኑን አደገኛ የዘረኝነት አስተሳሰብ እንደአዋቂነት ለመስበክ ይሯሯጣል? የዩኒቨርስቲዎች ስራ ምን ሆነና! ይህንኑን ያስተምራሉ፡፡ በቲቪም እየቀረቡ ይሰብካሉ። የስካር አስተሳሰብ በሉት፡፡
በኤሌክትሪክስ ይቀለዳል? ኢንዱስትሪንና ፋብሪካን እንደ ጠላት ለማየት ይቅርና፣ ቸል ለማለትስ ይቃጣዋል? ትራንስፖርት ላይ ያላግጣል?
“ከመኪና የፀዳ መንገድ” በሚል ፈሊጥ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተጀመረው ቀልድ፣ “ከመኪና ትራፊክ የፀዳ ቀን” ወደ ሚል ማላገጫ ዘመቻ ተባብሶ የጦዘው፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ለዚያውም፣ በአዲስ አመት በዓል ዋዜማ፣ ጳጉሜ 4 ቀን ነበር የዘመቻው ኢላማ፡፡ “መኪና ዝር የማይልበት ቀን”!ወይ ቀልድ!
አዎ፣ በዘረኝነት የሚጫወትና የሚራቀቅ፣ በኤሌክትሪክ የሚቀልድና የሚያላግጥ ሰው ሞልቷል። ለዚያውም በግላጭ፣ ለዚያውም በአደባባይ ነው እንጂ። ብዙዎቻችንም፣ ወይ አላዋቂ ተባባሪ ነን። ወይ ጉዳያችን ብለን አናስተውልም።
ባለፈው ሳምንት፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እልፍና እልፍ ሆነን ስንሮጥ፣ ምንኛ ያማረና እግጅ አስደሳች አጋጣሚ እንደነበር አስታውሱ።
የመዝናኛ ድግሱን፣ ከአመታት በፊት ከአእምሯቸው አፍልቀው፣ ባላሰለሰ ጥረትም ለታላቅነት ያበቁ ጥበበኞችና ትጉህ ሰዎች ፣ምስጋና ይድረሳቸው።
ለሩጫው የለበሰነው ማሊያ ላይ፣ ከጀርባችን ያዘልነው ዋና የፅሁፍ መልዕክት ግን፣ ሌላ ነገር ነው፡፡ በእርግጥ፣ፅሁፋን  ለማየት ደንታም ጊዜም አልነበረንም። የአንድ ድርጅት ማስታወቂያ ነው። ለአእዋፍ የማይመቹ የሃይል ማመንጫ ተቋማትንና ሃይል ማስተላለፊያዎችን ይቃወማል ማስታወቂያው።
የሃይል ማመንጫና ማስተላለፊያ ሁሉ፣ ለአእዋፍ የተመቸ መሆን እንዳለበትም ይገልፃል። Bird- Safe Energy Infrastructure ይላል ማስታወቂያው። ለአእዋፍ የማይመች የኤሌክትሪክ ተቋምና የማስተላለፊያ መስመር፣… መወገድ አለበት ፤ እቅድ ከሆነም መሰረዝ ይገባዋል ነው?
ሌሎች ድርጅቶች ደግሞ አሉ። የወንዞችን ነባር የፍሰት መጠንና የፍሰት አቅጣጫ በፍፁም መነካት የለበትም ይላሉ፡፡ የግድብ ግንባታዎችን ይቃወማሉ። ለማቋረጥም ዘመቻ ያካሂዳሉ። በእነዚህ ዘመቻዎች ሳቢያ፣ የግቤ 3 ግድብ፣ ለበርካታ ዓመታት እየተጓተተ ኢትዮጵያ ብዙ ከስራለች። እርዳታና ብድር ተከልክላለች።
የፀሃይ ሃይል፣ የነፋስ ተርባይን፣ ባዮጋዝ ምናምን እየተባለ ብዙ ቢሊዮን ብር በከንቱ ባክኗል። ባዮጋዝ ተብለው ከተሰሩት ግንባታዎች ምን ያህሉ አገልግሎት ይሰጣሉ? የፌደራል ኦዲተር በደቡብ ክልል ባካሄደው ምርመራ እንዳረጋገጠው፤ ከግማሽ የሚበልጡት ግንባዎች ከጥቅም ውጭ ናቸው። ከንቱ ኪሳራ ነው።
ለጂኦተርማል፣ ለፀሐይ ሐይልና ለነፋስ ተርባይን ተብሎ ከፈሰሰው 2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥም፣ ከግማሽ በላይ የሚሆነው፣ በከንቱ ባክኖ ቀርቷል። አሁን ባለው ምንዛሬ ከተሰላ፣ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ የድሃ አገር ሃብት  በብላሽ ጠፍቷል።
በኤሌክትሪክና በሃብት እጦት የተቸገረችው አገር ውስጥ፣ በኤሌክትሪክና በኃብት መቀለድ ምን ይባላል? የስካር አስተሳሰብ ነው።
እንዲህ አይነቶቹ የተሳከሩ፣ ብጥስጣሽ፣ አላማቢስ፣ እና መርህ የለሽ የጭፍንነት አስተሳሰቦች፣ቁጥር 3 የህልውና አደጋዎች ናቸው፡፡


Read 3734 times