Print this page
Monday, 25 January 2021 00:00

የ46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት - አንዳንድ ነገሮች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  የ78 አመቱ የእድሜ ባለጸጋ ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ባለፈው ረቡዕ በዋይትሃውስ በተከናወነው በዓለ ሲመት ቃለ መሃላ ፈጽመው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑ ሲሆን፣ ካማላ ሃሪስም ቃለ መሃላ ፈጽመው የአገሪቱ የመጀመሪያዋ ጥቁር እስያዊት ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል። ከበዓለ ሲመቱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የሚከተሉትን መራርጠንላችኋል፡፡
ከሳምንታት በፊት የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን በሚገኘው ካፒቶል ሂል የፈጸሙትን ነውጠኛ ድርጊት ተከትሎ፣ በአገሪቱ ያንዣበበው ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት፣ መላውን አሜሪካ በውጥረት በዓለ ሲመቱንም በከፍተኛ የደህንነት እና ጸጥታ ጥበቃ አጨናንቆት እንደነበር ተነግሮለታል፡፡
የፌዴራሉ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ፣ የዶናልድ ትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎችና ጽንፈኛ ቡድኖች በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተከትሎ፣ በ50 ግዛቶቿ ከፍተኛ ጥበቃና የጸጥታ ቁጥጥር ስታደርግ የሰነበተችው አሜሪካ፣ በዋሽንግተን ለጆ ባይደን በዓለ ሲመት ብቻ 25 ሺህ ወታደሮችን ያሰማራች ሲሆን፣ እንደተሰጋው ይህ ነው የሚባል እክል ሳያጋጥም በአሉ በሰላም ተጠናቅቋል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ 59ኛው በአለ ሲመት ሆኖ የተመዘገበው የጆ ባይደን በዓለ ሲመት፣ ከጸጥታ ስጋቱ ባሻገር ከወትሮው ቀዝቀዝ ያለ እንዲሆን ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ነበር፡፡
ድሮ ድሮ ስፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በአደባባይ በተገኘበት ይከናወን የነበረው የአሜሪካ በዓለ ሲመት፣ ዘንድሮ ግን እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ መላ የጠፋለትን የኮሮና መስፋፋት፣ የባሰ ላለማስፋፋት ሲባል እንደ ወትሮው ብዙ ህዝብ ባልተገኘበት መከናወኑ ግድ ሆኗል፡፡
የዛሬን አያርገውና ድሮ ድሮ በበዓለ ሲመቱ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆየሩ ሰዎች ይታደሙ እንደነበር ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ለአብነትም ባራክ ኦባማ በ2009 ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ 2 ሚሊዮን ህዝብ ዋሽንግተን ዲሲን ከዳር እስከ ዳር አጥለቅልቋት እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡
ስልጣን ላለመልቀቅ ወዲያ ወዲህ ቢሉም ከባይደን በዓለ ሲመት ከሰዓታት በፊት ለአራት አመት የኖሩበትን ነጩን ቤተ መንግስት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሰናበቱት ዘንድ ግድ የሆነባቸው ተሰናባቹ ትራምፕ በበዓለ ሲመቱ ላይ ባይገኙም፣ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ባራክ ሁሴን ኦባማ፣ ቢል ኪሊንተን እና ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ስነስርዓቱን መታደማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
1.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት በተነገረው በአለ ሲመት በ78 አመት ከ2 ወራት ዕድሜያቸው ቃለመሃላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት የገቡት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን፣ በአሜሪካ ታሪክ እድሜያቸው በጣም ከገፋ ወደ ስልጣን የመጡ ቀዳሚው ሰው ሆነው በታሪክ መዝገብ መስፈራቸውም ተነግሯል፡፡
ታዋቂዋ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ በዓለ ሲመቱን በማስመልከት የአሜሪካን ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር የዘመረች ሲሆን፣ በዋሽንግተኑ የነጻነት ሃውልት ፊትለፊት በተዘጋጀውና በዝነኛው የፊልም ተዋናይ ቶም ሃንክስ የመድረክ አጋፋሪነት በተካሄደው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይም ጄኔፈር ሎፔዝ፣ ብሩስ ስፐሪንግስተን፣ ኬቲ ፔሪ፣ ቦን ጆቪ፣ ዴሚ ሎቫቶና ፉ ፋይተርስን ጨምሮ ታዋቂ ድምጻውያን የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
የ22 አመቷ ታዳጊ አሜሪካዊት ገጣሚ አማንዳ ጎርማን በበኩሏ፤ ለባይደን በአለ ሲመት የከተበችውንና የአብሮነትና የአንድነት ጥሪ ያስተላለፈችበትን ማራኪ ግጥም ያቀረበች ሲሆን፣ በአሜሪካ በአለ ሲመት ላይ ግጥም በማቅረብ በእድሜ ትንሽዋ ገጣሚ ለመሆን ችላለች፡፡
በዓለ ሲመቱን በማስመልከት በእለቱ ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ከላኩት የተለያዩ አገራት መሪዎች መካከል፣ የታይዋን፣ የጃፓን፣ የብሪታኒያ፣ የኳታር፣ የጀርመን፣ የፓኪስታን፣ የጣሊያን፣ የቻይና፣ የኢራን፣ የካናዳ፣ የሩስያ፣ የፈረንሳይ፣ የህንድ፣ የስፔን፣ የግሪክ፣ የእስራኤል ወዘተ መሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ የሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቫንደር ሌይንም መልዕክት መላካቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2972 times
Administrator

Latest from Administrator