Saturday, 23 January 2021 17:34

… መኖር ማለት…

Written by  ፉአድ ተሾመ
Rate this item
(7 votes)


ስሜቴን እንዳጣሁ የሚሰማኝ ታክሲ   ውስጥ ተቀምጬ፣ ድሮ  የምለው  የትናንት  ያህል የራቀኝን የትዝታን ማህደር፣ በእዝነ–ልቦናዬ እየተመላለሰ፣ ሆዴን  ሲያልሞሰሙሰው  ነው። ትዝታዬን  ከተረሳ  ማህደሬ የሚጎረጉረው፣ የሚፈለፍለው፣  ድንገት እንደ መብረቅ ብልጭ ብሎ፣  ለስላሳ ዜማ ከስፒከሩ አፍ ወደ ጆሮዬ  እየተወረወረ፣  ከልቤ ሲከትም ነው። በስሜት እየናጠ፣  ዐይኔን  በሚቆጠቁጥ እንባ ሞልቶ፣  በትናትና  ዱሮዬ ላይ  እሰፍራለሁ።  ስሜቴ፤  እንዲህ  ቀዝቅዞ፣  ያረጀሁ  የሚመስለኝ  ታክሲ  ላይ  ተቀምጬ፣  ተክዤ   በትንሹ  በተከፈተው   የታክሲው  ተንሸራታች መስኮት  አልፎ፣  ፊቴን  እየዳበሰ፣ ውስጤን  ቅዝቃዜ  ሲወረው፣ በፍዘት  የምመለከተው አካባቢዬን ነው።
ስሜት የሚሰጡኝ ነገሮች፣ ዛሬ ላይ   ምንም  እንደኾነ  ‘ኖርማል  ነው’  ብዬ  በማልፈው  ነገር    ተሸብልለው፣  ተጀቡነው  ሲደበቁ፣  እየጠፉ  እንደኾኑ  ይሰማኛል።  መደነቅ፤  ከአጠገቤ  ጠፍቶ፣  ርቆ  እንደሸሸኝ   ሳስብ፣  ኑሮን   ኑሬ፣  ሮጬ  የጨረስኩ   ይመስለኛል። ቢመስለኝም፣  መኖር  በራሱ    ትርጉሙ  ምን  እንደኾነ  ለማወቅ  ግራ  የተጋባሁ  ይመስለኛል። መኖር   ግን  ምንድን  ነው?  መኖር   ይገለፃል  ወይስ  ይኖራል?  መኖርንስ  ሲኖሩ  መግለጥ  ይቻላል?  ለምን   በቀቢፀ–ተስፋ  ይሞላል?
መኖርን እያሰብኩት፣ መኖር ግን  መሰልቸትን ሲያከናንበኝ፣ ስሜቴን የትናንት፣  ዱሮዬን ናፍቃለሁ። ሁሉም  ነገሮች  ስሜትና   ትርጉም  ይሰጡኛል።  እያንዳንዷ  ድርጊቴ   በፍቅርና  በስሜት  የቅብጠትንና  የፈገግታን  ወገግታ  በኔ  ላይ  አረብቦ፣ ለአጠገቤዎቼ  ቀላል  ነበርኩ።  አሁን  ለምን  ከአዚም  ከበድኩ?  መኾኔን  የጠረጠርኩት  ነገር  ራሱ  መኾኑን   ለምን  ማመን  ለራሴ አልፈቅድለት   አልኩ?  ለምን  የገባኝን  እጠይቃለሁ?  ይሕንን  ጥያቄ  ስጠይቅ፤  “የምንጠይቀው   የማናውቀውን  ነገር  ብቻ  ሳይኾን  የምናውቀውን  ነገር  ራሱ  በትክክል  ማወቃችንን  ማረጋገጥ  ነው።”  የሚለው  ንባቤ፣  ጥያቄ  ውስጥ  ያውተፈትፈኛል።  
…  “የምናውቀው   ነገር፣  የምናውቀው  ምን  ያህል  ነው?”  የሚል  ጥያቄ  ዙሪያዬን  በሌላ  ጥያቄ  ይወጥረኛል።  የማውቀውን  ነገር በትክክል  አውቄ ማረጋገጥ  እንደምፈራ፣  በምን  ቃል  እንደማብራራ ይጨንቀኛል።  ማወቅ ግን ከመጠበቅ በምንድን ነው  የሚለየው? ማወቅ ግን የሕይወትን  ጣዕም  ለማጣጣም  የሚያመክን   ማርከሻ  መድሐኒት  የሚመስለኝ  ለምንድን  ነው?  የመገረምን፣ የመደነቅን  ቅፅበተ–ጊዜ  የሚቀማን  ማወቅ  አይደለምን?  ተፈጥሮ   እየራቃት፣  ቁሳቁስ   በሚሞላት  ከተማ፣  ማወቅ  ምንድን  ነው?
መጠየቅም  ያሰለቻል።  መሰልቸት፤  የሕይወትን  ወለፈንድነት  አያከናንብም!?  ዘበትነት፤ በመኖር  ርዝመት   ከመጠበቅ  ያርቃል።  መጠበቅ  ላይ የታሰረች  የመደነቅ  ገመድ፣  በማወቅ  ስለት  ተገዝግዛ፣ ሳስታ፣ ስትበጠስ  ማየት፣ ውስጤን አድክሞታል።
መጠበቅ፤  በአውቃለሁ  እና  በመልካም  አፍ  ተከብባ፣  በድርጊት  እና  ጊዜ  ላይ  ቀላ  ስትገኝ፣  ድክመቴ  ያኔ  ተጀመረ።  ይህ  ሁሉ  እህህታ  በመጠበቄ  ተፀነሰ።  ዛሬ፤  ከጎኔ  እያለች፣  ከደረቴ  ተንተርሳ፣  ከውስጤ እርቃለች። ሩቅ ከተማ   እያለች ያደመጥኳቸው ሙዚቃዎች፣ እነዚያ ያልተገናኘንባቸው የትምህርት ቤት   ጊዜያት፣ ለምንገናኝባቸው ቀናት፣  የናፍቆት መሰረቶች፣ የሐሳብ መመላለሶች፣ ዛሬ ታክሲ  ላይ ቁጭ  ብዬ  በትውስታ  ሲነቀንቁኝ፣ አሁን  ያለሁበት የስሜት  ደረጃ  በሚቆጠቁጥ  እንባ፣  የዕይታዬን  መልክ  ያደበዝዘዋል።
መጠየቅ፤  ለምን  ጠላሁ? ማወቅ፤  ማረጋገጥ  ለምን  ጠላሁ?  ከአካሏስ  ለምን  መራቅን   ፈራሁ?  እሷ፤  መሳሳቷ  ቢገባት  ለምን  የተሰበረውን  ስሜቴን  መጠገን  አቃተው?  ይቅርታ፤  ለምን  የተሰበረን    ስሜት  መጠገን  ተሳነው?  ለይቅርታ  ያለኝ  አመለካከት  በዚያው   አክትሞ  ለምን  ቀረ?  ከይቅርታ    በፊት   መጠንቀቅ  እንጂ፤  ከዚያ  ወዲያ  ይቅርታ፣ ስሜትን  ለመጠገን  አቅም  እንደሚያንሰው፣ የይቅርታ  ጠንሳሽ   ቀድሞ  ለምን  አልተረዳም?  ለይቅርታ፤  የለሰለሰ  ልብ  ለምን  አጣሁ? ይህን  የፈጠረው  እኔ  ነኝ፣  ብላ  በእሷ‘ነቷ  ስትሰራኝ፣  ለምን  ከመልካም  አፏ  ጀርባ  ያለውን  የስሜት ስብራት፣  ያኔ  ማሰብ  አቃተኝ?
… ዛሬ፡  መኖር፡  ስትጀምር፡  ከኔ፡  የአፌን፡  ይቅርታ ፡  ተቀብላ  …  ለይቅርታ፡  ምሕረትን፡  ወስዳ  …  ያ…መልካም፡  አፏን፡  ስትኖረው፡  እውነት፡  አልመስልህ፡  እያለኝ፡  መኖርን፡   ሲከብደኝ፡  ውስጤ፡  እየተከፋ፡  በደሌን፡  ባልተረዳችው፡  በቀል፡  መኖር፡  እኔን፡    ስልቹ፡  አደረገኝ።  ሳቄ፡  በውሸት፡  ተሸብልሎ፡  አፌ፡  ላይ፡  ሲንከረፈፍ፡  እያየች፡  ጊዜን፡  ለመልካም፡  ቀን፡  ስትቀጥር፡  ሳይ፡  ፅናቷ፡  ከኔ፡  ሲበልጥ፡  ይብስ፡  እብሰከሰካለሁ።  
የቀረበችኝ፡  በመሰለኝ፡  እነዚያን፡ አስርት፡  አመታት፡  ከጉርምስናዬ፡  ጊዜ፡የጠነሰስኩት፡  ቀረቤታዋ፡  እንዳልቀረበችኝ፡  መረዳቴን፡  የጊዜው፡  ርዝመት፡  እድሜዬን፡  እንደፈጀችው፡  ማሰብ፡  ማቆም፡ አልቻልኩም።  እንዳልነበረች፡  ያ……ን፡  ሁሉ፡  ዓመት፡  ሳስብ፡  እንባዬ፡  ይመጣል።  ከዚያ፡  ሁሉ፡  ዕድሜ፡  በኋላ፡  ባሕርይዋን፡  ተላብሼ፡  ማንነታችንን፡  ተቀያይረን፡  የቀረብኳት፡  መስሏት፡  ቀርባኝ፡  ስትኖር፡  የኔን፡  ስሜት፡  የሷ፡  እጣ፡  እንዳይኾን፡  እሰጋለሁ፤  እፈራለሁ።  ፍራቻዬን፡  ከስጋቴ፡  አውጥቼ፡  መኖር፡  እንደከበደኝ፡  በምን፡ ቃል፡  ገልጨው፡  በምን፡  ድርጊት፡  ከውኜው፡  በወጣልኝ፡  እላለሁ።  ድርጊቴ፡ መልካም፡  ኾኖ፡  ለሷ፡  እየተጠነቀቅኩ፡  እኔ፡  እሷ፡  ውስጥ፡  ምንም፡  እንደኾንኩ፡ ያሰብኩ፡  ከሷ፡  መራቄን፡  ባሰብኩ፡  ቁጥር፡  እደክማለሁ።  መንፈሴ፡  ተልፈስፍሶ፡  የሷን፡  እዝነት፡  ማየት፡  ነፍሴን፡  ያቀጭጨዋል።  
በመኖር፡  ያልተፈተኑ፡  የዘመኔን፡  ሙዚቃዎች፡  እየሰማሁ፡ ብስጭቴን፡ አንራለሁ።  የመኖር፡  ሕልውና፡ ሰፈረባቸው፡  ተስፋ፡  የተሰገሰገባቸው፡  ቀለም፡  ያስዋባቸው፡  አልባሳት፡  ያሸበረቀባቸው፡  ኾነው፡  እንደቀሩ፡  ሳስብ፡  እበሽቃለሁ። መኖር፡  የላቸውም።  ተስፋ፡  ብቻ።  ተስፋ፡  ሕይወት፡  የሚኾነው፡  ተስፋ፡  እስከቆረጡ፡  ድረስ፡  ነው፡  ማለት፡  ያስደፍረኛል።  የተስፋን፡  ሕመም፡  የሚያውቁት፡  ተስፋን፡  ሲቆርጡ፡  ነው።  ተስፋና፡  ምኞት፡  እንደተቀላቀለባቸው፡  መረዳት፡  ብዙ፡  ረቂቅነት፡  አይጠይቅም።  
በነዚህ፡  ሙዚቃዎች፡  ስትወዛወዝ፡  ሳያት፡  ከአስር፡  አመት፡  በፊት፡  እኔን፡  እየመሰለችኝ።  ለቀጣዩ፡  ጊዜያት፡  እኔ፡  ላለሁበት፡  ስሜት፡  የቀጠርኳት፡  ይመስለኛል።  ቦታ፡  የነፈገቻቸው፡  እኔነቶቼን፡  ለእሷ፡  እኔነት፡  ቦታ፡  እያሳጣኋት፡  መኾኗን፡  አለማወቋ፡  ያሳዝነኛል።
ታሳዝነኛለች።
ለራሴ፡  አዝናለሁ።
… ስሜያት፡  የመሳም፡  ስሜት፡  ውስጤ፡  ምንም፡  ትዝታ፡  ምንም፡  ስሜት፡  አልፈጥር፡  ሲል፡  ሌላ፡  ዓለም፡  እፈጥራለሁ።  የታችኛው፡  ወፍራም፡  ከንፈሯን፡  ከከንፈሬ፡  አንተርሼ፡  በአንገቷ፡  የሚንሸራተቱትን፡  እጆቼን፡  የሰውነቷን፡  ልስላሴ፡  እየሰለልኩ፡  ከጀርባዋ፡  ላይ፡  እያንሸራተትኩ፡  መቀመጫዋን፡  እየዳበስኩ፡  ጭምቅ፡  እያደረኩ፡  አንገቷን፡  ጡቶቿን፡  የጡቶቿን፡  ጫፍ፡  በስሜቷ፡  ውጥረት፡  እየተሳፈርኩ፡  የጭኗን፡  እርጥብ፡  ሞቃታማ፡  አካሏን፡  በአካሌ፡  እየፈለኩ፡  ብዙ፡  ማለክለክን፡  ከስሜት፡  ሲቃ፡  ጋር፡  ደርሼ፡  ከሽንፈት፡  እኔነቴ፡  ጋር፡  አርፋለሁ።  እሷ፡  ከደረቴ፡  እርጥብ፡  የቀዘቀዘ፡  ከንፈሯን፡  በአንገቴ፡  ስታዳርስ፡  የተሽለመለመ፡  እፍረቴን፡  ይዤ፡  ያልረጋ፡  ፈገግታዬን፡  ለግሳታለሁ።  በፈገግታዬ፡  ስር፡  እርካሽነቴ፡  እያስተጋባ፡  የስሜቴን፡  ክሽፈት፡  በፍርሃት፡  አጥብቄ፡  እንዳቅፋት፡  ያደርገኛል።
…መጨረሻ፡  የሚባለውን፡  የቃል፡  መዳረሻ፡  ለማሰብ፡  ብዙ፡  ጊዜ፡  ለማሰብ፡  ሸሽቻለሁ።  እሷ፡  የእኔን፡  ደስታ፡  በመመለስ፡  እሷ፡  እኔ፡  ከጎኔ፡  በመኾኔ፡  ብቻ፡  የምትደሰት፡  መኾኗ፡  ለእሷ፡  ደስታ፡  ከጎኗ፡  መኾኔን፡  ብቻ፡  አስባለሁ።  ከጎኗ፡  መኾኔ፡  ለእሷ፡  ደስታ፣  ደስተኛ፡  ቢያደርጋትም፡  እኔ፡  እየበደልኳት፡  እንደኾነ፡  እያወቅኩ፡  መኖር፡  ስልቹ፡  እና፡  የሕይወትን፡  ወለፈንዴነት፡  እየኖርኩ፡  መኾኑን፡  ስታውቅ፡  ራሷን፡  እንደምታጠፋ፡  እያወቅኩ፡  ሳትረዳው፡  ሳላስበው፡  መኖርን፡  ለመለማመድ፡  ማሰብ፡  እንዳለብኝ፡  አስባለሁ።
እያሰብኩ፡  በራሴ፡  ደስታ፣  በራሴ፡  ፈንጠዝያ፡  ለመጣሁባት፡  የምድር፡  ሕይወት፡  በዚህ፡  መንገድ፡  ማለፉ፡  ያስተክዘኛል።  የሕይወት፡  ትምህርት፡  ግን አስቀያሚ፡  ነው።  የምድር፡  የሕይወት፡  ደርዝ፡  ላይ፡  እንዳዲስ፡  መፈጠርን፡  እንደማለም፡  ምን፡  መምከን፡  አለ?  ከማለምና፡  ከምኞት፡  ያለፈ፡  አንዲት፡  ትርጉም፡  ያለው፡  ሕይወት፡  ግን፡  ናፍቃለሁ።
እንዲህ፡  እያልኩ፡  ከትካዜዬ፡  ነቅቼ፡  ከታክሲውም፡  እወርዳለሁ።
መኖር፡  ማለት…
እነሱ…
“ብዙ፡  ያሳየናል፡  መኖር፡  ደግ   ነገር!”
እኔ…
ብሒሉን፡  ሰምቼ
መኖር፡  ደግ፡  ነገር፡  መኖር ፡  መደናገር ፣
እየኖሩ፡  መሞት፡  መኖር፡  ማለት፡  ነበር።   … ]



Read 3686 times