Print this page
Saturday, 30 January 2021 10:53

“አንተም እሳት ነበርክ እሳት አዘዘብህ እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     የሚከተለው ታሪክ እውነተኛ ታሪክ ነው። ሆኖም እኛ እንደ ተረት እንጠቀምበታለን። ስምም የማንጠቅሰው ለዚህ ስንል ነው።
ከዕለታት አንድ ቀን በሀገራችን ላይ የአብዮት ንፋስ እየበረታ መጣ። የመንግስት አጋር ነን ብለው ከአውሮፓ የመጡ ሰዎች ነበሩ።
ሰዎቹ አገር ውስጥ ያሉ ወዳጆች ነበሯቸው! ስለዚህ ወዳጆች በኢትዮጵያውያን ጓደኞቻቸው ግብዣ አብረው በመተሳሰብ ይኖራሉ። አንድ ቀን ሌሎቹ በሌሉበት ሰዓት ከእነዚህ ወንድማማቾች አንደኛው ሌሎቹ መኝታ ቤት በር ላይ፡-
“ባንዳዎች ይወድማሉ!” ብሎ ፅፎ ወደ ቤቱ ይመለሳል። ጓዶቹ ሲመለከቱ የሚገቡበት ጠፋላቸው። መደበቂያ አጥተው በፍርሃት እራዱ።
የት ይሂዱ ? ይወድማሉ እየተባሉ እዚህ ቤት ማደር መቼም አይሞከርም።
አንደኛው፡-
“እኔ ከከተማው አንድ አክስት አለችኝ። ለምን እሷ ዘንድ ለጥቂት ቀናት አንሸሸግም?”
ሁለተኛው፡-
“እሱማ አያዋጣንም።”
“ለምን?”
“ዞሮ ዞሮ እንፈልጋቸው ካሉ የመጀመሪያ ሙከራቸው በየዘመዱ ቤት መሄድ ነው።”
“ስለዚህ ምን እናድርግ? የት እንሸሸግ?”
“እዚያ ወዳጃችን ቤት እንሂድ፤ እሱ ታማኝ ሰዋችን ነው።” ተባብለው  ወደሱ ቤት ሄደው አደሩ።
ወዳጃቸውም ሲስቅባቸው አደረ!
*   *   *
የመጨረሻው ጠንካራ ምሽግ የጠላት የራሱ ቤት ነው  ይባላል። ምነው ቢሉ? ጠላት የራሱን ቤት አይፈትሽምና። ያም ሆኖ የተነቃ እንደሆን ግን መዘዙ አያድርስ ነው!
ዞሮ ዞሮ ግን የቤትም ይሁን የጎረቤት ጠላትን መለየት ቀዳሚ ተግባር ነው። ዛሬም ይሁን ጥንት ጠላት ጠላት ነው። ነቅቶ መጠበቅ ያባት ነው! ትላንት ተጣልተን የታረቅናት ሱዳን፤ በአይዞሽ ባዮችዋ ታጅባ ዛሬ ዘራፍ ልትል ብትሞክር፣ ዳግመኛ የሐፍረት ሸማ ብትከናነብ፣ ጉዳቱ ለራሷ ነው… ለእኛማ ዕዳው ገብስ ነው! ሆኖም አፍሪካ በሰላም ውላ ትገባ ዘንድ ሰላምና ዴሞክራሲ ቢረጋገጥ፣ ለሁላችንም በጎ ነው! በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል የሚለውን የአበው አባባል አለመዘንጋት ነው! አንድም በዲሞክራሲ፣ ሁለትም በዲፕሎማሲ ካልተጓዝን ዳር የመድረስ ዕድላችን  ጠባብ ነው!
ከመርገምት ሁሉ የከፋ መርገምት ፣ ከትላንት አለመማር ነው!
ደራሲ ከበደ ሚካኤል፡-
“… ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አእምሮ
 እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋል።
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ!”
ለማንኛውም ጊዜ፤
“በሬ ሆይ
ሞኙ በሬ ሆይ!
ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ
ገደል ገባህ ወይ!”…
የሚለውን ብሂል ምንጊዜም አለመዘንጋት ነው… የምንለውም ለዚሁ ነው።
እግረ-መንገዳችንን ግን የሰሞኑን ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት፡-
“አንተም እሳት ነበርክ እሳት አዘዘብህ
እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ!” …ከማለት ወደ ኋላ አንልም።

Read 14430 times
Administrator

Latest from Administrator