Saturday, 30 January 2021 11:00

በሱዳን ወታደሮች የተዘረፉ ባለሃብት አርሶ አደሮች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

“አሁን ሁሉም ነገር ጨላልሞብናል”
የሱዳን ወታደሮች በሉግዲ፣ ማቻችና ረደም አካባቢ ድንበር አልፈው ወረራ ከፈፀሙ ሁለተኛ ወራቸው ተቆጥሯል፡፡ የአካባቢው ባለሃብት አርሶ አደር ባለሃብትም በዝምታና በትዕግስት እስከ ዛሬ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን አዝማሚያው ችግሩ በቀላሉ የሚፈታ አይመስልም የሚሉት ባለሃብቶቹ፤ የሆነውን የተፈፀመውንና የደረሰብንን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ይወቅልን ብለዋል፡፡
እነዚህ 16 የሚሆኑ አርሶ አደሮች ሰሞኑን በተወካዮቻቸው አማካይነት ለፌደራል የመንግስት አካላት አቤቱታቸውን  አቅርበዋል፡፡ ባለሀብት አርሶ አደሮቹ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት ተወካያቸውን አቶ ጌታቸው ማዋን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

             የሱዳን ወታደሮች ድንበር አልፈው መውረራቸው በሰፊው ሲነገር ቆይቷል፡፡ እስቲ በአካባቢው ስለሆነውና ስለተፈጠረው ጉዳይ ይንገሩን?
እኛ ለረጅም ዘመናት ከልጅ ልጅ ሲወራረስ በመጣው አኗኗራችን፣ ከጎረቤት ሱዳን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነው የነበረን። እኔ እንኳን ከአባቴ ተቀብዬ ወደ እርሻ ሥራ የገባሁት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ  ነው። ቦታው ሉግዲ ይባላል፡፡ ለምና ለእርሻ ተስማሚ ነው፡፡ ድንበር እንደመሆኑ ቀደም ሲል የኛ መከላከያ ሰራዊት በቦታው ላይ ነበር፤ በትግራይ የህግ ማስከበር ሂደት ሲጀምር ግን ወደ ተልዕኮው ተንቀሳቀሰ። በወቅቱ እኛ ምንም ይፈጠራል የሚል ስጋት አልነበረንም፡፡ ምክንያቱም ሱዳንና እኛ ለብዙ ዓመታት ጥሩ ግንኙነት ነበረን። ከ1987 ጀምሮ ላለፉት 26 ዓመታት እኔ በአካባቢው ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዴም ግጭት አልተፈጠረም፡፡ እንደውም እኛ ወደ እነሱ የእርሻ ቦታ ገብተን፣ በገንዘባችን መሬት በኮንትራት ወስደን ስናርስ ነበር፡፡ በስርአቱ በውል ነበር ከነሱ ላይ ተጨማሪ መሬት ኮንትራት ወስደን ስናርስ የነበረው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ ምንም ባልጠበቅነውና  ባላሰብነው አጋጣሚ፣ ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8፡30 በፓትሮል፣ዲሽቃ ታጥቀው ካምፓችን ድረስ በመምጣት፣ ንብረታችንንና ሁሉንም ነገር በሃይል የዘረፉን፡፡ ከእኔ ላይ እንኳን ከ6 መቶ በላይ በጎች፣ ትራክተሮች፣ ማረሻ፣ ቦቴዎች፣ ወፍጮ፣ የመብራት ጄኔሬተር፣ ወደ ታች 124 ሜትር ጥልቀት ያለው የውሃ ጉድጓድ ማውጫ የነበረ ጄኔሬተር፣ የውሃ ታንከሮች … ምንም የቀራቸው ነገር የለም፤ ዘርፈውኛል፡፡ ይሄ በኔ ብቻ የደረሰ ነው፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ንብረታቸው አንድም ሳይቀር ነው የተዘረፉት፡፡ በተለይ እንስሳት በርካታ ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡
በአጠቃላይ የተዘረፈው ምን ያህል ነው?
የእኔ ሁለት ትራክተሮች፣ ሁለት ማረሻ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር ወስጄ የገዛሁት የመስመር መዝሪያ ማሽን፣ ትላልቅ የነዳጅ ቦቴዎች ነበሩኝ፡፡ የፀረ አረም መርጫ ማሽን፣ ወፍጮ፤ በጎች፣ የዶሮ እርባታ -- ነበረኝ፤ እነሱንም ወስደውብኛል፡፡ በገንዘብ ሲሰላ  ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል። ይሄ የኔ ብቻ ነው፡፡ ከእኔ በተጨማሪ መዝግበን ከያዝናቸው የሌሎች ባለሃብቶች ንብረት መካከል የአቶ አብርሃም አለማየሁ 16 ሚሊዮን ብር፣ የአቶ ባህታይ ውብነህ ከ4.5 ሚሊዮን ብር  በላይ፣ የማማይ ግሩም ፋርም 25 ሚሊዮን ብር፣ የአቶ ካሳ መብራቴ 8 ሚሊዮን ብር፣የአቶ መለሰ ረዳ 39 ሚሊዮን ብር፣ የአቶ ታደሰ ለውጤ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ በላይ ሃየሎም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ ኡመር ሳልህ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የወ/ሮ በረይ ህሩይ ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ አዳምጠው ሰረበ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ ጠአም ሃይሉ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ መሪያው መኮንን ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ፣ የአቶ ኢብራሂም አህመድ 8 ሚሊዮን ብር፣  የአቶ መሃመድ ብርሃን አህመድ ከ3.7 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ንብረት ሲዘረፉ፤ የኔ ድርጅት አራት የጉልበት ሰራተኞች ደግሞ የወር ደመወዛቸውን በድምሩ 89 ሺ 620 ብር ከኪሳቸው ተዘርፈዋል። በአጠቃላይ በሱዳን ወታደሮች ወረራና ጥቃት ከ226 ሚሊዮን 940 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረታችንን አጥተናል፡፡
የእርስዎ የእርሻ ቦታ ምን ያህል ስፋት ነበረው?
የኔ 320 ሄክታር መሬት ነው፡፡ እርሻው ሙሉ ለሙሉ ሜካናይዝድ ነው፡፡
ምን ነበር የሚያመርቱት?
እኔ ለምሳሌ ዘንድሮ የዘራሁት ጥጥ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ ናቸው፡፡ አካባቢውም ለዚህ የተመቸ ነው፡፡ አነዚህ ሁሉ ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች ነበሩ፡፡ ሁመራ የሚታወቀው በሰሊጥ ነው፡፡
አካባቢው በትክክል ምን ተብሎ ነው የሚጠራው?
እኔ እዚህ ላይ እንደውም የኛ መገናኛ ብዙኃን ቢያርሙት መልካም ነው እላለሁ። ሱዳኖች ቦታውን  በሚጠሩበት አልፋሽቃ ብለው ሲጠሩ እሰማለሁ፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ እኛ ነዋሪዎቹ ቦታውን ሉግዲ፣ረድም መቻች ብለን ነው የምንጠራቸው፡፡ የኛ መገናኛ ብዙኃን ይሄን  ቢያርሙ ጥሩ ነው። ሱዳኖች ቦታውን በሚጠሩበት ሲጠሩት ስንሰማ ቅሬታ ይሰማናል፡፡  
ስለ ቦታው ታሪክ በጥቂቱ ቢነግሩን?  
እኔ ገና በ11 አመቴ ነበር ወደ ሱዳን የወጣሁት፡፡  ነገር ግን ያ ቦታ  በኛ ወላጆች ይታረስና ይተዳደር የነበረ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ አያት ቅድመ አያቶቻችን ሲያርሱት  የነበረ መሬት ነው፡፡ እኔ እንኳ ሱዳን ውስጥ በስደት 20 አመት ገደማ ቆይቼ ስመለስ ነው፣ እርሻውን ከአባቴ ተቀብዬ ዘመናዊ አድርጌ ማረስ የጀመርኩት፡፡ ሱዳኖች መሬታችን መሆኑን በሚገባ ያውቁታል፡፡ መሬቱ ድሮም የኛ ነው፤ አሁንም የኛ ነው፤ የአባቶቻችን፣ የአያቶቻችን ነው፡፡
እርስዎ ወረራው ድንገተኛ መሆኑን ነግረውናል…የሱዳን መንግስት ደግሞ ሚሊሻዎች ትንኮሳ ፈጽመውብናል፤ ለዚህ ነው እርምጃ የወሰድነው ሲሉ ይሰማል……
እንደዚህ አይነት ነገር በጭራሽ አልነበረም፡፡ እኛ እኮ ምንም ባልገመትነው ሁኔታ ነው ጥቃት የተፈፀመብን፡፡ ብንገምትማ ቢያንስ ንብረታችንን አናሸሽም ነበር እንዴ? በኔ የእርሻ ካምፕ ውስጥ የመዝናኛ ክበብ አለን፡፡ የሱዳን ወታደሮች እኮ ሲቪል ለብሰው በዚያ ክበብ ውስጥ ሲጠጡ ሲዝናኑ ነው የሚውሉት፡፡ ፍጹም ሰላማዊ ነበር ግንኙነታችን፡፡ ባለስልጣናት ራሳቸው መጥተው ይዝናኑ ነበር፡፡ ሲቪሎች ሱዳናውያንም ወታደሮችም መጥተው ከኛ ጋር ይዝናኑ ነበር፡፡ ግንኙነታችን በሙሉ መልካም ነበር፡፡ ወረራው ከተፈፀመ በኋላም እኔ ራሴ ለሱዳን ባለስልጣናት ደውዬ ነበር። “ምንም ችግር የለም፤ ይስተካከላል”  ሲሉኝ ነው የነበረው፡፡ የአካባቢው የሱዳን ወታደሮች አዛዥ የነበረው ግን ስደውልለት “ኧረ እኔ አልሰማሁም፤ ሌሎች ሃይሎች ይሆናሉ እንጂ ከኛ የተንቀሳቀሰ ሃይል የለም” ነበር ያለኝ፡፡ በእርግጥም የእነሱ ሃይል አልነበረም ወረራውን የፈፀመው፤ አዲስ የተሰማራ ጦር ነበር፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ፣ልዩ ሀይል ወይም ሚሊሻ በአካባቢው አልነበረም?
ከአሁን በፊት በመከላከያ ነበር የሚጠበቀው፤ ድንበሩ፡፡ ሉግዲ ላይ ካምፕ አለው፡፡ ነገር ግን  መከላከያ በትግራይ የሕግ ማስከበር ተግባር ላይ ሲሰማራ ነው፣ ሱዳኖች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ቦታው የገቡት፡፡
ወረራው በተፈፀመ ወቅት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ነበር? እርስዎ ምን ያህል ሰራተኞች ነበርዎት?
በወቅቱ እኔ ጎንደር ነው የነበርኩት። ማይካድራ በመከላከያ እንደተያዘ ነው እኔ ወደ ማይካድራ የሄድኩት፡፡ በወቅቱ ከውጊያ የሚሸሹ ሰዎች ወደ ሱዳን ይጓዙ የነበረው በዚያ መስመር ነበር፡፡ ስለዚህ እነሱ ይሄን ንብረት ይዘርፉብናል ይሆን የሚል ስጋት እንጂ ከሱዳን ወታደሮች እንዲህ ያለ ጥቃት ያጋጥመናል ብለን አላሰብንም ነበር። ሰራተኞችን በተመለከተ 20 ቋሚና እስከ 200 የሚደርሱ  ጊዜያዊ ሠራተኞች ነበሩኝ፡፡ በህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ብዙም የለም፡፡ አንድ የበጎች እረኛ ግን ወስደውብናል፡፡
ወታደሮቹ ቦታው ላይ  እንደደረሱ ምን ነበር ያደረጉት?
ሰራተኞቹን ሰበሰቡና አንድ ክፍል ውስጥ አጎሯቸው፡፡ ይሄን አድርገው ያገኙትን ንብረት ሁሉ ወደ መዝረፍና መውሰድ ነው የገቡት፡፡ በጎቹን ከእነ እረኛው አብረው እየነዱ ወሰዱ፡፡ ሌሎችንም በተመሳሳይ ያለ ምንም ከልካይ ነበር የወሰዱት፡፡ በወቅቱ እኔ ማይካድራ ላሉ የፀጥታ ሃይሎች ስለ ሁኔታው ተናግሬ ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታው ከአቅም በላይ ነው መሰለኝ ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም፡፡ 70 ኩንታል ማሽላ፣ 25 ኩንታል ሰሊጥ… እነዚህን ሁሉ ነው የወሰዱት፡፡ የቤቶችን በር፣ የሻወር እቃዎች ሳይቀር ነው እየነቀሉ የወሰዱት፡፡
ምርት ሰብስባችሁ ነበር?
ገና ምንም አልሰበሰብንም፡፡ የጥጥ የሰሊጥ ምርት አልተሰበሰበም፡፡ ያውም በብድር የተሰራ ነበር፡፡ የባንኩም የራሴም ነው የጠፋው፡፡ ለ26 ዓመት የለፋሁበትን ንብረት ነው በደቂቃዎች ያወደሙብኝ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ምርቱ ጥሩ ነበር፡፡ የኛ ብቻ ሳይሆን አርማጭሆ ሉግዲ  ሌሎች ቦታዎችም አዝመራው ጥሩ ነበር፤ ግን እንዳለ ዘረፉት፡፡ ሱዳኖች የራሳቸውን ኮምባይነር አምጥተው ነው ያጨዱት፡፡ እየወቁ ወዲያውኑ ወደ ኬሻ እየተሞላ ነው የሰበሰቡት፡፡  የኔ እርሻ ቦታ ላይ እንኳ ወዲያውኑ ሶስት ኮምባይነሮች ነበሩ የገቡት፡፡
እርስዎ ሌላ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የለዎትም?
እኔ ስራዬም ኑሮዬም ግብርና ነው፤ ሌላ ቦታ የለኝም፡፡ ጎንደር ላይ ሆቴል ግንባታ ጀምሬ ነበር፡፡ ከዚህ በማገኘው ነበር የምሰራው፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ጨልሞብኛል፡፡ የባንክ እዳ እንኳን ሳንከፍል ነው ይሄ ችግር የገጠመን፡፡ ለ26 ዓመት ከተራ እርሻ ጀምሮ ነው ወደ መካናይዝድ የገባነው፡፡ እኔ አሁን ምን እንደማደርግ አላውቅም፡፡ በአንድ በኩል የባንክ እዳ አለብን፡፡ እጃችን ላይ ምንም ትርፍ ገንዘብ የለም፤ ብቻ ብዙ ነገር ጨላልሞብናል፡፡ መንግስት የሚደጉመን ከሆነም ሌላ የእርሻ ቦታ የሚይቀየርልን ከሆነም በተስፋ ነው የምንጠብቀው፡፡ ሁሉንም የምንጠብቀው ከመንግስት ነው፡፡ የባንኮች እዳ አለብን፡፡ ይሄ እዳ እንዲራዘምልን እንፈልጋለን፡፡ ሁለተኛ መንግስት ድጎማ አድርጎልን ስራችንን እንድንቀጥል ያግዘን ዘንድ እንጠይቃለን። ሶስተኛ ያ ቦታ እስኪመለስ ድረስ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ቢያንስ የቦታ ቅያሬ ተደርጎልን፣ ስራችንን እንድንጀምር ሁኔታዎች እንዲመቻቹልን እንጠይቃለን፡፡ ቢቻል ነገሮች በሰላም ቢፈቱና ወደ ቦታችን ብንመለስ እንመርጣለን፡፡ ይሄ የሉአላዊነት መደፈር ነው፡፡ መንግስት በቀላሉ ያየዋል የሚል ግምት የለንም፡፡ ግን መጀመሪያ በሰላም እንዲያልቅ፣ የሰላሙን ሁኔታ አሟጦ እንዲጠቀም ነው የምንጠይቀው፡፡
በየጊዜው የሱዳን ወታደሮች ድንበር አልፈው ይገቡ ነበር ይባላል--?
ይሄ በእኛ አካባቢ ብዙም አልነበረም። ከክልል 3 ወይም አማራ ክልል ጋር በሚዋሰነው የደሎሎ አካባቢ ነበር፡፡ በአብድራፊ በአብርሀጅራ እንዲህ ያለ ችግር ነበር፡፡ ይሄን ችግር ደግሞ የሚፈጥረው አቶ አባይ ፀሀዬ ነበር፡፡ ሆን ብሎ ወንዝ ተሻግሮ ከሱዳን መሬት፣ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ሁልጊዜ ጦርነት ይቀሰቀሳል፡፡  
በእናንተ በኩል እንዴት እስከ ዛሬ ሰላም ሊሆን ቻለ?
በ1991 ይሁን 92 በትክክል አላስታውሰውም፤ በወቅቱ የተወሰንን ሰዎች ተጠርተን የድንበር ማካለል ይካሄዳል ተባልን፡፡ ቀደም ተብሎ ለኛ “ቦታችሁን እንዳትለቁ፤ ስንዝር መሬት እንዳትተው” ተብለን ነበር፡፡ በትክክል አመላክቱ ተባልን፡፡ አልፋችሁ ግን ወደ ሱዳን እንዳትገቡ የሚል መመሪያ ተሰጠን፡፡
ይህ የነሱ ነው ተባልን፡፡ በወቅቱ ከውጭ ሃገራት ሳይቀር ባለሙያዎች መጥተው ችካል ባይቸክሉም፣ በጂፒኤስ የማካለል ስራ ተሰራ፡፡ ቦታዎቹ ላይ ችካል ባይኖርም፣ የሁለቱም ሃገር ጋዜጠኞች፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የመከላከያ አባላት በተገኙበት ፅሁፍ እየተለጠፈ፣ ከሳተላይት ጋር በማገናኘት፣ በጂፒኤስ የማካለል ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ የተነሳ በኛ አካባቢ ምንም ችግር አልነበረም፡፡

Read 2826 times