Saturday, 06 February 2021 12:16

“በኛ ላይ እምነት ይኑራችሁ” - ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ለተሰባሰቡ ጥያቄዎች በዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል።
በአጠቃላይ ከ1200 በላይ ጥያቄዎች እንደቀረበላቸው የጠቆሙት ወ/ት ብርቱካን፤ አንደኛው ጥያቄ፡- የድሬድዋና አዲስ አበባ  የምርጫ ቀን ከሌላው የተለየበት ቀንን የተመለከተ ሲሆን ቀኑ የተለያየው በተለየ ፖለቲካዊ ምክንያት አይደለም። ቀኑ የተለየው የሁለቱ ከተሞች የምርጫ ወረዳዎች ከዋናው ምርጫ ጋር ለማስፈፀም አመቺ ባለመሆኑ ብቻ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሰብሳቢዋ የፀጥታ መድረክ ባለባቸው ቦታዎች ስለሚኖር የምርጫ ሁኔታ፣ ፅ/ቤት ተዘግቶብናል የሚሉ ፓርቲዎች አቤቱታ፣ ስለምርጫው ቅድመ ዝግጅት ለ1 ሰዓት ከ16 ደቂቃ በቆየው የፌስ ቡክ ማብራሪያቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
በፀጥታ ምክንያት አስቀድሞ በትግራይ ምርጫ እንደማይደረግ መረጋገጡን ያስታወሱት ወ/ት ብርቱካን፤ በሌሎች የከፋ የፀጥታ መደፍረስ ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫ እንደማይደረግና ቅድሚያ ለዜጎች ደህንነት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ኦፌኮ እና ኦነግ በኦሮሚያ ጽ/ቤቶቻቸው ስለመዘጋታቸው በተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረባቸውን ነገር ግን ክልሉ ሲጠየቅ የዘጋው ፅ/ቤት አለመኖሩን ምላሽ እንደሚሰጥና ፓርቲዎቹ የት አካባቢ ምላሽ አለመስጠታቸውን አስገንዝበዋል።
ከፖለቲከኞች እስር ጋር በተያያዘ ለቀረበላቸው ጥያቄም  ጽ/ቤቶቻቸው የተዘጉባቸውን አካባቢዎች አድራሻ እንዲሰጡ ተጠይቀው ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት አለማሳየታቸውን አስረድተዋል። ወ/ት ብርቱካን ደግሞ፤ በህግ በተያዘ ጉዳይ ቦርዱ ጣልቃ ገብቶ መፍትሄ መስጠት እንደማይችል ሰብሳቢዋ አስገንዝበዋል።
ቦርዱ ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶች በገለልተኛነት ለማገልገል የሚያስችለውን ቁመና መላበሱን የገለፁት ወ/ት ብርቱካን፤ ተጨባጭ ማስረጃ ለቀረቡባቸው አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ መሆኑንም አውስተዋል።
ምርጫ ቦርድ ላይ ህብረተሰቡ እምነት እንዲኖረው የጠየቁት ወ/ት ብርቱካን፤ “በኛ ላይ እምነት ያጣችሁ ለምን እንዳጣችሁ ብናውቅ ጥሩ ነው” ብለዋል።

Read 12257 times