Saturday, 06 February 2021 12:24

ኢዜማ ለምርጫው ከ140 ሚ. ብር በላይ በጀት መድቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

  ዋና ፅ/ቤቱን በ5 ሚሊዮን ብር አዘምኖታል በመላ አገሪቱ ከ228 በላይ ቅርንጫፎች ከፍቷል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ያካሂዳልእውን

           በዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ የሚያደርገውን ስልቶች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የሚገልጸው ኢዜማ፤ ለምርጫው ማስኬጃ የሚውል ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የመደበ ሲሆን ለዚህም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
የምርጫ ዘመቻውንም በብሔራዊ፣ በክልልና በወረዳ ደረጃ በሶስት ክፍል ከፍሎ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ያስታወቀው ኢዜማ፤ እስካሁንም በ406 የምርጫ ወረዳዎች ላይ እጩዎቹን መርጦ ማዘጋጀቱን ጠቁሟል። በቀጣይም የፀጥታ ችግር የሌለባቸው ቀሪ ወረዳዎችን ጨምሮ የምርጫ መወዳደሪያ ወረዳዎችን እስከ 5 መቶ ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው እጩዎችን በህዝብ ተሳትፎ በየወረዳው መርጦ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን፣ በራሱ ባወጣው የምርጫ የስነ-ምግባር መመሪያም እያሰለጠነ መሆኑን ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አመልክቷል፡፡
ከ40 በላይ በተለያዩ ጉዳዮች የተዘጋጁ የፖሊሲ አማራጮችን ቀርፆና አዘጋጅቶ ለ6ኛው ዙር ሃገራዊ ምርጫ ለውድድር የቀረበው ኢዜማ፤ በመላ ሃገሪቱ ከ228 በላይ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችንም ከፍቷል፡፡
ለምርጫ ዝግጅቱ ሰፊ የፋይናንስ አቅም በመፍጠርም፣ ዋነኛ የምርጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ እየሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቀው፡፡
ኢዜማ የካቲት 20 ቀን 2013 በግሎባል ሆቴል በሚያካሂደው የገቢ ማሰባሰቢያ የራት መርሃ ግብርና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች በመጠቀም ከ140 ሚሊዮን ብር  በላይ ገቢ ለማሰባሰብ አቅዷል፡፡ በራት መርሃ ግብሩ ላይ ለሚታደሙ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በየደረጃው የተዘጋጁ የ10 ሺህ ብር፣ የ25 ሺህ እና 50 ሺህ ብር የራት መግቢያ ካርዶች መዘጋጀታቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ከእራት መርሃ ግብሩ ባሻገር ፓርቲውን ማጠናከር የሚፈልጉ አካላት የባንክ ሃሳብ አማራጮችን እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉና ህብረተረሰቡ ትብብር እንዲያደርግም ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአዲስ አበባ በእያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ ለምርጫው ማካሄጃ 840 ሺህ ብር እንደሚያስፈልገው የገለፀው ኢዜማ ይህም በየወረዳው ካሉ ደጋፊዎች የሚሰበሰብ ይሆናል ብሏል፡፡
የገቢ አሰባሰቡን አስመልክቶ በትናንትናው እለት መግለጫ የሰጠው ኢዜማ በ5 ሚሊዮን ብር ከፍተኛ እድሳት ያካሄደበትንና በፕ/ር መስፈን ወልደ ማሪያም ስም የተሰየመን መለስተኛ የስብሰባ አዳራሽን ጨምሮ በዘመናዊ የቤት ውስጥ ዲዛይን  የተዋቡ የፅ/ቤቱን የተለያዩ ቢሮዎች ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል፡፡
https://youtu.be/N9mVRu1bjj8?t=43

Read 12586 times Last modified on Wednesday, 10 February 2021 19:33