Saturday, 06 February 2021 12:31

የአመራሮች ውዝግብን አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ምርጫ ቦርድ በኦነግ ፓርቲ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሕጋዊና ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም መሠረት፡-
የፓርቲው የተወሠኑ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ነኀሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈና በድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱን ሊቀ መንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ አሳውቀው እንደነበር፣ ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ አመራር ላይ ተከታታይ አቤቱታዎች አስገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል፤ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር መስከረም 02 ቀን 2013 ዓ.ም ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀ-መንበር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ እንደወሠነ ለቦርዱ አሳውቀዋል።
በፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሠትና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሣኔ ሃሣብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባዔ ለማቋቋም  በተሠጠው ሥልጣን መሠረት በማድረግ፤ የሁለቱንም ቡድኖች ደብዳቤዎችና አቤቱታዎች እንዲሁም የውስጥ ሕጎች የሚያይ የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋም
ውሣኔ አሳልፎ እንደነበርም ይታወሳል። በዚህም መሠረት በእነ አቶ አራርሶ በኩል ባለሞያ ቢመድቡም፤ በእነ አቶ ዳውድ በኩል ባለሞያ ለመመደብ ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ የፓርቲው የውስጥ ደንብ መሠረት መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው በማለት መልስ በመሥጠታቸው የባለሞያዎች ጉባዔ ማቋቋም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በኦነግ አመራር መካከል ተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው የመጀመሪያው የቦርዱ ጥረት ባለመሳካቱ ጉዳዩን ከባለሞያዎች ጉባዔ ይልቅ በራሱ ሊያየው ተገዷል። በዚህም መሠረት ከሁለቱም ወገን የገቡትን ዕገዳዎች በማየት እና የገቡ ሠነዶችን በመመርመር እንዲሁም ከሁለቱም ቡድን አመራሮች ጋር እንዲሁም ከሥነ-ሥርዓት እና ቁጥጥር ኮሚቴ አመራር አባላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም ወቅት ፓርቲው አመራር ቀውስ ውስጥ እንደገባ፣ ለአባላቱ አመራር መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ያቀረቧቸው ዕገዳዎች ሕጋዊ እንዳልሆኑ ቦርዱ ወሥኗል። በዚህም መሠረት የሁለቱም ወገን ዕገዳ የቀረበባቸው አባላት በነበራቸው ሕጋዊ ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ወሠነ። በሌላ በኩል ሁለቱም አካላት ሕጋዊ ሂደቱ የተሟላ ሠነድ ባለማቅረባቸው፣ ፓርቲው ያለበትን የአመራር ቀውስ ለመፍታት አለመቻላቸውን በመረዳት ቦርዱ የአመራር መከፋፈሉን ጠቅላላ ጉባዔ በማከናወን የፓርቲው አባላት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡ ታኅሣሥ 08 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከመወሠኑም በተጨማሪ የጠቅላላ ጉባዔውን ለማመቻቸት ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ ዐሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።
ከላይ በተጠቀሰው ውሣኔ መሠረት፤ ለሁለቱም አመራር ቡድኖች የቦርዱ ውሣኔ በደብዳቤ ደርሷቸው የመጀመሪያውን ውይይት በቦርዱ አመቻችነት በጋራ ለማከናወን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጥሪ ቢደረግላቸውም፤ በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ቡድን ቦርዱ በጠራው ስብሰባ ላይ ሲገኝ፤ በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን ግን “ቦርዱ ይህንን የማመቻቸት ሕጋዊ ሚና የለውም” በማለት በውይይቱ ላይ አልገኝም በማለታቸው በቦርዱ የተደረገው ጥረት አሁንም ሊሳካ አልቻለም።
ይህ ሂደት በዚህ ላይ እንዳለ፤ ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ማመልከቻዎችን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ምርጫ  ቦርድ፤ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም  ባደረገው  የቦርድ አመራር አባላት ስብሰባ የኦነግ  ሥራ  አስፈጻሚ መከፋፈልን አስመልክቶ እስከ አሁን የተደረጉ ጥረቶችንና ለመፍታት የወሠዳቸውን ዕርምጃዎች በዝርዝር መርምሯል። በዚህም መሠረት ቦርዱ እጁ ላይ ባሉት የሕግና የአስተዳደር መሣሪያዎች በመጠቀም ሊያግዝ የሚችልበት ተጨማሪ አሠራር አለመኖሩን ተረድቷል።
በዚህም መሠረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት፣ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮችና አመራሮች ለችግሩ መፍቻ ሊሆን የሚችለውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ ቦርዱ ማሳሰብ እንደሚገባው ወሥኗል። በመሆኑም ፓርቲው በመካከሉ የተፈጠረውን አለመግባባት በሥራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮችና አባላት ዐውቀው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲከናወን የሚያደርጉባቸውን
ማንኛውንም መንገዶች እንዲጠቀሙ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም



Read 1323 times