Saturday, 06 February 2021 12:36

“ህብር ኢትዮጵያ” - የምርጫ ተስፋና ተግዳሮቶቹ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

· እነ አቶ ልደቱና ኢንጂነር ይልቃል ተቀላቅለውታል
    · የፖለቲካ ምህዳሩ አለመከፈቱ በእጅጉ ያሳስበናል
    · በቀድሞ የኢዴፓ የምርጫ ምልክት ይወዳደራል
    · የፖለቲካ ችግራችን የርዕዮተ ዓለም አይደለም

          በመጪው ግንቦት ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ 49 ፓርቲዎች ከሰሞኑ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታቸውን መውሰዳቸው ተረጋግጧል፡፡ በዚህም መሰረት ብልፅግና ፓርቲ- የሚበራ አምፖል፣ ኢዜማ- ሚዛን፣ መድረክ- አምስት ጣት፣ አብን - ሰዓት፣ ባልደራስ - የተጨበጠ የቀኝ እጅ መዳፍ፣ ሕብር ኢትዮጵያ ደግሞ የቀድሞ የኢዴፓ ምልክት የሆነውን - አደይ አበባ መርጠዋል። ሌሎችም ፓርቲዎች ይወክለናል ያሉትን የተለያዩ የውድድር ምልክቶች መመርጣቸውን ከምርጫ ቦርድ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በእጩ መረጣ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣም እስከ ምርጫው መዳረሻ ባሉ ጊዜያት በተቻለ አቅም ሁሉ በምርጫው ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለአንባቢያን ለማስተዋወቅ ይሞክራል - በአመሰራረት፣ በርዕዮተ ዓለም፣ በአላማና ግብ፣ በፖሊሲ አማራጮች፣ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፡፡
ለዛሬ አምስት ፓርቲዎች ተዋህደው የመሰረቱትና በቅርቡ የኢዴፓ እና ኢሃን አመራርና አባላት የተቀላቀሉት የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ግርማ በቀለ፣ ከጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡


            እስቲ ስለ ህብር ኢትዮጵያ አመሰራረት ይንገሩን?
በለውጡ ማግስት ወደ ሃገር ቤት የተመለሱና ሃገር ውስጥ ያሉ አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች ተዋህደው ነው ህብር ኢትዮጵያን የመሰረቱት። ከ1984 ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲነት ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ም/ቤት፣ ቱሣ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ኢትዮጵያችንና ደቡብ አረንጓዴ ኮኮቦቹ ናቸው ፓርቲውን የመሰረቱት።
የፓርቲው አላማና ግብ ምንድን ነው?
ህብር ኢትዮጵያ ዋነኛ መሰረቱ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ሃገር በቀል እሴቶችን ማዳበር ላይ ነው። በአውሮፓውያንና በፈረንጆች በሚነገረው ላይ ተንጠልጥለን፣ የራሳችንን ጥለን፣ የነሱን ተሸክመን በመሄዳችን ምክንያት የፖለቲካ እሳቤና ትርጓሜያችን ከማህበረሰባችን እሴት ጋር መታረቅ ያቃተው ሆኗል። ህዝባችንም ፖለቲካ ውሸት ነው፤ ፖለቲካ ቁማር ነው በሚሉ እሳቤዎች እንዲያምን ተደርጓል። ከዚህ መደናገር ለመውጣት የሚቻለው፣ ሃገራዊ የፖለቲካ እሳቤዎችን በማዳበር ነው የሚል እምነት አለን። ሁለተኛው አላማ አድርገን የምንንቀሳቀሰው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ላይ ነው።
በየትኞቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ነው በስፋት የምትንቀሳቀሱት?
የምርጫ ቦርድ ህግ እንደሚለው፤ አንድ ፓርቲ ሃገራዊ የሚሆነው አብላጫው አባላት ከሚኖሩበት አካባቢ 40 በመቶ ፊርማ እንዲሁም ከሌሎች አራት ክልሎች ደግሞ ከእያንዳንዳቸው ቢያንስ  15 በመቶ አባላት እንዲይዝ ይጠበቃል። በዚህ መሰረት እኛ  ከደቡብ ክልል 40 በመቶ የአባላት ፊርማ ስናስገባ፤ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አዲስ አበባና ሶማሌ ክልሎች ከእያንዳንዳቸው 15 በመቶ አስገብተናል። ከዚህ አልፎ በትግራይ አባላት አሉን፤ በቤንሻንጉል መተከልና አሶሳ እንዲሁም በሲዳማም አሉን፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ነው በሰፊው በምርጫ ልንሳተፍ ዝግጅት እያደረግን ያለነው።
በምን ያህል የምርጫ ወረዳዎች ላይ እጩዎች አዘጋጅታችኋል?
 ጠንካራው የምርጫ አካባቢያችን የደቡብ ክልል ነው። የጎላ እንቅስቃሴም እያደረግን ነው። ክልሉን ሙሉ ለሙሉ እንሸፍናለን ብለን ነው የምናስበው። ከዚያ ውጪ በአማራ ክልል፡- ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ እጩዎችም በእነዚህ አካባቢ በስፋት እየመለመልን ነው። በኦሮሚያም ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሃረርጌ፣ አርሲ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ባሌና ጅማ እንዲሁም ፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ በስፋት እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው። እጩዎችም በእነዚህ አካባቢዎች አዘጋጅተናል። በቤንሻንጉልም በመተከልና አሶሳ፣ በሲዳማ ሙሉ ለሙሉ እጩዎች አሉን፡፡ አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ፤ ሶማሌ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።
እስካሁንም ወደ 280 እጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አዘጋጅተናል። አሁንም ገና የእጩዎች ምልመላ ሪፖርቶችን እየጠበቅን ነው፤ ተጠቃሎ ሲደርሰን የምንገልፀው ይሆናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ከዚህ በፊት አብሮነት በሚል ስብስብ አብረውን የነበሩት የኢዴፓ እና የኢሃን አመራሮችና አባላት ተቀላቅለውናል።
በምን መሰረት ላይ ነው ከእናንተ ጋር የተቀላቀሉት? በፕሮግራም ተመሳሳይ ሆናችሁ ነው?
ቀደም ሲል አብሮነትን የመሰረትንበት መርህ አለ። በዚያ መሰረት ፕሮግራሙን ተቀብለው አምነውበት ነው አባል የሆኑት።
ፖሊሲዎቻችሁ ምን ይመስላሉ?
ህብር ኢትዮጵያን የመሰረቱት ፓርቲዎች በተናጠል በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮች አሉን። በሁሉም ዘርፎች ዝርዝር ፖሊሲዎች አዘጋጅተናል። አሁን ሃገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማመሳሰል ተግባር እያከናወንን ነው፤ ወቅቱ ሲደርስ ይዘነው የምንቀርብ ይሆናል።
የምትከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ለዘብተኛ ሊበራል ዲሞክራሲን ነው የምንከተለው። ይህን ስል ግን የዚህ ሃገር የፖለቲካ ችግር የርዕዮተ ዓለም አይመስለኝም። 100 ምናምን ፓርቲዎች የተፈጠሩት በርዕዮተ ዓለም ልዩነት አይደለም። መርህና ሃገራዊ እሴቶች የመጥፋት ችግር ነው። ማህበራዊ እሴቶቻችንን ማጣታችን ነው ችግራችን እንጂ የርዕዮተ ዓለም አይደለም።
ህብር ኢትዮጵያ በዚህ ምርጫ ላይ ከሌሎች የተለየ ያደርገኛል፤ የኔ መገለጫ ይሆናል የሚለው ነገር ምንድን ነው?
እኛ መሰረታዊ እሳቤያችን ሃገራዊ እሴቶቻችን ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲን የመገንባት እሴት ማራመድ ነው። ይሄ ማለት ቀበሌዎቻችን የራሳቸውን መሪ መርጠው፣ በራሳቸው እሴቶች ብቻ እንዲደራደሩ ማስቻል ነው። አሁንም እኮ ከላይ ያለው ፖለቲካ ሳያስፈልጋቸው በማህበራዊ እሴታቸው በሰላም የሚኖሩ አካባቢዎች ቀበሌዎች አሉ። ያንን ማጎልበት ላይ እንሰራለን። አሁን እኮ ችግር ውስጥ የገባነው የሃይማኖት አባቶችን የሃገር ሽማግሌዎችን ፖለቲከኞች አድርገን እያበላሸን ነው። ከማህበራዊ እሴቶቻቸው ውጪ እንዲሆኑ እያደረግን ነው፤ ለብዙ ትርምስ የተዳረግነው የሚል እምነት አለን። ይህን ሃሳብ በሰፊው የምናራምድ ይሆናል። ይህም አንዱ መለያችን ይሆናል። ወደ ሃገራዊ እሴቶቻችን የተመለሰ መንግስት እንዲገነባ ማስቻል ነው አላማችን። ሁለተኛው እዚህ ሃገር ውስጥ በፖለቲካ እሳቤም ሆነ አተገባበር አዲስ አተያይ ያስፈልገዋል ብለን ነው የምናምነው። ይሄም ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ነው። ይሄም አላማችን መለያችን ይሆናል።
በቅርቡ ህብርን ከተቀላቀሉት አንጋፋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ አቶ ልደቱ ናቸው። አቶ ልደቱ የት ነው የሚወዳደሩት? ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ይወዳደሩ  ይሆን?
እሳቸው ፍላጎታቸውን ሊገልጹ ይችላሉ። ነገር ግን የፓርቲ አባል እንደመሆናቸው፣ ፓርቲው እሳቸውን የሚያጭበት ቦታ ላይ በምክክር እንዲወዳደሩ ያደርጋል። እኛ ለጠቅላይ  ሚኒስትርነት  ከፈለግናቸው ለህዝብ ተወካዮች እንዲወዳደሩ ተመካክረን ልንወስን እንችላለን፡፡
የምርጫ ምልክታችሁ አደይ አበባ ነው። ከዚህ በፊት ኢዴፓ የሚወዳደርበት ምልክት ነበር፡፡ እንዴት መረጣችሁት? ትርጉሙስ ምንድን ነው?
ህብር ኢትዮጵያ ምን ያህል ገዥ ሃሳብ ሲያገኝ ለመቀበል በሩ ክፍት እንደሆነ ማሳያው አንዱ፤ ኢዴፓ የተወዳደረበትን አደይ አበባ መጠቀሙ ነው፡፡ ገዢ ሃሳብ ስለሆነ እኛም መርጠነዋል፡፡ አደይ አበባ በመስከረም ወር የሚፈካ፣ ለኢትዮጵያ ልዩ የሆነ አበባ ነው፡፡ ከክረምቱ ወደ  ፀደይ የምንሸጋገርበትን ወይም ከጨለማ ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበትን ጊዜ አብሳሪ ነው፡፡ ቀለሙ ቢጫ ነው፡፡
ከጨለማና ጭጋግ ወደ ብርሃን የሚያሸጋግረን የተስፋ ምልክት ነው። አዲስ አመትን በአዲስ ተስፋ እንድንቀበል ልቦናችንን የሚያነሳሳ ልዩ ምልክታችን ነው። ለሃገራችን የሰነቅነውን ህልምና ተስፋችንን የምንገልጽበት ነው፡፡
ህብር ኢትዮጵያ አብላጫውን የፓርላማ ወንበር አሸንፎ መንግስት ቢሆን የመጀመሪያው ተግባሩ ምን ሊሆን ይችላል?
ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የመጀመሪያው ስራችን ይሆናል፡፡ ሲደራረቡ የመጡ የማህበራዊ ግንኙነቶች ሰንኮፎቻችንን መንቀል ላይ እናተኩራለን። የአስተሳሰብ ልዩነቶች የሚቻቻሉበትን፣ እስከ ዛሬ የመጣንባቸውን ቁስሎች የምናክምበትን፣ በጎ ማህበራዊ እሴቶቻችንን የምናሳድግበት፣ ጎጂዎቹን የምናስወግድበት አይነት ብሔራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም መፍጠር ነው አላማችን፡፡
በቀጣይ ምርጫ ስጋት ብላችሁ የምታስቀምጡት ምንድን ነው?
ስጋታችን አሁን ያለው መንግስት ባለፉት ሶስት የሪፎርም አመታት ባሳየው መንገድና ካለፉት አምስት ምርጫዎች የተለየ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ወይ የሚለው ነው፡፡ አሁን ያሉት የመንግስት አካላት በእነዚሁ ምርጫዎች ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩና የህወሃትን የምርጫ ሴራ በተግባር ተሳትፈውበት የሚያውቁና ተባባሪ ሆነው የኖሩ ናቸው፡፡ ዛሬም የምናያቸው ምልክቶች ከዚህ ሴራ እንዳልተላቀቁ አመልካች ናቸው፡፡ ፖለቲካ ቁማር ነው የሚል አመለካከታቸውን እንዲሁም  እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ሽኩቻ ስንመለከት፣ ከዚያ ከተለመደው አዙሪት እንዳልወጣን እንገነዘባለን፡፡
ምርጫውን ማካሄድ የሚያስችል ሃገራዊ ዝግጁነት አለመኖሩ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከዚህ አንጻር ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ፣ ከላይ ያለውን ሁኔታ ከመቀየር ውጪ፣ ዋነኛ ስራው የሚሰራበት መሬት ላይ ያለው አስተሳሰብ አለመቀየሩ አስጊ ነው፡፡ የተለመደው ማጭበርበር ሊኖር ይችላል፤ ምርጫው ከግጭት የፀዳ አይሆንም የሚለው አሁንም ከፍተኛ ስጋት ነው፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ አለመከፈቱና የተመቻቸ የፖለቲካ ሁኔታ አለመፈጠሩም በእጅጉ ያሳሳበናል፡፡
ተስፋ የምታደርጉትስ?
በዚህች ሃገር ውሰጥ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ሁለት ነገሮችን ያመላክተናል፡፡ አንደኛው፤ የምንታገልለት የብሔራዊ መግባባትና እርቅ መንገድ፣ ቅድሚያ እንዲያገኝ ህዝባችን ይፈልጋል። ይሄ ፍላጎት በራሱ ተስፋ እንዲኖረን ያደርገናል፡፡ በሌላ በኩል፣ ህዝቡ ከገዢው ፓርቲ ይልቅ እኛን ይመርጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሁለተኛው ተስፋችን፤ በምርጫው ብንሸነፍም እንኳን የማይናቅ ቁጥር ያለው ወንበር ይኖረናል፤ የተለያዩ ሃሳቦች በፓርላማው ይንሸራሸራሉ፤ ህዝቡም ሃሳቡ የሚሰማበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ተስፋ አለን፡፡


Read 1610 times