Print this page
Tuesday, 09 February 2021 00:00

በመፈንቅለ መንግስት የወረዱት የኖቤል ሰላም ተሸላሚዋ “በህገ-ወጥ ሬዲዮ” ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው ሰኞ ማለዳ በተደረገ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ወርደው ለእስር የተዳረጉት የኖቤል የሠላም ተሸላሚዋ የማይንማር ብሔራዊ መሪ አን ሳን ሱ ኪ፤  የአገሪቱን የገቢ ንግድ ህግ በመጣስ ከውጭ አገር ያስገቡትን “ህገወጥ የሬዲዮ መገናኛ” ያለፈቃድ ይጠቀሙ ነበር ተብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተነግሯል፡፡
ለዲሞክራሲ መስፈን ባደረገት ትግል ምክንያት 15 አመታትን በቁም እስር ያሳለፉትና በአገሬው ዘንድ “የዲሞክራሲ እናት” እየተባሉ ሲንቆለጳጰሱ የኖሩት አን ሳን ሱ ኪ፤ ከወራት በፊት በምርጫ አሸንፈው ከያዙት ስልጣን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት መውረዳቸውን ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ በህገወጥ መንገድ ከውጭ አገር ያስገቡትና ያለፈቃድ የሚጠቀሙበት የሬዲዮ መገናኛ ተገኝቶባቸዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው አመልክቷል፡፡
ፖሊስ በ ሱ ኪ ላይ የጀመረውን ምርመራ እስኪያጠናቀቅ ድረስ ግለሰቧ ለ15 ቀናት ያህል በእስር ላይ ይቆያሉ መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ እንደሚችሉም አክሎ ገልጧል፡፡
በወታደሮች በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ አንስቶ ደብዛቸው የጠፋው አን ሳን ሱ ኪ  በአሁኑ ወቅት ታስረው ያሉበት ቦታም በግልጽ እንደማይታወቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ ከእሳቸው በበተጨማሪ በወታደራዊ ሃይሉ ተይዘው ለእስር በተዳረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊን ማይንት ላይ የተለያዩ የወንጀል ክሶችን መመስረቱንም ገልጧል፡፡
በማይንማር የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ ከተፈጸመው አስከፊ ግፍና ስደት ጋር በተያያዘ በብዙዎቸ የሚተቹት የ75 አመቷ አን ሳን ሱ ኪ፣  ባለፈው ህዳር በተደረገ አገራዊ ምርጫ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ የተባለውን ፓርቲያቸውን ወክለው በማሸነፍ ወደ ስልጣን ቢመጡም፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል ግን ከተቃዋሚዎች ጋር በመወገን ምርጫው ተጭበርብሯል ሲል ቆይቶ በስተመጨረሻ፣ ባለፈው ሰኞ በጦር አዛዡ ሚን ኡንግ ሃይንግ መሪነት በተቀነባበረ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው አውርዶ መንበሩን በመረከብ የአንድ አመት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽንቷል፤ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የቀድሞ ባለስልጣናትንም አስሯል፡፡
ፓርቲያቸው ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ አን ሳን ሱ ኪ በአስቸኳይ እንዲፈቱ መጠየቁንና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የሴትዮዋ ደጋፊዎችም በማህበራዊ ድረገጾች እና በአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ በጀመሩት ዘመቻ ህዝቡ ለወታደራዊው ሃይል እንዳይገዛና በእንቢተኝነት ታጥቆ እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ የወታደሩ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ታዋቂ የአገሪቱ አክቲቪስቶች በአንጻሩ ህዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት መፈንቅለ መንግስቱን እንዳወገዙት የዘገበው ሮይተርስ በበኩሉ፣ የቡድን ሰባት አገራትም የማይንማር ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ ሃይል በአፋጣኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲሽር፤ ስልጣኑን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠው መንግስት እንዲያስረክብ፣ ያላግባብ ያሰራቸውን ባለስልጣናት እንዲፈታና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብር ጥሪ ማቅረባቸውን  ዘግቧል፡፡

Read 2235 times
Administrator

Latest from Administrator