Print this page
Saturday, 06 February 2021 14:16

“ቴአትር በዘመነ ኢህአዴግ ያሳየው እመርታ?”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 (የዩኒቨርሲቲ ትውስታ)

             ቴአትር ስንማር ነው፤ የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ የሚባል ኮርስ ስንወስድ፤ በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን በማይገባኝ ሁኔታ ሌሎች የትምህርት አይነቶች ላይ ባልተለመደ መልኩ የቃል ፈተና ወስደን ነበር። መምህራችን በቢሯቸው ተቀምጠው በየተራ እየገባን፣ የባለጉዳይ ወንበር ላይ ተቀምጠን፣ ለሚቀርብልን የቃል ጥያቄ የቃል መልስ መስጠት። የትምህርት ክፍሉን ስንቀላቀል ቁጥራችን በርከት ያለ ቢሆንም፣ ቀስ ቀስ በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡ ተማሪዎች ስለነበሩ፣ ይህንን ኮርስ ስንወስድ ምን ያህል ተማሪዎች በክፍል ውስጥ እንደቀረን የማስታውሰው፣ በዚያን እለት ለፈተና የተዘጋጁት ጥያቄዎች 22 እንደነበሩ ትዝ ሲለኝ ነው።
እናም ተራዬ ደርሶ ገባሁ፣ ገና ወንበሩ ላይ ተደላድዬ ሳልቀመጥ፣ ከጊዜ ጋር ቀጠሮ ያላቸው የሚመስሉት መምህራችን፣ ስለ ፈተናው አሰጣጥ፣ ዘለግ ባለ ድምፃቸው መመሪያ ቢጤ መስጠት ጀመሩ፡-
 “ሃያ ሁለት ጥያቄዎች አሉ፤ ከነዚህ መካከል አንድ ቁጥር ትጠሪያለሽ። የሚደርስሽ ጥያቄ ዘለግ ያለ መልስ የሚያስፈልገው ከሆነ አብራርተሽ ትመልሺያለሽ፤ 7 ደቂቃ ይሰጥሻል። መልሱ አጭር ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ ጥያቄ ትጠየቂያለሽ”
“እሺ” አልኩ።
የትኛው እንደሚሻለኝ እርግጠኛ ባልሆንም፣ ገና “ፈተና” ሲባል በደቂቃ 140 ጊዜ የሚመታውን ልቤን አደብ ለማስያዝ እየሞከርኩ። ቀላሉ እንዲገጥመኝ ለራሴ ተመኝቼ ሳልጨርስ፤
“የጥያቄ ቁጥር ምረጪ!” አሉ መምህሬ
“እእእእእ... ጥያቄ ቁጥር...” ብዬ ሳሰላስል፣ ለጥያቄው መልስ ከምሰጥበት ጊዜ የበለጠ ቁጥር ለመምረጥ የማጠፋው ጊዜ የቆጫቸው ይመስል፣ “ከአንድ እስከ ሃያ ሁለት ካሉት ቁጥሮች ውስጥ አንዱን ምረጪ” ብለው አጣደፉኝ። በድንጋጤ፤ “ማርያም አውጪኝ” ብዬ አፌ ላይ እንደመጣልኝ “21” አልኩኝ።
“21... 21....” አሉና ጥያቄ የፃፉበትን ወረቀት በእስክሪብቶአቸው ጫፍ እየጠነቆሉ፣ከአንድ ጀምረው ቁልቁል ወደ ጠራሁት ጥያቄ በአይናቸው ተንደረደሩና፤
“21!... ተይዟል” ብለው ቀና አሉ። ቀደም ሲል በመመሪያቸው ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስላልገለፁልኝ ግር እየተሰኘሁ ሌላ ቁጥር በማሰብ ላይ ሳለሁ “ተይዟል፤ ብርቱካን ተጠይቃ መልሳዋለች፤ ሌላ ምረጪ” ብለው አከሉበት። ቀጥሎ የጠራሁትን ቁጥር አላስታውሰውም፤ ብቻ አንዱን ጠራሁ። መምህሬ ፈገግ ብለው፤ “ዘርዘር ያለ መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው የመረጥሽው” አሉ። ፈገግ አባባላቸው “የታ’ባሽ፣ አገኘሁሽ” የሚል ይመስል ነበር። (አብዛኛው የሃገራችን መምህር ለተማሪ ፈተና በማክበድ የሚዝናና ይመስለኛል)
“ወይ ጉዴ አለቀልኝ; አልኩ
“ሰባት ደቂቃ ነው ያለሽ” ጊዜ ለመቆጠብ እኔን ሲያጣድፉ እሳቸው አንዱን መመሪያ እየደጋገሙ የሚያጠፉት ሰአት አይታወቃቸውም፤ ወይም ነገር በመደጋገም የፈተናውን ድባብ አስጨናቂ ሊያደርጉት ይሞክራሉ፤ ያም ተጨማሪ ደስታ ሳይሰጣቸው አይቀርም።
“ልብ ብለሽ አዳምጪ...ጥያቄ ቁጥር...” ይሉና ፋታ ይወስዳሉ። የኔ ልብ ምቷ ይጨምራል። የቴአትር አፃፃፍ መምህሬ ቢሆኑ ኖሮ፣ አንድ ተውኔት እንዴት ልብ አንጠልጣይ መሆን እንደሚገባው፣ በተግባር ሊያስተምሩኝ ይመስለኝ ነበር። ለነገሩ ተመርቄ ከወጣሁ ከጥቂት ጊዜአት በኋላ የኢቲቪ ጥያቄና መልስ አቅራቢ ሆኜ ስሰራ ይቺን “ጥያቄ ቁጥር...” እያሉ ተወዳዳሪዎች ላይ ጭንቀት መፍጠርን ሳልጠቀምባት አልቀረሁም። (እንዲህ ነው የተማሩትን በተግባር ላይ ማዋል)
“ቴአትር በዘመነ ኢህአዴግ ያሳየው እመርታ?” ጥያቄውን ዱብ አደረጉት። (አልጨመርኩም አልቀነስኩም፤ ጥያቄው ቃል በቃል ነው)።
“እደግመዋለሁ... ቴአትር...” ሊቀጥሉ ሲሉ “እመርታ ምንድነው?” አልኩኝ ጣልቃ ገብቼ። የእመርታ ትርጉሙ ጠፍቶኝ አልነበረም፤ ይልቁንም ለጥያቄው ማብራሪያ እስከሚሰጡኝ የማሰቢያ ጊዜ ለመግዛት ነበር።
መምህሬ ሃሳቤ ገብቷቸው ይሁን የእመርታን ትርጉም አለማወቄ አበሳጭቷቸው፤ “ይሄ እኮ ፈተና ነው ፤መልሰሽ እኔን ተጠይቂኛለሽ?” ብለው ተቆጡ። ሰአታቸውን እየተመለከቱ፣ የተሰጠኝ ደቂቃ መቁጠር መጀመሩን አክለው ነገሩኝ።
በታሪክ ትምህርታችን፣ ቴአትር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትን ተከትሎ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጅሮንድ ተ/ሐዋርያት ተ/ማርያም ፋቡላ/የአውሬዎች መሳለቂያ መጀመሩን ይነግረናል። ይህንንም ማወቅ መሰረታዊ በመሆኑ በጥያቄ መልክ አለመቅረቡ የሚጠበቅ ነው። የትምህርቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ግን ምን ነበር? ጠፋብኝ፣ በእርግጠኛነት ግን ዘመነ ኢህአዴግ ላይ አላደረሰንም። የማንም ድክመት ይሁን በምንም ምክንያት ግን በትምህርታችን ውስጥ የሚጠቀሱ የቴአትር ስራዎች ብዙዎቹ ቀደምት ናቸው (ከ"ውበትን ፍለጋ" እና ከ"ፍቅር የተራበ" ውጪ ለምሳሌነት የሚነሳ ከነበረ፣ አብራችሁኝ የተማራችሁ አስታውሳችሁ አርሙኝ)፡፡
እናም መምህራችን ሲያስተምሩን ምናልባትም ዘመኑን እየኖርንበት ስለነበረ ገና በታሪክነት አልደመሩት ይሆናል። ግን ለፈተና ሲሆን “ዘመነ ኢህአዴግን ያውም እመርታዋን ምን ሲሉ አሰቧት?” እያልኩ ሳሰላስል፤
“የመጀመሪያው ደቂቃ አልቋል” አሉኝ፤ በስል ድምፃቸው።
ዞሮ ዞሮ ያጠናሁትን ሳይሆን ያየሁትንና እየኖርኩ ያለሁትን እንድገልፅ ስለተጠይቅኩ በአንድ በኩል ዘና አልኩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ (በወቅቱ ቴአትር እሰራ ስለነበር) በቴአትር ቤቶች አካባቢ የሚነሱ ችግሮችን እንጂ እመርታ ለማየት እድል አልነበረኝምና፣ ምን እንደምመልስ ግራ እንደገባኝ ትንፋሼን ሳብ አድርጌ ፈተናው በቀጥታ የሚገናኘው ከውጤቴ ጋር በመሆኑም ስጋቴ የወለደልኝን ማብራራት ጀመርኩ።
“አንደኛ የቴአትርና የቴአትር ቤቶች መስፋፋት” አልኩ።
“ማለትም ተጨማሪ ቴአትር ቤቶች መከፈታቸው፤ እነዚህም የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር፣ ሜጋ አምፊ ቴአትር፣ የፑሽኪን የባህልና ቴአትር አዳራሽ እና ባህርዳር ሙሉዓለም የቴአትር አዳራሽ። ሁለተኛ በርካታ የቴአትር ክበባት ተመስርተዋል፤ በተጨማሪም በሆቴል አዳራሾችና በግል ሲኒማ ቤቶች ቴአትሮች መታየት ጀምረዋል።” አልኩኝ፤ የተብራራ እንዲመስል ረጋ ብዬ ቃላቶቼን ለጠጥ እያደረግኩ።
“የት ሲኒማ ቤት እና ሆቴል ነው ቴአትር የሚታየው? ምን የሚባል ቴአትር?” መምህሬ ስለጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች መረጃ ያላቸው አይመስሉም። አጠያየቃቸውም የማፋጠጥ ሳይሆን “እንዲህም ተጀምሯል?” የሚል አይነት ነበር። እኔም ያልጠበቁት አዲስ መረጃ መስጠቴ እንደ ተጨማሪ ነጥብ ተቆጥሮ ማርክ ያስጨምርልኝ ይሆን? ብዬ እያሰብኩ፣ አብራርቼ መለስኩ። "ለእረፍት የመጣ ፍቅር" በኢምፔሪያል ሆቴል፣ "የአዛውንቶች ክበብ" ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ "የዳዊት እንዚራ" (መሰለኝ አሁን ተዘንግቶኛል) ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም ሲኒማ ይታዩ ነበር።
“ሌላ...." ብዬ አንድ ሙሉ ደቂቃ በዝምታ ካጠፋሁ በኋላ፣ የፊልም መበራከትና የሲኒማ ቤቶች መስፋፋትም ተመልካቹ ኪነጥበብን ለመዝናኛነት እንዲመርጥ ስለሚያደርግ፣ በተዘዋዋሪ ወደ ቴአትር ቤቶች እንዲመጣ ያደርገዋል። ለባለሙያዎችም ተጨማሪ የስራ ዕድል ስለሚፈጥር..." ብዬ አበቃሁ።
በጠቅላላው አምስት ደቂቃዎችን ተጠቅሜአለሁ። የቀሩኝን ሁለት ደቂቃዎች ደግሞ ደጋግሜ እንዳስብና እንድጠቀምባቸው በመወትወት ራሳቸው መምህሬ ጨረሷት። ሌላ መልስ አልነበረኝም።
“መልካም! ፈተናው አልቋል። ትክክለኛ መልሶቹን እንመለከትና ከሰጠሽው መልስ በመነሳት ውጤትሽን እነግርሻለሁ” አሉኝ፤ እንደ አዲስ ተናጋሪ ድምፃቸውን እየሞረዱ፤ “አንደኛ ምላሽሽ መጀመር የነበረበት ለዘመነ ኢህአዴግ ትርጉም (definition) በመስጠት ነበር። ማለትም ‘ዘመነ ኢህአዴግ ማለት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ማለት ነው’ ካልሽ በኋላ እመርታዎቹን ትቀጥያለሽ። በዚህም አንዱንና ዋነኛውን በትክክል አብራርተሻል፤ በጣም ጥሩ ነው!” እያሉ በመልስኩበት ወቅት ሲፅፏቸው የነበሩ ነጥቦችን ከማስታወሻ ደብተራቸው ላይ እየተመለከቱና በሚያጉተመትም ድምፅ እያነበቡ፤ “ትክክል፣ ራይት፤ ትክክል፣ እእእ ህፃናትና ወጣቶች ብለሻል ራይት፣ ትክክል..” እያሉ ማረማቸውን ሲቀጥሉ፣ የኔም ልብ ሞቅ ማለት ጀምራ ነበር “ኤክስ” አሉ በመሃል ጮክ ብለው፤ “‘ፑሽኪን አዳራሽ’ ነው ያልሽው፣ ሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል ነው የሚባለው፣ ይሄ ፈተና ነው! ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የቴአትር ቤቶቹም የተመሰረቱበትን ጊዜ አልጠቀስሽም።” ቀና ብለው ሲመለከቱኝ አሳዘንኳቸው መሰለኝ፣ መለስ ብለው “ይሁን ብቻ ግማሽ እሰጥሻለሁ። ሌላው ግን አልተመለሰም”።
ሌላው ምንድነው? አልኳቸው በጉጉት
"ሌላውና ሁለተኛው ‘ሴቶችን ወደ ስልጣን ማምጣት ነው’" አሉኝ ።
ሴቶችን ወደ ስልጣን ማምጣት ከቴአትር ጋር ያለው ግንኙነት አልተከሰተልኝም። ግራ መጋባቴን አይተው ቀጠሉ፤ "ሴቶችን በቴአትር ቤቶች አስተዳዳሪነት መሾም! ጀማነሽ ሰለሞን የአ.አ ቴአትርና ባህል አዳራሽን፤ መንበረ ታደሰ እንዲሁም ማርታ ስለሺ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን እንዲመሩ መደረጉ ነው።
"ሶስተኛው እመርታ ደግሞ ቴአትሮች በብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ መሰራት መጀመራቸው ነው፤ ለዚህም ቅድም የጠቀስሽው የሜጋ አምፊ ቴአትር የኦሮምኛ ቴአትር ማሳየቱን ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። እናም የዛሬው ፈተና ይህንን ይመስላል” ብለው ወደ ማስታወሻ ደብተራቸው ተመልሰው ያገኘኋቸውን “ኤክስ” እና “ራይት” እየቆጠሩ ሲያሰሉ ከቆዩ በኋላ “እንግዲህ የዛሬው ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት የፅሁፍ ፈተናዎችና የክፍል ውስጥ ተሳትፎ ጋር ተደማምሮ (የአ.አ.ዩ የቴአትር ትምህርት ክፍል ከተጀመረ ጀምሮ "ለ30 አመታት በተማሪዎች የተሰሩ የመመረቂያ ፅሁፎች ዳሰሳ" በሚል ርዕስ የኮርስ ማሟያ ፅሁፍ ታዝዤ ማቅረቤን ልብ ይሏል)
በጠቅላላው ያመጣሽው ውጤት ሲ (C) ነው! በይ አሁን ፈጠን ብለሽ ቀጣዩን ተፈታኝ ጥሪልኝ” ብለው ወረቀቶች ማገላበጣቸውን ቀጠሉ። በሩን ከኋላዬ እየዘጋሁ “ተረኛ!” አልኩ።
እናም ዛሬ ከ10 አመታት በኋላ ቴአትር በዘመነ “ለውጥ” ላይ ሆና መቶ አመቷ ሲዘከር፣ ተረኛ ተፈታኞች ምን እየመለሱ ይሆን? እላለሁ። ቴአትርስ መቶ አመት ተጉዛ ያሳየችው እመርታ ምንድነው? እያልኩ የመምህሬን ጥያቄ እጠይቃለሁ። መልስ ያላችሁ ...
(ሜሮን ጌትነት፤ ከፌስቡክ ገጽ)

Read 1194 times
Administrator

Latest from Administrator