Monday, 08 February 2021 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

   አንዳንድ አስገራሚ አጋጣሚዎች አሉ። ምናልባት እያንዳንዱ ህይወት ያለው ፍጡርና ህይወት  ሌለው ነገር ውስጥ መላው ዩኒቨርስና ዘለዓለማዊነት ስለሚገኝ፣ መላው የኑኒቨርስና ዘላለማዊነት ውስጥ ዳግም መላው ፍጥረተ ዓለም በቅንጅት ስለሚንቀሳቀስ ይሆናል። እንደ ማህሌተ ቅኔ… እንደ መንዙማ ወይም እንደ …!! ልብ ካልን ዕለታዊ ኑሯችን በዚህ እውነት ድግግሞሽ የተሞላ ነው። ደረጃው፣ ዓይነቱና አቀራረቡ ወይም የባለቤቱ ንቃት (Awarness) ሊለያይ ይችላል እንጂ ሁሉም ሰው የዚህ ክስተት ምስክር ነው። ለምሳሌ ስናስበው የነበረ ሰው ድንገት ከች ሊል ወይም ስልክ ሊደውልልን ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ በሩቅ ወይም በወሬ ወሬ የጠላነውን ሰው በአጋጣሚ አግኝተነው ብናወራው፣ እንከን የለሽ ሆኖ ሊታየን ወይም ከልብ የምንወደው ሆኖ ሊገኝ ይችላል።
ከትናንት ወዲያ ሃሙስ ከሰዓት በሁዋላ ሰፈሬ በሚገኘው መዝናኛ አገልግሎት ክበብ መናፈሻ ውስጥ ቡና  እየጠጣሁ ስለምጽፈው ነገር አስብ ነበር። በሃሳቤ ውስጥ ታላቁ አሜሪካዊ ገጣሚና ተራኪ አላን ደላንፓ ከአእምኖዬ ጓዳ ድንገት ብቅ አለ። በልጅነቴ ካነበብኳቸው የሰውየው ድርሰቶች ውስጥ እስከ ዛሬ ያረሳሁዋት ጥቁሯ ድመት (The Black Cat) የተሰኘውን ብቻ በመሆኑ ሰውየውን ለምን እንዳስታወስኩ አልገባኝም። ወዲያው ግን ስለ ጥቁሯ ድመት ማሰብ ጀመርኩ። ባለ ታሪኳን ድመት በአእምሮዬ ሳሰላስል እግሬ አካባቢ የመለስለስ ስሜት ተሰማኝ። ጎንበስ ብል የምታምር ጥቁር ድመት እየተሻሸችኝ ነው።…እሱ ነው የገረመኝ።
አንዳንድ ሰዎች ጥቁር ድመት ይጠላሉ። መንገዴን ካቋረጠችኝ አይቀናኝም፣ ቀኔ ይበላሻል፣ አደጋ ያጋጥመኛል በማለት ይሰጋሉ። ባለ ቡናዋም ጥቁር ድመት አልወድም ብላ ልታባርራት ሞክራ ነበር። እኔ ግን ቀንና ምሽቱን በምቾት ነበር ያሳለፍኩት።
የአላን ደ ላንፓ ገፀ ባህሪም እንደ ሴትዬዋ ጥቁር ድመት አይወድም። ከስራው ወይም ከነበረበት ቦታ ወደ ቤቱ ሲመለስ ድመቷ ሶፋው ላይ ቁጭ ብላ ሲያያት ደሙ ይፈላል። “የማስበውን ነገር የምታውቅብኝ እየመሰለኝ እበሳጫለሁ፤ ሚስቴ ግን ትወዳት ነበር” ይላል።
በርግጥ ሰውየው ክፉ ነበር። ክፉ ባይሆን ኖሮ በትንሽ ንትርክ ሰበብ ውብና ደግ ሚስቱን ባልገደለ። ከገደላት በሁዋላም እንደልነበረች አድርጎ ደብዛዋን ባላጠፋ። ይባስ ብሎም ሚስቴ ጥላኝ ጠፋች በማለት ለፖሊስ ባላመለከተ ነበር። እንዲህ ዓይነት ሰው ክፉ ቢባል ምን ያንሰዋል? ፖሊሶቹ ሴትየዋን አፈላልገው ለማግኘት ባለመቻላቸው ግራ ተጋቡ። ምናልባት ፍንጭ ብናገኝ በማለት አንድ ቀን ወደ ባለትዳሮቹ መኖሪያ ቤት መጡ። የሴትየዋ ባለቤት ግቢውን አዟዙሮ አሳያቸው። ማስረጃ የሚሆን ነገር ግን አልተገኘም። ወደ መጡበት ሊመለሱ ሲሉ፡-
“ይቺ ድመት የት ሆና ነው እንዲህ እየደጋገመች የምትጮኸው?” ሲል ጠየቀ፤ አንደኛው መርማሪ።
“እንጃ” አሉ… ሌሎቹ።
ድመቷን እየገላመጡ። ፈለጓት። የለችም። ድምፁ ወደ ሚሰማበት አቅጣጫ ትኩረት ሲያደርጉ፣ የውሮ “ሚያው፣ ሚያው” እየጎላ መጣ። ከቤቱ አንደኛው ጎን ግድግዳ ውስጥ። ተጠግተው ሲያዳምጡ ውርዬ ትንፈራገጣለች።
“እንዴት እዚህ ግድግዳ ውስጥ ልትገባ ቻለች?” … ለዚህ ጥያቄ ማናቸውም መልስ አልነበራቸውም። ምንም ቢሆን ፍጡር ናትና ግድግዳው ፈርሶ በህይወት መውጣት ነበረባት።… እናም ግድግዳው ፈረሰ።
ውሮ ግን አልነበረችም።… ምን ተፈጠረ? መልሱን አላን ደላንፓ መጨረሻ ላይ ይነግረናል።
***
ወዳጄ፡- ሁለትና ሁለት ሲደመር አምስት ወይም ሶስት ይሆናል ማለት ስህተት ነው።… ከማህበራዊ ስምምነት ውጭ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም። የቁጥሩ ከፍና ዝቅ ማለት የጥፋቱ መጠን ላይ እንጂ የመርህ ወይም የእምነት ለውጥ አያመጣም። ስህተት ስህተት ነው።… ዶሮም ሆነ በሬ የሰረቀ ያው ሌባ እንጂ ሌላ ስም የለውም… እንደሚባው።
አንዳንድ ስህተቶች አጥፊውን ወይም የጥፋቱ በትር ያረፈበትን ሰው ወይ ነገር በተናጥል ሊጠቅሙ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ደሞዝ ከፋይ ወይም የባንክ ሰራተኛ በቁጥር ስህተት ትርፍ ገንዘብ ለማይገባው ሰው ቢከፍል ተከፋይ ሊጠቀም እሱ ሊጎዳ ይችላል። የባንኩ ሰራተኛ የጎደለ ገንዘብ ለደንበኛው ቢሰጥና ተከፋዩ ባለማወቅ ተቀብሎ ቢሰናበት ደግሞ እሱ ሲያተርፍ ደንበኛው ይጎዳል።
አንድ ሐኪም ለህመምተኛው ከመጠን ያለፈ ወይም ከመጠን ያነሰ መድሃኒት ቢሰጠው፣ (አድሚኒስትር ቢያደርግ) ጉዳቱ የአንድ ወገን ወይም የህመምተኛው ብቻ ነው። ለጠብ አጫሪነት፣ ለመኪና አደጋና ለጦርነት ምክንያት የሚሆኑ ስህተቶች ደግሞ ሁለቱንም ወገኖች ይጎዳሉ፣ የስህተቱ ጦር ሁለት ጫፍ አለው።
ተሰቡን፣ አካባቢውን፣ ማህበረሰቡን፣ አገርንና መላው ዓለምን ለማወክ ምክንያት የሚሆኑ ስህተቶችም ብዙ ናቸው፡፡ የእሳት ቃጠሎ፤ የደን ጭፍጨፋ፣ ለግላዊ ጥቅም የሚደረግ አደን እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎችን ከመዛመታቸው በፊት መከላከል ወይም በአጭር አለመግታት ከብዙ ጥቂት ምሳሌዎች ይሆናሉ፡፡
ወዳጄ፡- ተፈጥሮ ራሷ አንዱን አጭር፣አንዱን  ረጅም፣ አንዱን  ባለ ሙሉ አካል፣ አንዱን አካለ ጎዶሎ፣ አንዱን ሩቅ አሳቢ፣ አንዱን ተልካሻ ማድረጓ ስህተቷ ነው። የዕምነት ስህተትም አለ፡፡ አንዱ በሚታይና ውጤቱ በታወቀ የለውጥ ህግ ሲያምን፣ ሌላኛው ለጠንቋይና ለአማልክት ያጎነብሳል። ብዙዎች ደግሞ የስሜታቸው ተገዢዎች ናቸው፡፡ ለማያዩትና ለማያውቁት መንፈስ ይሰግዳሉ፡፡ መብታቸው ነው የኔ ልክ ነው፤ ያንተ ልክ አይደለም ከተባሉና ከተነታረኩ ወይም ጦር ከተማዘዙ ግን ተሳስተዋል ማለት ነው፡፡
የዘመናችን ታላቅ ስህተት ደግሞ እንደ ሌሎች ነገሮቻችን ሁሉ አለማወቅና ኋላ ቀርነት የፈጠሩት የፖለቲካና የአስተሳሰብ ሚዛን መዛባት ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ የምናውቃቸው የፖለቲካ ደርጅቶችና በወገናዊነት የተቃኙ መንግስታቶቻችን ስህተቶቻችን በመሆን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡
ወዳጄ፡- እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ብዙ ስህተቶች የተፈጠሩት ለወገንተኝነት ከፍተኛ ግምት ስለምንሰጥ ነው፡፡ ራስን ከፍ ማድረግ ክፋት የለውም፡፡ ክፋት የሚሆነው ራስን ከፍ አድርጎ በመገመት ውስጥ ሌላውን የማሳነስ ዓቅም እንዳለ አለመረዳታችን ላይ ነው፡፡ የደስታ ስሜት መቀነስና የመከራ ጎዳና ቁልቁለት፣ የሃዘንና ትካዜ ከፍታ ማሳያ ነው፡፡ ሃዘንና ትካዜ ሲቀንስ ዳግሞ ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ይሆናል። ስህተቶቻችን የሚደጋገሙት በፖለቲካም ሆነ በእምነት አመለካከትና ዝንባሌያችን ውስጥ ሁለቱን ተቃራኒ መንፈሶች ሚዛናዊ ለማድረግ ከመጣር ይልቅ ለአንድ ወገን ስናደላ ወይም ግላዊ ፍላጎታችንን ብቻ ለማዳመጥ፣ ራሳችንን  ዝግጁ ስናደርግ እንደሆነ ይመገታል፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ከስር ስር ካልታረመ፣ ወደ ዕድገትና ብልጽግና የሚደረገውን እርምጃ እያደናቀፈ ወደ መነሻችን ይመልሰናል፡፡ …..Back To Square One እንደሚሉት፡፡
ወዳጄ፡- ስህተቶች ሁሉ የየራሳቸው ድባብ አላቸው፤ ከሚፈጥሩት ቀውስ ጀርባ ሁሌም ምክንያት አይጠፋም፡፡ ለምሳሌ እንደኛው ባለ አገር፣ አንድ የተራበ ሰው ሆቴል ገብቶ ከተመገበ በሁዋላየሚከፍለው ገንዘብ ስለሌለው፣ ሊሮጥ ቢሞክር ተይዞ ሊደበደብ ወይም ሊፈረድበትና ሊታሰር ይችላል፡፡ ለዚህ ድርጊት መፈፀም ሁለቱም ወገኖች በቂ ምክንያት አላቸው። “ጥፋቱ የማን ነው?” የሚለው ጥያቄ ግን አልተመለሰም፡፡ ለነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ለመሰጠት፣ ሚዛናዊ ፍትህ ለማስፈን ማህበራዊ ስምምነት ያስፈልጋል፡፡
…..እንደ ሃሳብ፡፡ ምናልባት እንደ ልዩነት ሊቆጠር የሚችለው፣ በሂሳብ ህግ የሚገኘው ውጤት ደረቅ ዕውቀት ሲያረጋግጥ፣ ማህበራዊ ፍትህ ውስጥ ግን ለስላሳ ስሜት(common sense)           መኖሩ ነው፡፡
***
ወደ ታሪካችን ስንመለስ፡- መርማሪዎቹ ግድግዳው ውስጥ የድመት ድምጽ በተደጋጋሚ በመስማታቸው ውርዬን ለማዳን ግድግዳው እንዲፈርስ አደረጉ፡፡ ግድግዳው ሲፈርስ የተገኘው ግን የምስኪኗ ሚስት አስክሬን ነበር፡፡
ሠላም!


Read 1461 times