Saturday, 13 February 2021 10:55

“በትግራይ በተፈጠረው ነገር አዝናለሁ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን የህግ ማስከበር ሂደት አስመልክተው ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጡ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በዚሁ የማብራሪያ ፅሁፋቸው በትግራይ ጦርነት በመካሄዱ መከፋታቸውንና የተፈጠረው ሁኔታ እንደሚያሳዝናቸው፤ ነገር ግን ለዚሁ ሁሉ ተጠያቂው በህግ አልገዛም ያለው የህወኃት ቡድን መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በትግራይ የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻና ውጤቱ፣የሰብአዊ ድጋፍና የሰላም ጉዳይ ከጎረቤት ሃገራት ጋር ስላለው ወቅታዊ ግንኙነት ጠ/ሚኒስትሩ በስፋት አንስተዋል፡፡
 በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስት የተደረገው ኦፕሬሽን፣ የትግራይን ህዝብ ከመጥፎ አገዛዝ አላቆ ነጻነት ያጎናጸፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ለኢትዮጵያና በአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም መረጋጋትና የወደፊት መልካም እድል ነው ብለዋል በዚያው ልክ ስጋትም እንዳለ በመጠቆም፡፡
ሙሰኛና አምባገነን የነበረው ህወኃት መወገዱን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ለሀገሪቱ ህልውና ስጋት ሆኖ ከቆየው የብሔር ትምክህተኝነት ነጻ እንሆናለን፤ አንድነት፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ ያብባል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን በፅሁፋቸው ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዘር ልዩነት ምንጭና ዋነኛ ባለቤት የነበረውና የኢትዮጵያውያንን የእርስ በእርስ ግንኙነት በዘረኝነት የመረዘው ህወኃት ላይመለስ አብቅቶለታል ብለዋል
በህወኃት ላይ የተወሰደው እርምጃ በአለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ግርታንና ዘር ተኮር ጥቃት እየተፈፀመ ነው የሚል ብዥታን እንደፈጠረ የማይካድ መሆኑን ያመለከቱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው ለተጎጂዎች የሰብአዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና የዘር ተኮር ጥቃትም ጨርሶ አለመፈፀሙን አረጋግጠዋል፡፡
“እንደ ጠቅላይ ሚኒስተርና የጦር ሃይሎች አዛዥ የኔ የመጀመሪያ ሀላፊነት፣ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከውስጥም ከውጭም  ጥቃት መከላከል ነው” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ማንም መንግስት ቢሆን ወታደሮቹና ሰላማዊ ዜጎቹ እንደ ህወኃት ባለ ሃይል ጥቃት ቢፈፀምባቸው እጁን አጣምሮ አይቀመጥም ሲሉ የተወሰደው እርምጃ ተገቢና ማንም መንግስት ቢሆን ይህን ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በትግራይ በፍጥነት ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ነገር ግን ግጭቱና ተያይዞ የተከሰተው የሰዎች ሰላም ማጣትና ሞት በግሌ እኔንም አስከፍቶኛል፤ ሁሉም ሰላም ወዳድ ሰብአዊ ፍጡር ይሄን ስሜት ይጋራል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በትግራይ ፈጣን ሰላምና መረጋጋት በማምጣት በኩል አሁን እየተሳካልን ነው ብለዋል፡፡
በትግራይ ያለውን የዜጎች ሰቆቃ ማስወገድና በመላ ሃገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር የወቅቱ ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ነው ለተባበሩት መንግስታትና አለማቀፍ ረድኤት ድርጅቶች ችግሩን በጋራ እናቅልል የሚል ጥሪ እያቀረብኩ ያለሁት ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በትግራይ መንግስታቸው ቀን ከሌሊት በመትጋት አስፈላጊ ሰብአዊ ድጋፎች በማቅረብ እየታተረ መሆኑንና የሰብአዊ መብትን ለማረጋገጥም ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን በፅሁፋቸው አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ የህወኃት የቀደመ ማንነትና አላማ በስፋት ባብራሩበትና ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ባጋሩት ፅሁፋቸው፤ ህወኃት ገዢ ፓርቲ ሆኖ በስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያውያንን በብሄር ከፋፍሎ አጣልቷል፤ ይህ ፕሮጀክቱም ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተርፏል ብለዋል፡፡
 ከእነ እኩይ አላማው ላይመለስ በተሸኘው የህወኃት ፍርስራሽ ላይም ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግደው አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንባት ራዕይ ይዞ መንግስታቸው እየሰራ መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
በሃገር ውስጥም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚመለከት ስርዓት ከመፍጠር ባሻገር በህወኃት ተበላሽቶ የነበረውን የጎረቤት ሃገራት ግንኙነት በድጋሚ የማስተካከል ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውንም ዶ/ር ዐቢይ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲሰፍንና ቀጠናው እንዲረጋጋ አበክራ ትሰራለች ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ይህን ለማረጋገጥም ከጎረቤቶቻችንና ከዓለማቀፍ  ማህበረሰብ ጋር እንሰራለን ብለዋል- ለዓለም ባሰራጩት ዘለግ ያለ ጽሁፋቸው፡፡

Read 1330 times