Print this page
Saturday, 13 February 2021 12:13

ከሯጭ ፈረስ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከእለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ተሰብስበው ድግስ ለመደገስ ያስቡና የድግሱን እቃ ግዥ የሚያሳኩ እጩዎችን ለመምረጥ ይወያያሉ። በመጀመሪያ በአያ አንበሶ ጥያቄ ሰጎን ስሟ ተጠቀሰ። እመት ጦጢት ሃሳብ ሰጠች፡-
“ሰጎን ለሩጫና ለሽቅድምድም ትመቻለች፤ ነገር ግን የእቃ ግዥነት ልምድ የላትም፤ ስለዚህ ሌላ ተመራጭ እንጠቁም” አለች።
ቀጥሎ ዝሆን ሀሳብ  ሰጠ፡-
“እንደ እኔ እንደ እኔ ጦጢት የምትሻል ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ገበያውን ስለምታውቅ የተሻለ እቃ ግዥ ትሆነናለች”
ቀጥሎ ዝንጀሮ ተነሳና:-
“ጦጢት ብልጥ ናት እንጂ የምግብ ዓይነት ምርጫዋ ውስን ነው፤ ስለዚህ ነብርን ብንልከው ያዋጣናል”
አያ ጅቦ ቀጥሎ ሃሳቡን ገለጠ:-
“አያ ነብሮ ጥሩ ምርጫ አይመስለኝም፤ እሱ ስጋ በል ስለሆነ ስጋ ያሳሳዋል። ስለዚህ ስጋ በሎቹንና ቅጠል በሎቹን ያምታታቸዋል። በእኔ እምነት ዔሊ ሄዳ ገዝታ ብትመጣ ያዋጣናል እላለሁ”
በአያ ጅቦ ሃሳብ አብዛኛዎቹ እንስሳት ተስማሙና ዔሊ ወደ ገበያ ተላከች። ጥቂት ሰዓታት እንዳለፈ አውሬዎቹ ማጉረምረም ጀመሩ። ረሃቡ ጠንቶባቸዋል።
“ድሮም ዔሊን መላካችንና ይቺን ቀርፋፋ መልዕክተኛ ማድረጋችን ትልቅ ስህተት ነው። ገና እየተንቀረፈፈች ደርሳ እስክትመለስ ድረስ ሁሉም በርሃብ ሊሞት ይችላል; አሉ።
ለካ ዔሊ ገና አልተንቀሳቀሰችም ኖሯል። አንገቷን በበሩ ብቅ አድርጋ፡-
“እንደዚህ የማታምኑኝ ከሆነ እንደውም ከነጭራሹ አልሄድም” አለች፡፡
*   *   *
የሀገራችን የሰው ሃይል ምጣኔና ምርታማነት መለኪያ ከሆኑት መስፈርቶች አንዱ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ  ነው። (The right man at the right place) የሚባለው ነው። የተማረ የሰው ሃይልን በወጉ አለመጠቀም ትልቅ በደል ነው። በአንጻሩም የተማረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ እውን በአግባቡ ተምሯል ወይ ብሎ መጠየቅም ያባት ነው።
የተማረው ክፍል አገሬን እወዳለሁ እንዲልና ምን ጎድሎባታል? ምንስ ሞልቶላታል? እኔ ምን አስተዋጽኦ ላድርግ? ብሎ እንዲጠይቅ ማድረግ ተገቢ ነው። የቀድሞው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፡- “ሀገሬ ምን ታደርግልኛለች ከምትል እኔ ለሀገሬ ምን ላድርግላት በል” ብለው ነበር። የህዝቡን የትምህርት ስርዓቱን መመርመር፣ ከተቻለም በየጊዜው መፈተሽ ዋና ነገር ነው። ምንግዴነትን ማስወገድ ያሻል። አንድ የሀገራችን ገጣሚ እንዳለው፡-
“እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ
 እሱ ነው ያረዳት ሀገሬን እንደ በግ
ብዬ ግጥም ልጽፍ ተነሳሁኝና
ምናገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና”
እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። አንድም የምርጫ ዘመን እየመጣ ነውና ትክክለኛውን ተመራጭ አንጥሮ በአግባቡ መምረጥ፣ ለሀገርና ለህዝብ ሁነኛ እርምጃ እንደሚሆን ከወዲሁ እንገንዘብ።
አይሰግሩም ተብሎ ፈረስና በቅሎ
አይሮጡም ተብሎ ፈረስና በቅሎ
እንደው በጥላቻ
ትመረጥ ይሆናል ዔሊ ለኮርቻ
የሚለውንም ሀገርኛ አባባል አለመዘንጋት ነው። ትክክለኛና አግባብነት ያለውን ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊነቱን በተለይ ከዲሞክራሲ መጎልበት አንፃር ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ለዓመታት ስንናገር ቆይተናል። ሆኖም ነቢብ ወገቢር እንዲሉ፣ እስከዛሬም ለግብሩ አልበቃንም። ገና ብዙ መንገድ መጓዝ ይጠበቅብናል። ይህም በፈንታው ትክክለኛውን አቅጣጫ ማወቅንና መምረጥን ግድ ይለናል። ከሯጭ ፈረስ ይልቅ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች የምንለው ለዚህ ነው።

Read 14843 times
Administrator

Latest from Administrator