Monday, 15 February 2021 00:00

የአለማችን አጫሾች ቁጥር ከ1.8 ቢሊዮን ማለፉ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሲጋራ ሳቢያ ለሞት ይዳረጋሉ

            በአለም ዙሪያ የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር ከ1.8 ቢሊዮን ማለፉንና በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማጨስ ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ አናዶሉ ኤጀንሲና ታዋቂው የሳይንስ መጽሔት ባወጡት ዘገባ ገልጸዋል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ በአለማችን ከሚገኙት 1.8 ቢሊዮን ያህል አጫሾች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ባላደጉ ወይም በማደግ ላይ ባሉ ድሃ አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ከማጨስ ጋር የተያያዙ የሞት አደጋዎችም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚከሰቱ ናቸው፡፡
እድሜቸው ከ15 አመት በላይ ከሆናቸው የአለማችን ወጣቶች መካከል 21.9 በመቶው አዘውትረው የሚያጨሱ መሆናቸውንና ከአጫሾች ዙሪያ በመገኘታቸው ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥርም 1.2 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ በመላው አለም ከሚገኙት ህጻናት መካከል 40 በመቶ ያህሉ ከአጫሾች አጠገብ በመሆናቸው ብቻ ለጤና ችግር እንደሚጋለጡና፣ በየአመቱ ለሞት ከሚዳረጉት ህጻናት መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት ከአጫሾች አጠገብ በመሆናቸው ለሞት የሚዳረጉ ስለመሆናቸውም አክሎ ገልጧል፡፡
47.4 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿ ሲጋራ የሚያጨሱባት ኪሪባቲ ከአለማችን አገራት ከህዝብ ብዛቷ አንጻር ብዙ አጫሾች የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ በሞንቴኔግሮ 46 በመቶ፣ በግሪክ 43.7 በመቶ ዜጎች እንደሚያጨሱም አክሎ ገልጧል፡፡
ላሰንት መጽሄት በበኩሉ፤ አገራት የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስዱም ከአለማችን አገራት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት ለውጥ ለማስመዝገብ አለመቻላቸውን ዘግቧል፡፡
ትንባሆ በውስጡ 7 ሺህ ያህል ጎጂ ንጥረ ነገሮች እንዳሉትና 250 ያህሉ ሰውነትን ክፉኛ የሚመርዙ፣ 50 የሚሆኑት ደግሞ ለካንሰር የሚያጋልጡ መሆናቸውንም ዘገባው ሃኪሞችን ዋቢ በማድረግ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

Read 2737 times