Sunday, 21 February 2021 17:41

ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንኡ (ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን አጽኑ)

Written by 
Rate this item
(7 votes)


           የሚከተለው ትርክት የአረቦች ተረት ነው።
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ንጉስ፣ ሶስት በእስር ላይ ያሉ ፈላስፎቻቸውን አስጠርተው፤  “መልካም ሃሳብ ያለው ፈላስፋ ሽልማቱ መፈታት ነው፤ እስኪ ተአምር ነው የምትሉትን ሃሳብ ንገሩኝ፤ ታላቅ ተዓምር የነገረኝን ሰው እሸልመዋለሁ” አሉ።
አንደኛው ፈላስፋ፡- “ይሄን ፈረስዎን ሌጣውን እጋልበዋለሁ” አለ።  
ሁለተኛው ፈላስፋ፡- “ይሄን ፈረስዎን ሳር እያበላሁ እያማለልኩ፣ እየጋለብኩ፣ ከየትኛውም ፈረስ ቀዳሚ አደርገዋለሁ” አለ።
ሶስተኛው ግን፡- “እኔ ደግሞ ቋንቋ አስተምረዋለሁ” አለ።
ሁለቱ እስረኞች በመገረም፤ “አብደሃል እንዴ? እንዴት አድርገህ ነው ፈረሱን ቋንቋ አስተምረዋለሁ ብለህ ለማለት የደፈርከው?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡  
ሶስተኛው ሰውዬ፡- “ሶስት መንገዶችን አስቤ ነው። አንደኛ ወይ ፈረሱ አማርኛ አይገባውም ብዬ እከራከራለሁ፤ ሁለተኛ ወይ አማርኛ ገብቶት አንድ ቀን ይናገራል፤ በመጨረሻም  ወይ ንጉሱ ይሞታሉ። በመካከል እኔ ለራሴ ጊዜ እገዛለሁ አለ” ይባላል።
*   *   *
ጊዜ መግዛትን የመሰለ ነገር የለም። ማምሻም እድሜ ነውና። ዋናው ነገር ደግሞ ያንን ዕድሜ ምን እንሰራበታለን የሚለው ነው። የሚባክነው እድሜ ከበዛ በሕይወታችን ላይ መሳለቅ ነው። የዛሬውን ህይወት ማባከን አይደለም፣ ከነገ ላይም መስረቅ ነው የሚጠበቅብን። (Plagiarize the future እንዲሉ) ለእድገት አንዱ መሰረቱ ለነገ መሰረት መጣል ነው። ከመነሻው ያላማረ አብዛኛውን ጊዜ መድረሻው ያማረ አይሆንም። የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ አይነት ነው። (The end justifies the means) የሚባለውን አይዘነጉም።
የሀገራችን ፖለቲካ ቶሎ ተናኝ (Volatile) ነው፤ በቶሎ ይግላል፤ በአንድ አፍታ ይቀዘቅዛል። ፖለቲከኞቻችንም እንደዚያው ተናኝ ናቸው። በሰላሙ ጊዜ አይዘጋጁም። ሁኔታዎች ከተወሳሰቡ በኋላ መደነጋገር ስራቸው ነው። ይህ ደግሞ ዳፍንተኝነትን ያስከትላል።
የሀገራችን ኢኮኖሚ ለያዥ ለገራዥ ማስቸገሩ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። መላ እመታበታለሁ፣ ዘዴ እዘይድበታለሁ ያለ ምሁር ነጋዴው፣ አዋቂው፣ አላዋቂው፣ ብልጡም የዋሁም እኩል ይደነጋገራል።
ስለዚህም የወል ማሀይምነት ጽናትም ያስፈልገዋል። ጽናቱ ለእቅድ፣ ጽናቱ ለዘላቂነት ይበጃል። ወጣም ወረደም ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንኡ የሚለውን በኃይለ ስላሴ ጊዜ ይሰጥ በነበረው ዲግሪ ላይ እንደ መፈክራዊ ምክር የሚቀመጠው ሃምሳ ዓለቃዊ አነጋገር፣ ለዛሬም አግባብነት ያለው መሆኑን እንረዳ። “ሁሉንም ሞክሩ፤ የተሻለውን አጽኑ” የምንለው ዛሬም፣ እንደሚሠራ ስለምንረዳ ነው!  


Read 15098 times