Sunday, 21 February 2021 17:26

የሚዲያ ነጻነት ሲገደብ ሙስና ይንሰራፋል!

Written by  በለው አንለይ
Rate this item
(4 votes)

 "--በምርመራ ጋዜጠኝነት አማካኝነት በየአገራቱ ለህዝብ ከቀረቡ በርካታ ስራዎች መካከል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ሪቻርድ ኒክሰንን ለስልጣን ስንብት ያበቃውና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የወጣው ጽሑፍ “የወተር ጌት ቅሌት” በስፋት ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡--"
             
             ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሃርመኒ ሆቴል፤ ፀረ-ሙስና ላይ ያተኮረ አንድ ወርክሾፕ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ “መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነትን በማስፈን ሙስናን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚታገሉ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጎልበት” በሚል ርዕስ በትራንፓረንሲ ኢትዮጵያ አማካኝነት የተሰናዳ ሲሆን ፕሮጀክቱ፤ ለሶስት ዓመት የሚቆይና በአውሮፓ ሕብረት (Civil Society Fund III) የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ነዉ፡፡
ትኩረቱን ሙስናን መከላከል ላይ ያደረገዉ ፕሮጀክቱ፤ ባለድርሻ አካላት ብሎ ከለያቸዉ መካከል አንዱና ዋናው መገናኛ ብዙኃን ናቸዉ፡፡ መገናኛ ብዙኃንን እንደ አንድ ሁነኛ ሙስናን መከላከያና መመርመሪያ መሳሪያ አድርጎ በመውሰድ፣ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር አብሮ ለመስራት ያሳየው ተነሻሽነት የሚደነቅ ነዉ፡፡ በእርግጥም መገናኛ ብዙኃን ሙስናን በመከላከል፣ በማጋለጥና የህዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ የማይተካ ሚና የሚጫወቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ናቸዉ፡፡ የአገራችን መገናኛ ብዙኃን ሙስናን በመከላከል ረገድ ሚናቸዉ ዝቅተኛ እንደሆነ በዕለቱ የመክፈቻ ጥናት ያቀረቡት አቶ ሰለሞን ጎሹ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙኃን አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ (ከህግ፣ ከመዋቅርና አደረጃጀት አንጻር) ሙስናን ከመከላከል ይልቅ የራሳቸውን ህልውና ጠብቀው ለመቆየት የሚታገሉ ናቸዉ፡፡ በአገራችን ጠንካራ መገናኛ ብዙኃን ይኖሩ ዘንድ ከምንም በላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ በወርክሾፑ ተሳታፊዎች ዘንድ አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡  
ሙስና በአገርና ህዝብ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ለማጤን የግድ የጥናት ማህደር ማገላበጥ አስፈላጊ አይመስለኝም። አሁን ላይ አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጦችን በማየት ብቻ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ሙስና ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል ሲሆን በተለያዩ መስኮች ሊገለጽ ይችላል፡፡ ጉቦን ጨምሮ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውውር፣ የመንግስት ግዥ፣ ግብርና ታክስ፣ የኮንስትራክሽን ስራዎችና የመሳሰሉት ዋና ዋና የሙስና መንስኤዎች ናቸዉ። ሙስና የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ በመንገዳችን ላይ የወደቀ ትልቅ እንቅፋት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአንድ ወቅት እንዳሉት፤ ሙስና የዜጎችን እምነት የሚገድል፣ ስራ ፈጠራን የሚያዳክምና የሚያጠፋ ካንሰር ነዉ፡፡ አገራችን አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ ሙስና የነበረው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ ነ። ሙስናን ለመከላከል መወሰድ ያለበት እርምጃ ሁሉ መወሰድ አለበት፡፡ ለአብነት ያህል በትግራይ ክልል የተካሄደዉ ህግን የማስከበር ዘመቻ፣ ሙስናና ዘረፋን የመከላከል አንዱ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነዉ፡፡
ሙስናን መከላከያ ዋናው መንገድ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ግልጽነት ሲነሳ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት የማይረሳ ጉዳይ ነዉ፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ መገናኛ ብዙኃን የማይተካ ሚና አላቸዉ፡፡ መገናኛ ብዙኃን የህዝብን አስተያየት፣ አመለካከትና ስሜት  የሚለኩ ባሮሜትር እንደደመሆናቸዉ መጠን፣ በነጻነትና በኃላፊነት ስሜት መስራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለነገ የሚባል ስራ አይደለም፡፡ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የመከላከሉ ጥረት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የተጠናከረ የሚዲያ ነጻነት ሲኖር፣ ሲጎለብትና ሲስፋፋ ብቻ ነው፡፡ በአንጻሩ የመናገርና የፕሬስ ነጻነት መብት ሲገደብ ሙስና በእጅጉ ይንሰራፋል፡፡ ነጻ ሚዲያ፤ የነጻ ሀሳብ መድረክ ከመሆኑም በላይ ዜጎች በመንግስት አሰራርና አመራር ላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ የሆነ ሚና ይጫወታል፡፡ የሚዲያ ነጻነት ለማንኛውም አገር ዲሞክራሲ ዋናው የደም ስር ነዉ፡፡ ተወያይቶ መምረጥ፣ ተሰብስቦ መቃወም/መደገፍ፣ ማምለክ፣ ህግ ለሁሉም የቆመች ስለመሆኗ ማረጋገጥ፣ ወዘተ ሁሉም ተግባራዊ የሚሆኑት ወከባ፣ ማሳደድና ተአቅቦ ያልተደረገበት የመናገርና የመረጃ ልውውጥ መብት ሲሰፍን ብቻ ነዉ፡፡ “የነጻነቶች እናት” በመባል የሚታወቀው የአመለካከትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እስካልጎለበተና እስካልተስፋፋ ድረስ፣ ሙስና ለአገራችን ዕድገት እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ሆኖ ይቀጥላል፡፡
በተለይ ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችሉ ሥራዎች ተብለዉ ከሚታወቁት ሶስት ስልቶች (የመከላከል፣ የመመርመርና የመክሰስ) ዉስጥ የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ ከፍተኛ ነዉ፡፡ ለዚህም የምርመራ ጋዜጠኝነት (investigative journalism) ላይ ትኩረት በማድረግ ሙስናንና ሙሰኞችን ለህዝብ ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት የተደበቀ ምስጢርን ይፋ በማድረግ፣ ስውር ሴራን በማጋለጥ፣ በህዝብና በአገር ጥቅም ላይ የሚወጠኑ ጥፋቶችን ለአደባባይ በማብቃት፣ ህዝባዊ ፍርድ የሚያስገኝ ተግባር ነው፡፡ በምርመራ ጋዜጠኝነት አማካኝነት በየአገራቱ ለህዝብ ከቀረቡ በርካታ ስራዎች መካከል የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ሪቻርድ ኒክሰንን ለስልጣን ስንብት ያበቃውና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ የወጣው ጽሑፍ “የወተር ጌት ቅሌት” በስፋት ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ሚና አዳዲስ ሁኔታዎችን ተከታትሎ የሚያሳውቅ የመረጃ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የመንግስት ሹማምንት ወንበራቸውን መከታ አድርገው የሚፈጽሟቸውን ሙስናና የስልጣን ዋልጌነትን የሚመረምርና የሚያጋልጥ የህዝብ ጠበቃ ነዉ፡፡
 ከዚህ በተጨማሪ ነጻ ሚዲያ፣ የመንግስት ሹማምንት በስልጣናቸው አላግባብ እንዳይጠቀሙ የሚቆጣጠር፣ መንግስት ከህዝብ የተቀበለውን አደራና የተሸከመውን ኃላፊነት በትክክል እንዲወጣ የሚጠብቅ፣ ህዝብ መብትና ግዴታውን እንዲያውቅ የሚያደርግና በመንግስትና በህዝብ መካከል የተለያዩ አመለካከቶችና ሀሳቦች በነጻ እንዲንሸራሸሩ የሚያስችል የመንግስትና የህዝብ አስተያየት መገኛ መሳሪያና አገናኝ መድረክ ነዉ፡፡   
የፀረ ሙስና ትግሉ ጠንካራ አለት ላይ እንዲገነባ፣ የመንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ደጋግሞ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን የተጣለባቸውን ህዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጡ ዘንድ ከመንግስት ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ተጽዕኖ፣ ነጻና ለመረጃ ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ ሁሉም የመንግስት ባለስልጣን፣ ህዝቡ፣ የመንግስትን ስራ ለማወቅ ያለውን መብትና የመንግስት ባለስልጣናት ያለባቸውን የተጠያቂነት መርህ በመከተል፣ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው ህጉ ይደነግጋል፡፡

Read 1654 times