Monday, 22 February 2021 07:21

“ሰዓሊው ለአገሩ እንደሚያስፈለግ ከታመነ መደገፍ አለበት”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ምስጢር ማውጣት መጠቆም አይደለም
ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ፤ የ1ኛ ዓመት ምስረታ በዓሉን ባለፈው ሰሞን አክብሯል፡፡ ከቦብ ማርሌይ 76ኛ ዓመት የልደት መታሰቢያ ጋር የተያያዘው የኦዳ ክብረ በዓል፤ ‹‹እንዋሃድ›› በሚል መርህ በልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች የታጀበ ነበር፡፡
ሰዓሊዎች የአፄ ምኒልክ፤ የአፄ ኃይለስላሴን፤ የዶክተር መላኩ በያን፤ የቦብ ማርሌይን፤ የማርከስ ጋርቬይን፤ የማንዴላን፤ የፌላ ኩቲ እና ሌሎችን አንጋፋ ሰብዕናዎችን  ምስሎች ሰርተው በመታሰቢያነት አቅርበዋል። በመደመር ካንቫስ አዲስ አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ትልልቅ የጥበብ ስራዎች  በፍሬሞች ተወጥረው ተጎብኝተዋል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በተለያዩ ሰዓሊዎች የተሰሩ ግዙፍ የስነጥበብ ውጤቶችም በየስቱድዮው ለጎብኝዎች ቀርበዋል፡፡  ከኢትዮጵያ የዓለም ፌደሬሽን የተጋበዙ የ”ድራምስ ኦፍ ራስተፈርያን” አባላት የሙሉ ሰዐት የከበሮ ጨዋታ ፤ ፀሎት እና አነቃቂ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ቱርካዊና ኢትዮጵያዊት ሙዚቀኞች በጋራ የቦብ ማርሌይንና የራሳቸውን አዲስ የሙዚቃ ስራዎች ተጫውተዋል፡፡
‹‹ምስጢር ማውጣት መጠቆም አይደለም፤ መዋሐድ ነው፡››
ኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበብ  ስፍራ፤ 1ኛ ዓመቱን ባከበረበት ዋዜማ ላይ፤ ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው፤ የኢትዮጵያ ጎማ ቁጠባ ምክትል ስራ አስኪያጅ፣  ረዳት ፕሮፌሰርና ሰዓሊ ጎሳ ገብረስላሴ፣  ጥሪ ለተደረገላቸው የሚዲያ ተቋማት ልዩ መግለጫ ሰጥቷል፡፡  ‹‹የጎሳ ምስጥሮች›› በሚል  ርእስ   መግለጫውን  የጀመረው  ዋሽንቱን በመጫወት ነው ለጥሚና በሚል   ‹‹ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን እያፈረሱ ነው፡፡ ለምን? ባህላቸውን እያፈረሱ፤ መገበያያ ገንዘባቸውን እያፈረሱ፤ ዶላር እያመለኩ፤ ህንፃ እያመለኩ ነው፡፡ ለምን? … ጭንቅላታችን ምንድነው የሆነው?... ተው ስማኝ ተው…ስማኝ አገሬ? ችግር የለም አንበል፡፡ በሙሉ ጭንቅላታችን ችግር ውስጥ የተቀበርን ነን፤ ችግር የለም ማለት አደንዛዥ እፅ ነው፡፡ ችግር ብቻ ነው ያለው፤ ከመጀመርያ እስከመጨረሻ። የሰላሙን የመፍትሄውን መንገድ ያምጣልን፤ አንጎላችንን ይከፈትልን ›› ሲልም መልዕክት ያዘለ ዜማ አሰምቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ጀመረና ጋዜጣዊ መግለጫውን የጀመረው። መግለጫውን ‹‹የጎሳ ምስጢሮች›› በሚል የሰየመበትን ምክንያት አብራራ፡፡ ስሙ ጎሳ እንደሚባል፣ በሚዲያም ብዙ የሚጠራ ቃል እንደሆነ ከጠቀሰ በኋላ፤ ‹‹ በአብዛኛው የራሴ ምስጢሮች ናቸው ሲል አስረዳ፡፡ “ምስጢር ለመናገር ለምን ያስፈልጋል? ለምን ያስፈራል? ስም በማጥፋት ስለሚያስከስስ ይሆናል፡፡ ምስጢሮች ሲባል… የመቼዎቹ ምስጢሮች ይነገራሉ? የትኞቹ ይከለከላሉ፤ አይነገሩም?። እንደ ጎሳ የምፈልገው ሁሉንም ለመናገር ነው፡፡ ግን አይቻልም፡፡ ሰዎች ድርጅቶች ይቀየማሉ፡፡ ማስቀየም ደግሞ መጥፎ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሰዓሊና የስነጥበብ ሰው ስለሆንኩኝ፤ መግለጫዬን የጎሳ ምስጢሮች ብየዋለሁ፡፡ መደመር የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ እወደዋለሁ፡፡ 1ኛ ዓመታችንን ስናከብር  “እንዋሐድ” ብለናል። ለመደመር ለመዋሃድ ካስፈለገ፣ እውነት መውጣት አለባት፡፡ እውነት ተደብቆ የሚሆን ነገር የለም፡ ምስጢር ማውጣት መጠቆም አይደለም፡፡ መዋሐድ ነው። መደመርን ካነሳን፤ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ምስጢር ተነግሮ ነው ወይስ ተደብቆ መደመር የሚቻለው። ከባድ ምርጫ ነው፡፡ ዝምታ መንቀዝን ይጨምራል፤ መናገር ቅያሜን ይፈጥራል፡፡ ምን ይደረግ? ቀስ በቀስ አንዳንዴ  ትንሹን፣ አንዳንዴ  ትልቁን  መናገር ነው፡፡ አንዳንዴ በስዕል ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መፃፍ፡፡ ይሄ የመደመር ካንቫስ አሰራር ነው። እኛ አንድ ላይ ሆነን የፈጠርነው ይህን የአስተሳሰብ መንገድ ነው፡፡›› ሲል አስረዳ፡፡
የጎሳ ምስጢሮቹ የተባለው መግለጫ  በሶስት አበይት አጀንዳዎች ላይ አያተኩሯል፡፡ በፍትህ ስርዓቱ፤ በባንኮች አሰራርና  በስነጥበብ ኢንዱስትሪው፡፡ ሁሉንም ባይሆን በጥቂቱ እንዳስሰዋለን፡፡ በመጀመርያ ያነሳው በፍትህ ስርዓቱ የገጠመውን እክል  ሲሆን ‹‹እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጭንቅላቱን መፈተሽ አለበት፡፡ እኛ አገር የሚያስፈልገን የጭንቅላት ለውጥ ነው፡፡ አለበለዚያ በስብሰን ነው የምንቀረው፤ ጭንቅላታችንን ካልቀየርን ተስፋ የለንም፡፡“ሰው ጭንቅላቱን መቀየር ያለበት ፍትህን በገንዘብ መሸጥ ነውር መሆኑን በመረዳት ነው” በማለት፤ ፍትህን በገንዘብ መፈለግ፤ ማሰብ የለብንም ሲል አጥብቆ መክሯል፡፡
ሌላው የጎሳ ምስጢር   የባንኮችን አሰራር የሚዳስስበት ነው፡፡ ‹‹የባንክ ምስጢር ብዙ ነው፡፡ የባንክ ቦርድ ሆኜ ሰርቻለሁ አውቀዋለሁ፡፡ በባንኮች አሰራር የኢትዮጵያ ብር እየተገደለ፤ ከየት ነው ብልፅግና የሚመጣው፡፡ በባንክ አሰራር ውስጥ ስለ ዶላር የሚያማክሩት ሁሉ በዶላር የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ብር እየሞተ፣ ዶላር እየበለፀገ የሚገኘው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ዶላር ስምንት ብር ነበር፤ አሁን ከአምስት እጥፍ በላይ አድጎ፣ ከ40 ብር በላይ ሆኗል። የውጭ ንግድ አድጓል፡፡ ኢንቨስትመንት ጨምሯል ይባላል፤ ግን ውሸት እየተደጋገመ ነው፡፡ ስለዚህም ባንክን የሚመሩ ራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡
ከሰሞኑ የጎማ ቁጠባ ዋና መስርያ ቤት የፈረሰበትን ሁኔታም ሲያስረዳኝ፤ ‹‹ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ አሜሪካ ለ20 ዓመታት ስኖር በፍፁም ዜግነቴን አልቀየርኩም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፤ ጎማ ቁጠባ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ነው፤ ይሄ የሚያጠያይቅ አይደለም። የመሰረቱት አባቴ አቶ ገብረስላሴ ኦዳ እና ወንድማቸው አቶ ገብረየስ ኦዳ ናቸው፡፡ የእነሱን ኢትዮጵያዊነት የሚጠራጠር ካለ ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ ፋብሪካው  በቀዳማዊ ሃይለስላሴ በኢንዱስትሪ ሽልማት የተቀበለ ነው፡፡ ሰሞኑን የፈረሰው የኦዳ ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ተወልደን ያደግንበት ነው፡፡ ለኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአክሲዮን ኢንቨስትመንት ነው ተብሎ ንብረቱን ሰጠን፡፡ ይህ ሁኔታ ተቀልብሷል፡፡ ንብረቱን የቀየርነው በአክሲዮን ነበር፡፡ ዋና መስሪያ ቤቱም ፈረሰ፡፡ ከኦሮሚያ አክሲዮንም ሆነ ከንብረቱ ሳይሆን ጎማ ቁጠባ ባዶ እጁን ቀረ፡፡ በስፍራው 3.5 ቢሊዮን ብር ወጥቶ የባንክ ህንፃ ሊገነባ ነው። ምንድነው የሚጠቅመው? የኢትዮጵያ መንግስት ባንኮችን መፈተሽ አለበት፡፡ ባንኮች እኛ አገር ገንዘብ ይወስዳሉ፡፡ ምን ያደርጋሉ? ፎቅ ይሰራሉ፡፡ ፎቁ ስንዴ አመረተ?› ሲልም በመገረም ይጠይቃል፡፡
“በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያለው ምስጥር የሚሰሩትን አያውቁም፤ መቆጣጠር አያውቁም፡፡ የግል ባንኮች አክሲዮን ለውጭ አገር ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሸጥ በመመርያ ተከለከለ፡፡ አፈፃፀም ላይ ቼክ ተደርጓል ወይ? የሸጠው አልተቀጣም፤ የገዛው ነው የተቀጣው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ያስቀጣል? የኢትዮጵያ ጎማ ቁጠባ ኃ/የተ/የግ/ማህበር፣ ንብረቱን በአክሲዮን ሲቀይር የማህበሩ አባላትን ፓስፖርት የጠየቀ አልነበረም፡፡  ከምስረታቸው ጀምሮ ፓስፖርት ሳይጠየቁ  ለብዙ አመታት ሸጡ። የሆኖ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ መመርያ ነው ተብሎ  ጎማ ቁጠባ ንብረቱንም አክሲዮኑንም አጣ፤ ጎማ ቁጠባ ኢትዮጵያዊ ድርጅት አይደለም ተብሎ እንዴት ይበየናል?” ሲል ጥሪ ለተደረገላቸው የሚዲያ ባለሙያዎች ደረሰብን ያለውን አስረድቷል፡፡
ባለፈው ሰሞን ሰንጋ ተራ አካባቢ የነበረው የጎማ ቁጠባን የሽያጭ ክፍል  ባልተጠበቀና የፋብሪካውን ፈር-ቀዳጅ ታሪክ ባላከበረ ሁኔታ እንዲፈርስ ተደርጓል፡፡  በመጀመርያ ደረጃ በፋብሪካና  አምራች ኢንዱስትሪ ደረጃ ለኢትዮጵያ ያስተዋወቀ ኩባንያ መሆኑ ትልቅ ቁምነገር ሆኖ መታየት ነበረበት፡፡ የኢትዮጵያ ጎማ ቁጠባ ስራ፣ በታሪክ የመጀመርያው በኢትዮጵያውያን የተመሰረተ አንጋፋ የግል ኩባንያ ሲሆን በኢንቨስትመንት መስኩ  65 ዓመታትን የተጓዘ ነው።
 በሰበታ ከተማ ዲማ ላይ የኢትዮጵያ ጎማ ቁጠባ ዋና ፋብሪካ የሚገኝ ሲሆን ለስነጥበብ መጠጊያ ሆኖ የቆየ፤ በተለይ ለሰዓሊና ቀራፂ ተስፋሁን ክብሩ በሩን ክፍት በማድረግ   በብረታ ብረትና የጎማ ተረፈ ምርቶች ታላላቅ የጥበብ ስራዎች እንዲከናወኑ ምክንያት ሆኗል። ከስነጥበብ  ባለሙያዎች ጋር በመተሣሠር፣ አዳዲስ ምዕራፎችን የከፈተም ነው።  በአጠቃላይ ለኦዳ መደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ መመስረት፣ የኢትዮጵያ ጎማ ቁጠባ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ ነው፡፡ የስነጥበብ ስፍራው አሁን የሚገኘው በኦአይቢ ኦዳ ሪልስቴት (OIB ODA REALESTATE) ይዞታ ላይ ሲሆን ከሰሞኑ በተፈጠሩ ሁኔታዎች  የሚደናቀፍ ነገር አለመኖሩን፤ በጎማ ቁጠባ በኩል ስነጥበብና ኢንዱስትሪ ተጣምረው መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ገልጸዋል ‹‹ እኔ የምፈልገው ሌላው ሰው የሚፈልገው ላይሆን ይችላል። እንደ ጎሳ የማምነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ፎቅ መገንባት አንገብጋቢ  አይደለም። የፎቆች ግንባታ ሚዛኑን ጠብቆ፣ በአረንጓዴ ልማትና በሰው ሃብት ልማት ላይ መስራት ይኖርብናል። ኦዳ መደመር አፍሪካ  የስነጥበብ ስፍራ የጀመረው እንቅስቃሴ በመላው አዲስ አበባና ኢትዮጵያ እየሰፋ መቀጠል አለበት። ራዕያችን የስነጥበብ ስፍራው የሚገኝበት የኦአይቢ ኦዳ ሪልስቴት ንብረት፤ ጎማ ቁጠባ የተመሰረተበት አካባቢ፤ ዙረያገባውን ያሉት የትልልቅ የሚዲያ ተቋማት ቦታዎችን በሚያካልል ሁኔታ ሰፊ የስነጥበብና ሚዲያ ማዕከል ለአዲስ አበባ እንዲፈጠር ነው›› ሲልም አብራርቷል፡

Read 2356 times