Thursday, 25 February 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነት ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(9 votes)

  https://youtu.be/VUboFMARdW8?t=330

"--የማይካድራውን ዘግናኝ ድርጊት ስሰማ ግን ለራሴም መፍራት ጀመርኩ፡፡ ምናልባት ህወሓት በመቀሌ አቅራቢያ የሚሸነፍ ከሆነ፣ የመጨረሻ ዕድሉን ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ መቀሌ መጥተው የሚኖሩትን ዜጎች ሰብስቦና መትረየስ ደቅኖ፣ መከላከያ ከትግራይ እንዲወጣ ወይም ደግሞ ወደ ድርድር እንዲመጣ ለማስገደድ ይጠቀምብን ይሆን ብዬ ፈራሁ፡፡--"
             
          ክፍል 3፡ መከላከያን ሰንጋ በሰንጋ ያደረገው ንግግር
ወርሐ የካቲት ላይ ነው ያለነው፡፡ የካቲት ደግሞ ለህወሓት ትልቅ ትርጉም ያላት ወር ናት፡፡ እናም ወደ ዛሬው የሰሜኑ ጦርነት ትረካዬ ከመሄዴ በፊት ስለ የካቲት 11 የህወሓት የልደት በዓል ትንሽ ላውራ፡፡
የጥቅምት 24ቱ ክስተት ባይፈጠር ኖሮ፣ ባለፈው ሐሙስ የዋለው የካቲት 11 ቀን 2013፣ ህወሓት 46ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከብር ነበር፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ህወሓት እንደ ድርጅት ባይኖርም፣ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ግን በትግራይ አንድ ወሬ በጣም በስፋት ሲናፈስ ነበር፤ ‹‹የካቲት 11 (2013) ዶ/ር ደብረፅዮን በድል ወደ መቀሌ ይገባል›› የሚል፡፡ ከመቀሌ ወደ አላማጣ እየተጓዝኩ ሳለ በመንገዳችን አንድ ኬላ ላይ ሲፈትሸን የነበረው አንድ የመከላከያ አባል፣ ይሄንን ወሬ በተመለከተ እንዲህ አለን፡- ‹‹ዶ/ር ደብረፅዮንን እኮ እኛ ይዘነዋል፤ አሁን ከእኛ ጋር ነው ያለው፡፡ ትግራይ ላይ ግን በህዝቡ ውስጥ ዶ/ር ደብረፅዮን የካቲት 11 ይመጣል›› እየተባለ ይወራል፤›› አለን። እንግዲህ የካቲት 11ም አለፈ፤ ህወሓትም አልመጣም፡፡
በነገራችን ላይ ህወሓት ትግራይ ላይ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ድጋፍ አለው፡፡ በህዝቡ ውስጥ ያለው ስነ ልቦና በመሐል ሀገር ሰዎች ‹‹የትግራይ ህዝብ በህወሓት ታፍኗል›› እየተባለ እንደሚወራው አይደለም፡፡ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ‹‹በህወሓት ታፍኛለሁ፤ ነፃነቴንም አጥቼያለሁ›› ብሎ አያስብም፤ ስለዚህ አያማርርም፡፡ ህወሓትን ከፌዴራል መንግስት ጋር ያጣላው ብቸኛው ምክንያት፤ ህወሓት ክልላዊ ምርጫ ስላደረገ ወይም የህዝብ ድጋፍ ስላለው ሳይሆን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ አባላት ላይ በፈፀመው ጥቃት የተነሳ ነው፡፡ አሁን ወደ ትረካዬ ልመለስ፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 2013 የትግራይ ክልል ፕ/ት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ በመግባት ከፌዴራል መንግስት ጋር እንዲያደራድራቸው ጠየቁ።
ህዳር 1 ቀን 2013 ማታ፣ የትግራይ ልዩ ኃይል፣ በሰሜን ዕዝ ያለው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ግድያና ጭፍጨፋ በተመለከተ አንደበተ ርዕቱው ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ መግለጫ ሰጡ። ጄነራሉ በዚህ ንግግራቸው፤ ‹‹ህወሓት ባዘጋጀው ድግስ ላይ የታደሙ የክፍለ ጦር መሪዎችን እንዳገተና ወታደሩ እጅ እንዲሰጥ ጥሪ እንዲያቀርቡ እንዳስገደዳቸው፤ 21 ዓመት ሙሉ በአንድ ምሽግ በወንድማማችነት የኖሩትን የመከላከያ ወታደሮች፣ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ሌሊት በተኙበት እንደረሸኗቸው፤ የህወሓት ልዩ ኃይሎች በተኩስ ልውውጥ የሞቱ የጓደኞቻቸውን ሬሳ ለይተው ሲቀብሩ፣ የተሰው የመከላከያ አባላትን ግን ሳይቀብሩ ጭራሽ ሬሳቸውን ከበው ሲጨፍሩ እንደነበር፤ እንዲሁም፣ ያፈኗቸውን የተወሰኑ የመከላከያ አባላት ልብሳቸውን አውልቀው ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ እንደላኳቸው….›› ገለፁ፡፡
ጄኔራል ባጫ በመደምደሚያቸው፤ ‹‹የህወሓት ወታደሮች ቁማችንን ብቻ ሳይሆን ሬሳችንንም ጭምር ነው ለአውሬ ያስበሉን፤ እነዚህን አረመኔዎች በህይወት እንዲኖሩ ልንፈቅድላቸው አይገባም፤ በመሆኑም ጦርነቱ ኢትዮጵያን ማዳን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብንም ከእነዚህ አረመኔዎች ነፃ ማውጣት ነው!!›› አሉ፡፡
የጄነራል ባጫ ንግግር ምስል ከሳች ስለሆነ፣ የህወሓት ልዩ ኃይሎች የፈፀሙት አረመኔያዊ ድርጊት በአእምሮዬ እየተሳለ ዘገነነኝ፡፡ ከህወሓት ወጣ ያሉ ባህርያቶች ውስጥ ሁልጊዜ የሚገርመኝ ነገር ‹‹አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተማመን፣ አንድነት›› ለሚባሉ የሞራል እሴቶች ያለው ባዕድነት ነው፡፡ ለህወሓት አባላት በዚህ ዓለም ላይ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠውና የመጨረሻው የህይወት ግብ ‹‹ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ›› ነው፤ ሌላው ሁሉ የማይረባ ነው፡፡ ህወሓት ሥልጣንን የሚፈልገው በህዝቦች መካከል የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ እሴቶችን ለማስፈን ቢሆን ኖሮ ‹‹መፍቀሬ-ሥልጣን›› መሆኑ ችግር አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን፣ ህወሓት ሥልጣንን የሚፈልገው ከእነዚህ እሴቶች በተቃራኒ ያለውን ነገር ለማስፈንና የኢኮኖሚ ብዝበዛ ለመፈፀም ነው፡፡ ህወሓት የፌዴራል ሥልጣን ማጣቱ ያልተዋጠለትም ለዚህ ነው፤ 21 ዓመት ሙሉ በወንድማማችነት የኖሩትን የትግራይ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሰራዊት በመካከላቸው የነበረውን የአብሮነት፣ የወንድማማችነት፣ የመተማመንና የአንድነት እሴቶቻቸውን ደርምሶ እርስ በርስ እንዲገዳደሉ ያደረገውም ለዚህ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት እኩይ ባህሪ ያለው አመራር ነው፣ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛት የኖረው፡፡
ለማንኛውም፣ ጄነራል ባጫ ይሄንን መግለጫ የሰጡት እንባ እየተናነቃቸው ነው፤ ንግግራቸው ብዙ ኢትዮጵያውያንን አሳዘነ፤ የህዝብ ቁጣም በህወሓት ላይ ተቀሰቀሰ፤ በቀጣይ ቀኖችም ከአማራ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ወረዳዎች ህወሓትን የሚያወግዙና መከላከያን የሚደግፉ ሰልፎች ተደረጉ፤ በአማራ ክልል ሰልፍ የተከለከለው ህወሓት ወደ ባህርዳርና ጎንደር ሮኬት እየተኮሰ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም፡፡ በየሰልፉ ታዲያ በርካታ ሰንጋዎችና ሚሊዮን ብሮች ለመከላከያ ኃይል ተለገሰ፡፡ የጄነራል ባጫ ንግግር፤ መከላከያን ሰንጋ በሰንጋ አደረገው!!
የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ምንም የብሄርና የሃይማኖት ልዩነት፣ በአንድነት መከላከያ ኃይልን ደግፎ ቆመ፡፡ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደዚህ ዓይነት ህብረት ለመጨረሻ ጊዜ የታየው ከ21 ዓመት በፊት ነበር፤በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት፡፡  
ምንም እንኳ ህወሓት ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሃይማኖት እየከፋፈለ ሲያባላ የኖረ ድርጅት ቢሆንም፣ በስተመጨረሻ ግን ሳያስበው በሞቱ አፋፍ ላይ ህዝቡ በአንድነት እንዲቆምና በራሱ ላይ በቁጣ እንዲነሳ አደረገው፤ በዚህም የፈራው ደረሰ!!
ህዳር 02 ቀን 2013 መቀሌ ከተማ (ምናልባትም መላው ትግራይ) ሙሉ በሙሉ መብራት ጠፋ፤ ይሄም ሁኔታ እስከ ህዳር 4 ቀን 2013 ማታ ድረስ ለ3 ተከታታይ ቀናት ቀጠለ። በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥም ጦርነቱ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማወቅ ተሳነን፡፡ ሆኖም ግን፣ ጥቅምት 30 ላይ ከተከሰቱ ሁለት ነገሮች በመነሳት ህወሓት እየተሸነፈ ስለመሆኑ ፍንጭ አገኘን፡፡
የመጀመሪያው፣ የህወሓት ሚሊሺያዎችና ወጣቶች የማይካድራ አማራዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈፀማቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዶ/ር ደብረ ፅዮን የአፍሪካ ህብረት ጣልቃ በመግባት ከፌዴራል መንግስት ጋር እንዲያደራድራቸው መጠየቃቸው ነው። ሁለቱም የተሸናፊነት ምልክቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል የቃል አቀባያችንም ወሬ፣ ከድል ዜና ወደ አማራ ክልልና የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ያተኮረው፡፡
የማይካድራውን ዘግናኝ ድርጊት ስሰማ ግን ለራሴም መፍራት ጀመርኩ፡፡ ምናልባት ህወሓት በመቀሌ አቅራቢያ የሚሸነፍ ከሆነ፣ የመጨረሻ ዕድሉን ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ወደ መቀሌ መጥተው የሚኖሩትን ዜጎች ሰብስቦና መትረየስ ደቅኖ፣ መከላከያ ከትግራይ እንዲወጣ ወይም ደግሞ ወደ ድርድር እንዲመጣ ለማስገደድ ይጠቀምብን ይሆን ብዬ ፈራሁ፡፡ ህወሓት ይሄንን ላለማድረግ ምን ይከለክለዋል? የሞራል ልዕልናው? ወይስ የዓለም መንግስታት ጫና?! በሌላ በኩል ግን፣ ህወሓት ይሄንን ቢያደርግ በራሱ ህዝብና በዓለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ‹‹እንደ ሽፍታነትና አሸባሪነት›› የሚያስፈርጀው ስለሚሆን ‹‹እንደዚህ ዓይነቱን ውርደት እንኳ አይሞክረውም›› በማለት ለራሴ ማፅናኛ አቀረብኩ፡፡
ህዳር 4 ቀን 2013 ህወሓት ሁለት ተወንጫፊ ሮኬቶችን ወደ ባህርዳርና ጎንደር ኤርፖርቶች ተኮሰ፡፡ መንግስት ሮኬቶቹ ኤርፖርቶቹ አካባቢ የተወሰነ ጉዳት እንዳደረሱ ሲገልፅ፤ የህወሓቱ ጌታቸው ረዳ ግን የሁለቱንም ኤርፖርቶች ተርሚናሎች ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን ተናገረ።
ህዳር 5 ቀን 2013 መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል፣ በወሎ አላማጣ መስመር በመንቀሳቀስ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን የዋጃና የጥሙጋ ከተሞችን ተቆጣጠሩ። የአካባቢው ህዝብም ደስታውን በአደባባይ ሲገልፅ ተመለከትን።
ህዳር 6 ቀን 2013 መከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ኃይል፣ አላማጣን (ራያን) ተቆጣጠረ። ህዝቡም በጭፈራ ደስታውን ገለፀ። ቃል አቀባያችን ግን ‹‹አላማጣ አሁንም በእኛ ቁጥጥር ናት፤ እንዲያውም መከላከያ ግራካሕሱ ተራራ ላይ ከፍተኛ እልቂት ደርሶበት ወደመጣበት ተመልሷል›› በማለት ለግቢያችን ሴቶች ማስተባበያ ሰጠች፡፡
ህዳር 6 ቀን 2013 ህወሓት ተወንጫፊ ሮኬቶችን ወደ ኤርትራ መተኮሱን የክልሉ ሚዲያዎችና ባለ ሥልጣናት ገለፁ። ከኤርትራ በኩል ግን ምንም ዓይነት የአፀፋ ምላሽ አልተሰጠም።
ህዳር 7 ቀን 2013 በትግራይ የስልክና የኢንተርኔት መቋረጥን ተከትሎ፣ አገልግሎት ያቋረጡት ባንኮች ህዝቡ በመቸገሩ ሳቢያ በወረቀት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ። ሆኖም ግን፣ ባንኮቹ አገልግሎት የሚሰጡት ደንበኞቻቸው አካውንት በከፈቱበት ቅርንጫፍ ብቻ ነው በማለቱ ህዝቡ ተቸገረ።
የግቢያችን ሴቶች አንድ ላይ የሚገናኙት ጠዋት ወጥ ሲሰሩ ወይም ልብስ ሲያጥቡ አሊያም ማታ እረፍት ሲያደርጉ ነው፡፡ እናም በእነዚህ ሰዓታት ሴቶቹ የቃል አቀባያችንን ገለፃ ይናፍቃሉ፡፡ ቃል አቀባያችን ካለች፣ ስብስቡ ሳይፈርስ ለረጅም ሰዓት ይቆያል፡፡
ህዳር 8 ቀን 2013 ጠዋት እንደተለመደው፣ የግቢያችን ሴቶች፣ ወጣቸውን እየሰሩ ተሰባስበዋል፡፡ ቃል አቀባያችንም የዕለቱን መግለጫዋን እንዲህ በማለት ጀመረች፣ ‹‹መከላከያ ይሄንን ሰንጋ በልቶ በልቶ ሲተኛ፣ እኛ በተኙበት እንጨርሳቸዋለን፡፡ በነገራችን ላይ፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያበቃለት ነገር ነው፤ ከመበታተን አትድንም፡፡ እኛ ከላይ እያጠቃን፣ ኦነግ ሸኔ ደግሞ ከኦሮሚያ እየገፋ ነው፤ አልሸባብም አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ደቡብ ላይ ወላይታዎች አማራን ጠራርገው እያስወጡ ነው፡፡ በመሬት ይገባኛል የተነሳ ሱዳንና አማራ ጦርነት ገጥመዋል፡፡….ኢትዮጵያ አልቆላታል፡፡›› ቃል አቀባያችን ይሄንን ስትል ፊቷ እየበራ ነው፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት ኢትዮጵያ ተበታትና ህወሓት ቢተርፍላት ቃል አቀባያችን ደስታዋ ነው፤ ይሄ ስሜት የቃል አቀባያችን ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ስሜት ነው፡፡  ወደ ቤት  ገብቼ አማራ ቴሌቪዥን ስከፍት አንድ የጎንደር ወጣት፤ ‹‹አሁን የእኛ ስጋት ህወሓት የመቀሌ ህዝብ መካከል መሽጎ እንዳይዋጋና የመቀሌ ህዝብ እንዳይጎዳ ነው›› ሲል ሰምቼው ገረመኝ፡፡ የነገ ሰው ይበለን!


Read 9320 times Last modified on Wednesday, 24 February 2021 18:22