Monday, 22 February 2021 08:33

መራሔ ንባብ፤ ያሸለበ የንባብ ባህላችንን ለማንቃት

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(2 votes)

  ሰሞኑን በወጣ የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ መሠረት፤ ከግማሽ በላይ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተሸጋገሩ አይቮሪኮስታውያን ተማሪዎች ማንበብ አይችሉም፡፡ ተማሪዎቹ ማንበብ የማይችሉት የተፈጥሮ ችግር ኖሮባቸው አይደለም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ጤናማ  ናቸው፡፡ ግን እንዴት ሳያነቡ ጤንነት ይኖራል? የሆኖ ሆኖ በርካታ ጽሑፎች አንብበውና አመዛዝነው፣ ዕውቀት በመጨበጫ ዕድሜያቸው ላይ ፊደል መለየት እንኳን አይችሉም ነው የተባለው። ኪሳራውን አስቡት!  ደግሞ እኮ ከዓመት መዓት ከክፍል ወደ ክፍል እየተሸጋገሩ ነው 9ኛ ክፍል የደረሱት፡፡ ግን እንዴት? በትውልድ ላይ መቀለድ ይሏል ይሄ ነው፡፡
በእኛም ሀገርም እውነታው ከዚህ ብዙም የሚለይ አይመስለኝም፡፡ የትምህርት ሥርዓቱ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ እናም ሁለተኛ ደረጃ ካጠናቀቁም በኋላ ጭምር በደንብ ማንበብ የሚችሉ (ሳያደናቅፋቸው) ወጣቶች ማግኘት ብርቅ ቢሆንብን አይገርምም፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ የተካሄደው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ፣ ጎልማሶችን ቢያንስ “ከመሐይምነት” ለማላቀቅ የታለመ እንደነበር ይታወቃል። ዛሬ ግን መሐይምነት በየትምህርት ቤቱ ሰፍኗል። ፊደል ቢቆጥሩም  ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ተበራክተዋል፡፡  
በአንድ ዩኒቨርሲቲ በምሁራን ላይ በተካሄደ መደበኛ ያልሆነ ጥናት፣ ምሁራኑ፣ የ“የ”ን የፊደል ዘሮች አሟልተው እንዲጽፉ ተጠይቀው ነበር፡፡ በወቅቱ ከተጠየቁት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ምሁራን መካከል ግን አንድም "የ፣ ዩ፣ ዪ፣ ያ፣ ዬ፣ ይ፣ ዮ" ብሎ በትክክል የጻፈ አልተገኘም ተብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህሩና ደራሲው ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ፣ እነዚህንና መሰል ከንባብ ጋር የተያያዙ የክሂሎት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያግዝ፤ “መራሔ ንባብ፤ የማንበብ ክሂል ማበልጸጊያ” የተሰኘ ባለ 220 ገጽ መጽሐፍ በቅርቡ አበርክተውልናል። መጽሐፉ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ድኅረ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያገለግላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት፣ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ደረጀ ገብሬ መጽሐፋቸው በምን ላይ እንዳተኮረ ሲገልጹ፤
"--የዛሬ እውነቶቻችን ደግሞ በአመዛኙ የሚገኙት በመጻሕፍት ገጾች ውስጥ ነው። ስለዚህም ነው ልጆች የመጻሕፍት ፍቅር እንዲያድርባቸው በማንበብ ክሂላቸው መኖር፣ ማደግና መጠንከር ላይ እንሥራ የሚለውን ነጥብ በጥብቅ ያተኮርኩበት--" ብለዋል፡፡
ከዚሁ ክሂል ጋር በተያያዘም፤
"…መንግሥታት በሚያዋቅሩት በማናቸውም አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ውስጥ ደግሞ ጎልማሶች በጥቅሉ፣ በትምህርቱ ዘርፍ ደግሞ ተማሪዎችና መምህራን ቀጥተኛ ተሳታፊዎች፣ ውለኛ ተዋናዮች መሆናቸው ይታመናል፡፡ ይሁንና ይበልጥ ጉልህ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ተማሪዎች ትላንትን የሚመረምሩ፣ ዛሬን የሚጨብጡና የሚያበጃጁ፣ ነገንም የሚተልሙ መሆናቸውም ግልጽ ነው። መምህራን ደግሞ ይህ ከተማሪዎች የሚጠበቀው ክሂል ይገኝና ይዳብር ዘንድ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ናቸው ፡፡" ብለዋል።
መጽሐፉ 18 ምዕራፎችን ይዟል። ምዕራፍ ሁለት ስለ ማንበብ ዓላማ፣ ምዕራፍ ሦስት የማንበብ ክሂል የእድገት ደረጃዎች፣ ምዕራፍ አምስት የማንበብ ክሂል ለማስተማር የሚረዱ ዝርዝር የክፍል ውስጥ ተግባራት፣ ምዕራፍ ሰባት የማንበብ ክሂል ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው፣ ምዕራፍ ዘጠኝ የልጆችን የማንበብ ችሎታ ለማዳበር የወላጆች ድርሻ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡  
ማንበብ እያደገ የሚሔድ ክሂል መሆኑን የጠቀሱት ምሁሩ፣ የልጆች የማንበብ ዐቅም እንዴት እንደሚለካም እንዲህ ያብራራሉ፡-
"የልጆችን የማንበብ ክሂሎት ዕድገትን ያጠኑ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ፣ የአንድ ልጅ የማንበብ ዐቅም የሚለካው የሚገኝበት ዕድሜ በዐሥር ተባዝቶ ነው፡፡ ለምሳሌ አንደኛ ክፍል የጀመረና ሆሄያት ያጠናቀቀ የ7 ዓመት ሕፃን (7*10) ሰባ ቃላትን በ1 ደቂቃ ማንበብ ይጠበቅበታል፡፡ 3ኛ ክፍል የደረሰ የ10 ዓመት ልጅም እንዲሁ (10*10) መቶ ቃላትን በደቂቃ አቀላጥፎ  ያነባል ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ስሌት ምናልባት እንደየ ቋንቋዎቹ  ባሕርያትና ያፃፃፍ ሥርዓት ሊለያይ መቻሉንና የተማሪውን ከባቢያዊ ሁኔታ የተሟላ መሆን ከግምት ማስገባት ያስፈልግ ይሆናል፡፡" (ገጽ 15-16)
በሌላ በኩል፤ ከመጽሐፍ ንባብና ጽሑፍ ዝግጅት ጋር የተያያዙ ብዙ መረጃዎችም አሉት፡፡ ለምሳሌ ልጆች ለምንድነው በእርሳስ መጻፍ ያለባቸው? (ገጽ 50)፣ ውጤታማ የሆኑ እና ያልሆኑ የቃላት ማስተማርያ ስልቶች (ከገጽ 168 እስከ ገጽ 172)፣ ንባብን ለማዳበር የመጻሕፍት ዐውደርዕይ ጠቀሜታ (ገጽ 98)፣ የመጻፍ ችሎታን ስለማዳበር (ገጽ 174) እና ትምህርታዊ ንባብ (ገጽ 160) መጥቀስ ይቻላል፡፡
ምሁሩ በዚህ መጽሐፍ ለተማሪዎች መጻሕፍትን ማን መምረጥ አለበት? ማንስ እየመረጠ ነው? ሲሉም ይሞግታሉ፡-
"--የተማሪዎችን የትምህርት አያያዝ፣ የችሎታና የዝንባሌ ሁኔታዎችን ከየትኛውም ወገን በተሻለ የሚረዱት መምህራን እንደመሆናቸው መጠን መጻሕፍትንም በመምረጥ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠሪ ቢሆኑ እጅግ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ መማርያ መጻሕፍትንም ሆነ ማመሳከርያዎችን በመምረጥ ረገድ በተማሪዎች የክፍል ክንውን ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸው በየትምህርት ቢሮዎች በኃላፊነት ያሉ ባለሥልጣኖች መጻሕፍት እንዲያዘጋጁ መመርያ ያወጣሉ፤ ይመርጣሉ፤ ደረጃ ያወጡና ወስነው ይልካሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ኃላፊዎች በክፍል ውስጥ ዘወትር የሚደረገውን ትምህርታዊ እንቅስቃሴና ተግባራዊ ልምምድ ዕለት በዕለት በቅርብ ሆነው የሚከታተሉ አይደሉም፤እንደ መምህራን በእያንዳንዱ ክፍል፣ በእያንዳንዱ ተማሪ ዘንድ ያለውን ተጨባጭ ፍላጎትና ዝንባሌ እንዲሁም ችሎታ፣ እምነትና የሕይወት ትልም የሚረዱ አይደሉም፡፡ በመሆኑም የመማርያንም ሆነ የማመሳከርያ መጻሕፍትን በመምረጥ ረገድ ለመምህራን ቅድሚያውን ቢሰጡ በትምህርት ቤቶቹ፣ በየደረጃዎቹ የተመጣጠነ ትምህርት፣ የተመጣጠነ ልምምድ ይገኝ ዘንድ መርዳታቸው መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡--" (ገጽ154)
በመጨረሻም፤ መራኄ ንባብ መጽሐፍ፤ በተለይ ለወላጆች፣ ለቋንቋ መምህራን እንዲሁም የንባብ ክሂሎታቸውን ለማጎልበት የሚሹ ሁሉ ቢጠቀሙበት በእጅጉ ያተርፉበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን  በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 794 times