Sunday, 28 February 2021 00:00

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ የፍ/ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበሩ እንዳሳሰበው ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  በኦሮሚያ ክልል የፍ/ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበሩ በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምርቃት ላይ ተቃውሞ በማሰማቱ የታሰረውና ፍ/ቤት ዋስትና የሰጠው ተማሪ እስካሁን አለመለቀቁን ኮንኗል።
በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ የፍ/ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ያመለከተው ኮሚሽኑ፤ ጉዳዩ አፋጣኝ ትኩረትና መፍትሄ ይሻል ብሏል በመግለጫው።
የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ “ፍትህ ለሃጫሉ ሁንዴሳ ፤ እነ ጃዋር ይፈቱ! ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ” የሚሉ መፈክሮች ማሰማቱን ተከትሎ፣ የታሰረው ተመራቂ ተማሪው መሃመድ ዲክሲሶ ፍ/ቤት ከቀረበ በኋላ ፍ/ቤቱ በዋስትና ቢለቀውም ከእስር ቤት ሊወጣ አለመቻሉን ኮሚሽኑ አመልክቷል። በምን ምክንያት እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ? ለሚለውም ምላሽ የሚሰጥ አካል የለም ያለው ኮሚሽኑ፤ ተማሪው በተያዘበት ወቅትም በፖሊሶች በተደጋጋሚ በጥፊ መመታቱን ፣ በዱላ ሁለቱን እግሮቹን መደብደቡንና ጎኑ አካባቢ እንደ ተመታ አረጋግጧል። ይህም በተጠርጣሪዎች ላይ የሚፈጸም ኢ-ሠብአዊ አያያዝ አሁንም መቀጠሉን አመላካች መሆኑን ጠቁሞ በተለይ በኦሮሚያ ያሉ የፍትህ ተቋማት የሰዎችን ሰብአዊ
መብት ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ አሳስቧል። በተጠርጣሪው ላይ የተፈጸመው ድብደባ ተጣርቶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲደረጉ የጠየቀው ኮሚሽኑ “ተማሪው የፈፀመውና ለእስር ያበቃው ጉዳይም የሚያስጠይቅና በወንጀል ክስ የሚያሳስር ጉዳይ አልነበረም” ብሏል። ተማሪ መሃመድ ዲክሲሶ የጅማ ወረዳ ፍ/ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሁለት ሺህ ብር ዋስ እንዲፈታ ትእዛዝ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም ኢሠመኮ መግለጫውን እስካወጣበት ከትናንት በስቲያ ሃሙስ የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በእስር ላይ እንደነበር ታውቋል።


Read 7759 times