Sunday, 28 February 2021 00:00

“በአክሱም ከ2 መቶ በላይ ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል” - አምነስቲ ኢንተርናሽናል “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያው ስለመፈፀሙ መረጃ አለኝ፤ እየመረመርኩ ነው” - ኢሠመኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  በትግራይ ከተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ጋር በተገናኘ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመንግስትና በኤርትራ ወታደሮች ተፈፅመዋል ያላቸውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በምርመራ ይፋ ያደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው፤ ነገር ግን የኤርትራ ወታደሮች የበቀል እርምጃ ስለመውሰዳቸው መረጃው አለኝ ብሏል፡፡ አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተገናኘ በህዳር ወር በሁለት ቀናት ውስጥ ከ2 መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ በተለይ በአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ማነጋገሩ እንዲሁም በከተማዋ በሚገኙ ሁለት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቀብር ስፍራዎችን የሚያመለክቱ ጥራት ያላቸው ማስረጃዎች ከሳተላይት ማስረጃ ማግኘቱን አምነስቲ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ አምነስቲ ይህን ምርመራ ሲያደርግ፣ 41 ከጥቃት የተረፉ የአይን ምስክሮችን ማነጋገሩንም ጠቅሷል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች በህዳር 10 እና 11 አክሱም ከተማ በመግባት በመንገድ ላይ ያገኙትን ሰው ላ ይ ሁ ሉ ተኩስ መ ክፈታቸውን፣ ቤት ለቤት በመዘዋወርም ግድያ መፈፀማቸውን ያመለከተው አምነስቲ፤ ይህም በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው ብሏል፡፡ በጥቃቱም የኤርትራ ወታደሮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን መግደላቸውን፣ ሰላማዊ ሰዎችንና ታጣቂዎች ያልለየ ግድያና፣ እንግልት መፈፀማቸውን፣ መጠነ ሰፊ ዘረፋ ቤት ለቤት ጭምር መፈፀማቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡ ከሳተላይት በተገኘ መረጃ መሰረትም በሁለት አብያተ ክርስቲያን ጥራት ባለው ምስል የሚታዩ ሁለት የጅምላ መቃብር ቦታዎች መገኘታቸውን አመልክቷል-ሪፖርቱ፡፡ የአክሱም ነዋሪዎች በጥቃቱ በመደናገጥ ለከፍተኛ መረበሽና የስነ- ልቦና ጉዳት መዳረጋቸውን፣ ሃዘናቸውም እጅግ የበረታ ሆኖ መክረሙን ሪፖርቱ አትቷል፡፡ በአክሱም ከተማ በኤርትራውያኑ የተፈፀመው ግድያ ፣ዘረፋና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በአጠቃላይ ለዘጠኝ ቀናት የቆየ ቢሆንም፤ በሁለት ቀናት ውስጥ የፈፀሙት ግን የከፋ ድርጊት መሆኑን ሪፖርቱ ያትታል። አምነስቲ በዚሁ ሰፋ ያለ ሪፖርቱ፤ የአይን እማኞችን የሰጡትን ዝርዝር ምስክርነትና መረጃ አቅርቧል፡፡ ይህን የተቋሙን ሪፖርት ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው አጭር መግለጫው፤ በአክሱም ተፈፅሟል ስለተባለው ድርጊት ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁሞ በንፁሀን ላይ የኤርትራ ወታደሮች የበቀል እርምጃ ስለመውሰዳቸው ግን መረጃ እንዳለው አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ግኝት፤ የህወኃት ታጣቂዎች ለፈፀሙባቸው ጥቃት፣ የኤርትራ ወታደሮች በወሰዱት
የበቀል እርምጃ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ስለመገደላቸው ጠቁሟል-ኢሠመኮ፡፡ ይህ የበቀል ጥቃት የተፈጸመውም የህወሃት ታጣቂዎች አክሱምን ለቀው ከወጡ በኋላ መሆኑንና ይህን ድርጊት ጨምሮ ኮሚሽኑ በመላ ትግራይ ተፈፅሟል ስለ ሚባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጠለቅ ያለ ምርመራ እያካሄደ
መሆኑን አስገንዝቧል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በምርመራ ስለተገኙ ግኝቶች የመንግስት አካላት አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘ በሪፖርቱ አመልክቷል። ለአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ሃይል ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሪፖርቱን አቅርቦ ምላሽ ቢጠባበቅም እንዳልተሳካለት
አመልክቷል። መንግስት ከሰሞኑ በትግራይ ስላለው ሁኔታ አለማቀፋ ማህበረሰብ ግንዛቤ ያገኝ ዘንድ ቢቢሲና ሮይተርስን ጨምሮ ሰባት አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም 137 ያህል አለማቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ወደ ትግራይ ገብተው ሁኔታውን እንዲታዘቡ መፍቀዱ ይታወቃል፡፡

Read 8015 times