Monday, 01 March 2021 19:42

ከ54 የአፍሪካ አገራት የኮሮና ክትባት መስጠት የጀመሩት 9 ብቻ ናቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   - የሌጎስ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ከአፍሪካ አጠቃላይ ተጠቂዎች ይበልጣል ተባለ
       - በኮሮና ክትባት የጎንዮሽ ጉዳት ለሚደርስባቸው 92 አገራት ዜጎች ካሳ ይሰጣል

           በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙት 54 አገራት መካከል እስካለፈው ረቡዕ ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለዜጎቻቸው መስጠት የጀመሩ አገራት 9 ብቻ መሆናቸውን ስታቲስቲያ ድረገጽ ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡ በአህጉሪቱ የተለያዩ አይነት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን መስጠት የጀመሩት አገራት ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሼልስ፣ ሩዋንዳ፣ ሞሪሺየስ፣ ዚምባቡዌና ሴኔጋል መሆናቸውን የጠቆመው መረጃው፤ አገራቱ ከሚሰጧቸው ክትባቶች መካከል አስትራዜንካ፣ ሲኖፋርም፣ ስፑትኒክ 5፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ፋይዘርና ሞዴርና እንደሚጠቀሱም ገልጧል፡፡ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋና ክትባቶችን
ቢቀበሉም ገና መከተብ አልመጀመራቸውን የጠቆመው ድረገጹ፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከአለማቀፉ የክትባት ጥምረት፣ ከግዢና ከአገራት ልገሳ የሚያገኙዋቸውን ክትባቶች በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡ ኮቫክስ የተባለውና ክትባቶችን በፍትሃዊነት ለአገራት ለማዳረስ የተቋቋመው አለማቀፍ ጥምረት ወደ አፍሪካ የላከው የመጀመሪያው ክትባት ባለፈው ረቡዕ ጋና የደረሰ ሲሆን፣ ጋና የደረሰው 600 ሺህ የኮሮና ቫይረስ ክትባት በብሪታኒያ
የተመረተው ኦክስፎርድ አስትራዜኒካ መሆኑንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ጥምረቱ በቀጣይ ቀናትም ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ክትባቶችን እንደሚልክ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ እስከ 2021 የፈረንጆች አመት መጨረሻ ለአፍሪካ 600 ሚሊዮን ያህል ክትባቶችን ለመስጠት ማቀዱንና ይህም 20 በመቶ የአህጉሪቱን
ህዝብ ለመከተብ እንደሚያስችል መነገሩን አክሎ ገልጧል፡፡ አል አይን በበኩሉ፤ በኮቫክስ ጥምረት ውስጥ በአባልነት በተካተቱ 92 አገራት የሚሰጡ የኮሮና ክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለሚያስከትሉባቸው ሰዎች የገንዘብ ካሳ የሚከፈልበት አሰራር መቀየሱን ዘግቧል፡፡ በአለም የጤና ድርጅትና ቸብ ሊሚትድ
በተባለ ኩባንያ አጋርነት የሚተገበረው ይህ የካሳ አሰጣጥ ፕሮግራም፣ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2022 ድረስ በኮቫክስ በኩል ከሚሰራጩ ክትባቶች ጋር በተያያዘ ከባድ እክል የሚገጥማቸውን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡ በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ከ3.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል 62 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች መሆናቸውን የአለም የጤና ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ በናይጀሪያዋ የንግድ ከተማ ሌጎስ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 4 ሚሊዮን እንደሚደርስና ይህ ቁጥር
በአፍሪካ አህጉር በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር እንደሚበልጥ ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ በናይጀሪያ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር
153 ሺህ እንደደረሰ ቢነገርም፣ የአገሪቱ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በአራት ግዛቶች የሰራው ጥናት ግን በሌጎስ ከተማ ብቻ 4 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ እንደማይቀሩ የሚጠቁም መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡


Read 1011 times