Saturday, 06 March 2021 12:57

መንግስት ገበያ የማረጋጋቱን ስራ በጥቂት ቀናት ውስጥ እጀምራለሁ አለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

    በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል ምርቶችን ለህብረተሰቡ እንዲከፋፈል ይደረጋል ተብሏል፡፡
በከፍተኛ መጠን አየናረ የመጣውን የሸቀጦች ዋጋ ለማረጋጋት የሚያስችል አዲስ አሰራር በጥቂት ቀናት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግና ከአለማቀፍ ኩባንያዎች የሚረከባቸውን ምርቶች በልማት ድርጅቶች በኩል ለህብረተሰቡ እንደሚከፋፈሉ ተገለፀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሚኒስቴር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ እንደተናገሩት፤ አሁን የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና ገቢያውን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች ተግባራዊ ማድረግ ይጀመራል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ከንግድ አሻጥር ጋር የሚያይዙ አንዳንድ አካላት እንዳሉ የጠቆሙት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ የችግሩ መንስኤ ግን የንግድ አሻጥር ሳይሆን የንግድ ስርዓቱ ባለበት ችግር ሳቢያ የተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድም መንግስት በቀጥታ ምርቶችን ከአለም አቀፍ ኩባንያዎች በመግዛትና ለመንግስት የልማት ድርጅቶች በማቅረብ ለህብረተሰቡ እንዲከፋፈሉ የሚደረግበትን አሰራር በቅርቡ ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል።
 በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል ምርቶቹን የማከፋፈል ስራው በቅርቡ ይጀመራል ያሉት ምርቶቹ በአለ በጅምላና በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት በኩል ይከፋፈላሉ ብለዋል። የስርጭቱን ሁኔታ የሚቆጣጠር አካል እንደሚኖርና ምርቱ በትክክል ለህብረተሰቡ መድረሱን የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዳቦ አምራች ድርጅቶች ያጋጠማቸው የግብአት እጥረት በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚፈታ የጠቆሙት ሚኒስቴር ዴታው፤ መንግስት በግዥ ያመጣው ስንዴ ወደ አገር ውስጥ የገባ በመሆኑ በቅርቡ ለዳቦ አምራቾች እንደሚከፋፈል ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ጭማሪውን ተከትሎ የተደረጉትን የዋጋ ጭማሪዎች ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ሚኒስቴር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡




Read 678 times