Saturday, 06 March 2021 13:13

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ በአፋጣኝ እንዲወጡ የተባበሩት መንግስታት አሳሰበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን ተቃውመዋል


             የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለመምከር ከትናንት በስቲያ  ጠርቶት በነበረው ስብሰባ ሩሲያ፣ ህንድና ቻይና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አያስፈልግም የሚል አቋም ሲያንፃባርቁ፤ የመንግስታት ድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት በዝግ ባካሄደው ስብሰባ  በድርጊቱ ላይም በጦርነቱ ወቅት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ስለመኖሩ መረጃዎች መኖራቸውን የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ እንደነበሩ መክሯል።
ጦርነቱን ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን፣ ተገቢው ተከታታይነት ያለው እርዳታ የማይቀርብ ከሆነም የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አስገንዝበዋል።
ዋና ፀሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፤ በሰብአዊነት ላይ በሚፈፀም ወንጀልና በጦር ወንጀል ስሙ በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለው የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ በአፋጣኝ ለቆ እንዲወጣ ማሳሰባቸው  ታውቋል።
በትግራይ በአሁኑ ሰዓት መንግስት የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩንና አስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን መንግስት በተደጋጋሚ እየተገለጸ ቢሆንም ከትናንት በስቲያ የመከረው የፀጥታው ም/ቤት ፤በክልሉ አሁንም የረሃብ ስጋት መኖሩንና አመፅ ቀስቃሽ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ መሆኑን አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት 4.5 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው የጠቆመው የመንግስታቱ ድርጅት በአጠቃላይ በበቂ ሁኔታ እርዳታ ለማቅረብ 4 መቶ ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል። መንግስት በበኩሉ፤ 3.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በበቂ ሁኔታ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ሰሞኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ተቋማትን ጨምሮ 84 ያህል መንግስታዊ ያልሆኑ የረድኤት ድርጅቶች በትግራይ በነጻነት እየተንቀሳቀሱና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም መንግስት አክሎ ገልጿል።
ከትናንት በስቲያ በዝግ በመከረው የጸጥታው ም/ቤት ላይ ሩሲያ፣ ቻይናና ህንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነትን ሲቃወሙ፤ ቋሚ አባላቱ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ እንዲሁም ተለዋጭ አባላት የሆኑት አየርላንድ፣ ኬንያ፣ ሜክሲኮ ፣ ኒጀር፣ ኢስቶኒያ፣ ሴንት ቬንት፣ ቬትንናምና ቱኒዚያ ጣልቃ ገብነቱን ያልተቃወሙ ሀገራት መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

Read 948 times