Saturday, 06 March 2021 13:15

በምርጫው 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ መረጋገጡ ተገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ለዘንድሮ ምርጫ 15 የፖለቲካ ድርጅቶች እጩዎችን በማስመዝገብ ተሳትፏቸውን ያረጋገጡ ሲሆን እስከ ረቡዕ ድረስ በነበረው የእጩዎች ምዝገባ፣ ከ2 ሺህ በላይ ተወዳዳሪ እጩዎች መቅረባቸውን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ አስታውቀዋል፡፡
በእጩዎች ምዝገባና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ባለፈው ረቡዕ  የመከሩት የምርጫ ቦርድ ሰብሰቢዋ፤ 15 የፖለቲካ ድርጅቶች በምርጫው እንደሚሳተፉ መረጋገጡን ጠቁመው፤ መረጃዎች ገና ተጣርተው ባይጠናቀቁም እስከ ረቡዕ ድረስ 2 ሺህ ያህል እጩዎች በፓርቲዎቹ መመዝገባቸውን አመልክተዋል።
 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእጩዎች ምዝገባ ጋር በተያያዘ የገጠሟቸውን ችግሮች ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የእጩዎች መታሰርና በየአካባቢው የሚገኙ የምርጫ ቦርድ ፅ/ቤቶች የተሟላ አገልግሎት አለመስጠት እንደ ጉድለት ተጠቅሰዋል።
ቦርዱ በመላው ሃገሪቱ 673 የምርጫ ፅ/ቤቶች ማደራጀቱን የጠቆሙት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ፤ በሁሉም ፅ/ቤቶች ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው፤ የተጠቀሱ ጉድለቶችም እየተቀረፉ መሆኑን ተናግረዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች መታሰርን በተመለከተም ለቦርዱ አቤቱታ ያቀረቡት ፓርቲዎች መፍትሄ ማግኘታቸውን የገለጹት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ በሃረር የአብን እጩ እንዲሁም በጋምቤላ የኢዜማ እጩዎች መታሰራቸውን በተመለከተ ለቦርዱ በቀረበው አቤቱታ መሰረት፣ ከየአካባቢው አስተዳደሮች ጋር ተነጋግሮ እንዲፈቱ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ምርጫ ፓርቲዎቹ ከአባላትና እጩዎች እስር ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎች እንደሚያቀርቡ ያመለከቱት ሰብሳቢዋ፤ የመንግስት አካላት በምርጫ ወቅት  የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ከማሰርና ከማዋከብ ባህል መላቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።


Read 813 times