Saturday, 06 March 2021 13:15

የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ መብት ምርመራ ቡድን ወደ ትግራይ ለመግባት ጥያቄ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ወደ ትግራይ ገብቶ ተፈጽሟል የተባለውን የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ የሴቶች ጥቃትና አጠቃላይ የጦር ወንጀል ጉዳይን ለመመርመር እንዲችል ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል።
በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ሂደት ጋር ተያይዞ፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተመለከተ በርካታ ሪፖርቶች እየደረሱት መሆኑን የጠቆሙት  የመንግስታቱ ድርጅት የሠብአዊ መብቶች ጉዳይ ሃላፊዋ ሚሼል ባቼት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን እንድናጣራ ይፍቀድልን ሲሉ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ በይፋ ጠይቀዋል።
በኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ የህወኃት ታጣቂዎች፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ከደረሱኝ ጥቆማዎችና መረጃዎች ተረድቼአለሁ ብሏል - ድርጅቱ፡፡
እነዚህን ጥቆማዎችና መረጃዎች ለማጣራትና ትክክለኛውን ምርመራ ለማድረግ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ቢሮ ፍላጎት እንዳለውና የመንግስትን ፈቃደኝነት እየጠበቀ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
በትግራይ ከተካሄደው የህግ ማስከበር ሂደት ጋር ተያይዞ፣ የሰላማዊ ሰዎች ጅምላ ግድያ፣ የሴቶች መደፈርና ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም የሃብትና ንብረት ዘረፋዎች ስለመፈጸማቸው  መረጃዎች እንደደረሰው ድርጅቱ አመልክቷል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ በተለይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ያወጣውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ፣ ከፌደራል ፖሊስና ከጠቅላይ አቃቢ ህግ የተውጣጣ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ልኮ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ጠቁሞ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም ጥልቅ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሰባ አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ 135 ያህል የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች ወደ ትግራይ ገብተው  ሁኔታውን እንዲመለከቱ መንግስት መፍቀዱ  ይታወቃል።
በሌላ በኩል፤ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም ተገቢው የምግብና ሌሎች አስፈላጊ እርዳታዎች እየቀረቡ መሆኑም ተመልክቷል።




Read 864 times