Saturday, 06 March 2021 14:05

የአለማችን ነጻነትና ዲሞክራሲ በ2020 እጅግ በከፋ ሁኔታ አሽቆልቁሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የፖለቲካ መብቶችና የህዝብ ነጻነቶችን ጨምሮ የተለያዩ መስፈርቶችን ተጠቅሞ የአገራትን አጠቃላይ ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ አለማቀፍ የነጻነት ሁኔታ ሪፖርት የሚያወጣው ፍሪደም ሃውስ የተባለ ተቋም፣ ከሰሞኑም የ2020 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በአመቱ የአለማችን ዲሞክራሲና ነጻነት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን አስታውቋል፡፡
በአለም ዙሪያ የሚገኙ 195 አገራትና 15 ግዛቶችን አጠቃላይ የዲሞክራሲና ነጻነት ሁኔታ ያጠናው ተቋሙ፣ በዘንድሮው ሪፖርቱ 82 አገራትን “ነጻ”፣ 59 አገራትን “በከፊል ነጻ” እና 54 አገራትን “ነጻ ያልሆኑ” በሚል በሶስት ከፍሎ አስቀምጧቸዋል፡፡
የአመቱ ነጻነትና ዲሞክራሲ የሌለባት ቀዳሚዋ አገር ተብላ የተጠቀሰቺው ሶርያ ስትሆን፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቱርኬሚኒስታንና ሰሜን ኮርያ እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ የነጻነትና ዲሞክራሲ መሻሻል ያሳዩት ቀዳሚዎቹ 5 የአለማችን አገራት ሱዳን፣ ማላዊ፣ ቦሊቪያ፣ ቺሊና ሰሜን ሜቄዶኒያ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአንጻሩ ከፍተኛ ማሽቆልቆል ያሳዩት ደግሞ ካይሬጊስታን፣ ቤላሩስ፣ ማሊ፣ ኮትዲቯርና ታንዛኒያ ናቸው ብሏል፡፡
በአመቱ የአለማችን ነጻና ዲሞክራሲያዊ አገራት ተብለው የሚጠቀሱትን አሜሪካና ህንድን ጨምሮ 73 የአለማችን አገራት ባለፈው አመት ከነበሩበት ደረጃ ማሽቆልቆላቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የነጻነት ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉ በአንጻሩ 28 አገራት ብቻ መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል ሱዳንና ማላዊ ይጠቀሳሉ ብሏል፡፡
ባለፉት 10 አመታት እጅግ ከፍተኛ የነጻነትና ዲሞክራሲ ማሽቆልቆል የታየባቸው ሶስቱ ቀዳሚ የአለማችን አገራት ማሊ፣ ቱርክና ታንዛኒያ መሆናቸውን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ኢትዮጵያ አምና ከነበረችበት ደረጃ በ2 ዝቅ ማለቷንም ያሳያል፡፡

Read 3320 times