Saturday, 18 August 2012 12:20

የአቡነ ጳውሎስ ቀብር ከስድስት ቀናት በኋላ ይፈጸማል

Written by  መልካሙ ተክሌ
Rate this item
(0 votes)

በተወለዱ በ76 ዓመታቸው በተሾሙ በኻያኛ ዓመት ዘመነ ፕትርክናቸው ሐሙስ ከንጋቱ 11 ሰዓት በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር በመጪው ሐሙስ ይፈጸማል፡፡ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2004 ሰባት ሰዓት ላይ አስክሬናቸው ከሚገኝበት ሆስፒታል ወደ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ተወስዶ ፍትሃት ሲደረግለት ካመሸ በኋላ በ11፡00 ሰዓት ላይ አስከሬናቸው በግልጽ ሰረገላ ተጭኖ በብፁዓን አባቶች አጃቢነት ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ገብቶ ያድራል፡፡በማግስቱም ከሌሊቱ 11፡00 ጀምሮ በብፁዓን ዐባቶች መሪነት ቅዳሴ ይደረግ እና ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ የሽኝት ፕሮግራም ከተደረገለት በኋላ ሥርዓተ ቀብሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሐይማኖት ከተቀበሩበት መቃብር አጠገብ እንደሚፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጿል፡፡

ፓትርያርኩ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ማምሻውን ወደ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ገብተው ለረጅም ጊዜ ክትትል ሲያደርጉላቸው በቆዩት የሆስፒታሉ ዶክተሮች ሕክምና ቢደረግላቸውም ሕይወታቸውን ግን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ የፍልሰታ ማርያም ጾምን  በድሬዳዋ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ወቅድስት አርሴማ የሴቶች ገዳም  የማሳለፍ ልማድ እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አቡነ ጳውሎስ በዘንድሮው ሱባኤ ግን በአዲስ አበባ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እያሳለፉ እንደነበር ታውቋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቡነ ጳውሎስ የነበረባቸው የስኳር ሕመም በጾሙ ወቅት እየጨመረባቸው መጥቶ እንደነበር እና ጸሎተ ቅዳሴ ጀምረው መጨረስ እያቃታቸው ያቋርጡ እንደነበር ታውቋል፡፡የዐይን እማኞች እንዳረጋገጡትም እግራቸው እጅግ እያበጠ ያስቸግራቸው ስለነበር ጫማቸውን አውልቀው እግራቸውን በወንበር ላይ ሰቅለው ይቀመጡ ነበር፡፡

ወደ መኖሪያቸው ሲወጡም ይኹን ሲገቡ በሰዎች ርዳታ ታግዘው እንደነበር ያረጋገጡት ምንጮች ከቆየባቸው የስኳር በሽታና ከፍተኛ የደም ግፊት ሕመሞቻቸው (hypertension and diabetes) መወሳሰብ ጋራ በተያያዘ ሁለቱም እግሮቻቸው ከአውራ ጣታቸው ጀምሮ እስከ ጉልበታቸው ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቶ እንደነበር የዐይን እማኞች አረጋግጠዋል፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውን በሚመለከት በትናንትናው ዕለት መግለጫ የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በበኩላቸው፤የስኳር ሕመም ጾም እና መንገላታት እንደማይወድ በማስታወስ አቡነ ጳውሎስም በዚሁ የፍልሰታ ጾም የስኳር ሕመማቸው ከፍ ብሎ እንደነበርና ዕሮብ ለማስቀደስ አለመቻላቸውን በዚሁ ዕለት ማታ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ባሉበት ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡

በአቡነ ጳውሎስ መኖሪያ ቤት እና ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በርካታ ንብረቶች እና ቅርሶች እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን ኅልፈተ-ሕይወታቸው ከተሰማ ከሰዓታት በኋላ ሐሙስ ረፋዱ ላይ ፖሊስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ታሽጓል፡፡የመንበረ ፓትርያርክ እና የጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ከወትሮው ጠባቂዎች በተጨማሪ የአዲስ አበባ ፖሊስ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን ማየት ችለናል፡፡

ሐሙስ ጠዋት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ በመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለተገኙት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ምእመናንና ጋዜጠኞች የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ዜና ዕረፍት ካረጋገጡ በኋላ ሐዘኑን መግለጽ የፈለገ ወደ አዳራሹ እየዘለቀ ሐዘኑን ሲገልጽ ተስተውሏል፡፡ ይህ ሁኔታም እስከትናንትና ድረስ ቀጥሎ ውሏል፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈተ-ሕይወት ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ሲኾን በተገኙት አባቶች የፓትርያርኩ ሥርዐተ-ቀብር አፈጻጸም በቀዳሚ አጀንዳነት ታይቶ በትናንትናው ዕለት የፓትርያርኩ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመጪው ሐሙስ ይፈጸም የሚለው ውሳኔ ተላልፏል፡፡

አቡነ ጳውሎስ በምድራዊ ሕይወት

የ76 ዓመቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተወለዱት በያኔው የትግራይ ጠቅላይ ግዛት እንዳ አባ ገሪማ ገዳም ነው፡፡ የበፊት ስማቸውም አባ ገብረመድህን ገብረዮሐንስ ሲሆን በዚያው አካባቢ መንፈሳዊ ትምህርት በመማር በድንግልና መንኩሰዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የነገረ-መለኮት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት የነበራቸው ተማሪ በመሆናቸው ከወቅቱ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ በርካታ ሽልማቶች ተቀብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በግል ትጋታቸውና በወቅቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴውፍሎስ ምርጫ ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ አሜሪካ በሚገኘው የሩስያ ቅዱስ ቭላድሚር ኦርቶዶክስ ኮሌጅ የምስራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያን የነገረ-መለኮት ዲፕሎማ፣ በየል ዩኒቨርሲቲ ባችለር ኦፍ ዲቪኒቲ ዲግሪ፣ ቀጥሎም እዚያው አሜሪካ ከሚገኘው ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በነገረ-መለኮት የማስትሬት ዲግሪ፣ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በሃልዎተ-እግዚአብሔር የምርምር ጹሑፋቸው የዶክትሬት ዲግሪ መቀበላቸውን በመጋቤ ምስጢር ወልደሩፋኤል ፈታሒ በ2000 ዓ.ም በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተፃፈው “የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዓለም አቀፋዊ ሰውነት” የተሰኘ መጽሐፍ ይጠቅሳል፡፡

በወቅቱ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያስተምሩ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ባለመቀበላቸውና “በሀገሬ አገለግላለሁ” በማለት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ እስከ ጳጳስነት በደረሱ በተለያዩ ኃላፊነቶች በማገልገል ላይ ሳሉ ባለፈው መንግሥት ለሰባት ዓመታት በማረሚያ ቤት፣ ከዚያ በኋላ ለአንድ ዓመት በቁም ታስረዋል፡፡ ከቁም እስራቸው ነፃ ሲወጡም ወደ አሜሪካ እንደገና በመመለስ መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ከዚያ በፊትም እጅግ በጣም ያቀርቧቸው በነበሩት ፓትርያርክ አቡነ ቴውፍሎስ በመሾም አቡነ ጳውሎስ፤ የስዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ዲን በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአቡነ ቴውፍሎስ ፕትርክና ዘመን በቤተክርሰትያኒቱ የታሪክ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የስብከተወንጌል የበላይ ኃላፊ፣ እንዲሁም የቤተክርስትያኒቱ የልማትና ክርስትያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር እና የትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ከአሜሪካ በቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ በ1984 ዓ.ም በመመለስም ለፓትርያርክነት በመመረጥ ሃያ ዓመት አገልግለዋል፡፡ በሙሉ ስማቸው “ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ፣ ሊቀጳጳስ ዘ አክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስትያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ኃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚደንት” በመባል የሚታወቁት አቡነ ጳውሎስ ከጵጵስና እና ፕትርክና አሿሿማቸው ጀምሮ ውዝግብ ገጥሟቸዋል፡፡ በፓትርያርክ አቡነ ቴውፍሎስ አንብሮተ እድ መነኩሴው አባ ገብረመድሀን “አቡነ ጳውሎስ” ተብለው ሲሾሙ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትን አላማከሩም በሚል ቅሬታ ተነስቷል፡፡ ከ18 ዓመት በኋላ በ1984 ዓመተ ምህረት ፓትርያርክ ሲሆኑም የወቅቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት በመኖራቸው ሕግን የጣሰ ነው ተብሎ እንደነበርና ተቃውሞው እስከ ኅልፈተ-ሕይወታቸው ቀጥሎ እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ፓትርያርኮች ዳራ

የመጀመርያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ከፓትርያርክነት በፊት የኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ለመሆን ግብፃዊው የኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በሕይወት እያሉ አይቻልም በመባሉ ለአራት ዓመታት መጠበቅ የግድ እንደነበር በዲያቆን መርሻ አለኸኝ የተፃፈው “ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን” መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ በ1940 ዓመተ ምህረት የሸዋ ጳጳስና የደብረ ሊባኖስ እጨጌ፣ በ1943 የኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ በ1951 የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡ በ79 ዓመታቸው በ1963 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የስኳር ሕመምተኛ ነበሩ፡፡ ጣና ሐይቅ ገዳማትን ሲጐበኙ በነበረ የውሃ ጨረርም በመጨረሻዎቹ ዓመታት ዐይነስውር እንደነበሩ መጽሐፉ አትቷል፡፡ 12 ቀን ብሔራዊ ሐዘን ታውጆላቸው ነበር፡፡

በግንቦት 1963 ዓ.ም ሁለተኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት አቡነ ቴውፍሎስ ለአምስት ዓመታት በዚሁ ኃላፊነት ቤተክርስትያኒቱን ካገለገሉ በኋላ በጊዜያዊ መንግሥቱ በቁጥጥር ስር ውለው ለሦስት ዓመታት ከታሰሩ በኋላ በገመድ ታንቀው ተገድለዋል፡፡ አቡነ ቴውፍሎስን ለመጠየቅና ለወላይታ ደብረ መንክራት ተክለሃይማኖት ቤተክርስትያን አካባቢ ለሚያከናውኑት የልማት እንቅስቃሴ ርዳታ ለማሰባሰብ የመጡት አባ መላኩ ወልደሚካኤል አቡነ ቴውፍሎስ በእስር ላይ እያሉ በወቅቱ በመንግሥት ግፊት በተደረገ ምርጫ አምስት አባቶችን በማሸነፍ ፓትርያርክ ሲሆኑ ጵጵስና ስላልነበራቸውና ፓትርያርኩ በሕይወት በመኖራቸው መዋቅራዊ መሰላልን ባለመጠበቁ ጉርምርምታ ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህንኑ ቅሬታ ለማስወገድም መንበረ ፕትርክናውን ከመረከባቸው በፊት የጵጵስና ሥርዓት ተፈፅሞላቸዋል፡፡ ግንቦት 28 ቀን 1980 በሞት የተለዩት አቡነ ተክለሃይማኖት ፍፁም የሆነ የምንኩስና ሕይወት በመኖራቸውና ከድንች ያላለፈ ምግብ በመመገባቸው ሲያርፉ 25 ኪሎ ግራም ብቻ እንደነበሩና በባዶ እግር ይሄዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አቡነ ቴውፍሎስ በተገደሉ በ13ኛ ዓመት አፅማቸው ከልዑል አስራተ ካሳ ግቢ ጅምላ መቃብር ተቆፍሮ ወጥቶ፣ በሕይወት እያሉ አሠርተውት በነበረው የጐፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን ያረፈው፤ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሆነው      በዓለ-ሲመታቸውን በሚያከብሩበት ዋዜማ ሐምሌ 4 ቀን 1984 ዓ.ም ነበር፡፡ በማግስቱ    በዓለ-ሲመታቸውን አክብረው ሥራ የጀመሩት አቡነ ጳውሎስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በርካታ አስተዋፆዎችን ማበርከታቸውን የሚገልጸውን ያሕል፤ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ሕገወጥ ሥርዓት እንዲሰፍንበት አድርገዋል በሚል አነጋጋሪ ፓትርያርክም ነበሩ፡፡

 

 

Read 85655 times