Saturday, 13 March 2021 11:40

የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ የምርመራ ውጤት ይፋ አደራረግ ውዝግብ ፈጥሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ሁለተኛ አመት ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 1 ታስቦ የዋለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ የምርመራ ውጤት ይፋ አደራረግ በአሜሪካና ኢትዮጵያ መካከል ውዝግብ መፍጠሩን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ የምርመራ ቡድን አባላት የምርመራ ግኝቱን ከኢትዮጵያ የምርመራ ቡድን ግኝት ጋ ሳያመሳክሩ በራሳቸው ይፋ ለማድረግ ማቀዳቸውን የውዝግቡ መነሻ ሲሆን የኢትዮጵያ የአደጋ ምርመራ ቢሮ በበኩሉ፤ በቅርቡ የምርመራ ግኝቱን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
በምርመራ ስራው ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ጫና መፈጠሩን  የጠቆመው የኢትዮጵያ  የአደጋ ምርመራ ቢሮ፤  በአሁኑ ወቅት የምርመራ ግኝቱን ሪፖርት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የአሜሪካ የምርመራ ቡድን በተናጠል ሪፖርቱን ለማውጣት ማቀዱን የዘገበው አልጀዚራ፤ ችግሩንም በፓይለት ብቃት ማነስ ለማሳበብ ያቀደ የምርመራ ግኝት ይፋ ሊያደርግ እንደሚችል ምንጮቼ ነግረውኛል ብሏል፡፡
 መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተለያዩ አገራት ዜጎችን አሳፍሮ ከቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፊያ በመነሳት ወደ ኬኒያ ሲበር የነበረው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን፤ ቢሾፍቱ አቅራቢያ ሲደርስ ወድቆ የ167 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡ ባለፈው ረቡም  የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ሻማ በማብራትና የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ  አደጋው የደረሰበትን ሁለተኛ ዓመት አስበው እንደዋሉ ታውቋል፡፡

Read 1252 times