Saturday, 13 March 2021 11:52

ጠ/ሚኒስትሩ ህወኃት ለአፍሪካ አደገኛ ድርጅት እንደነበር ገለፁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በትግራይ ስላለው ሁኔታ ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ደህንነት ም/ቤት በላኩት የፅሁፍ መልዕክት ህወኃት ኢትዮጵያውያንን በዘርና በሃይማኖት ከፋፍሎ  ሲያባላ የኖረና ለአፍሪካም  አደገኛ የነበረ ድርጅት እንደሆነ ገለፀ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ከለውጡ አስፈላጊነት ጀምሮ  በለውጡ ውስጥ ስለታቀዱ የፖለቲካ ማሻሻያዎች በሰፊው በዘረዘሩበት  ህውኃት ከኢትዮጵያም አልፎ ለምስራቅ አፍሪካም ብሎም ለአፍሪካ  ጠቃሚ አልነበረም ብለዋል።
“ለውጡ ከመጣ በኋላ አስተዳደሬ ከጠባቡና ከፋፋዩ ህውኃት ጋር ትግል ሲያደርግ ነበር” ያሉት ጠ/ሚሩ፤ ህውሃት የነበረው ብቸኛው መሣሪያ አንዱን ብሄር ከሌላው ማጋጨት የእርስ በእርስ ጥርጣሬ መፍጠርና  ማባላት ነበር ብለዋል- በመልእክታቸው፡፡ አስተዳደራቸው አሁን የተፈጠረው ችግር እንዳያጋጥም ያላሰለሱ ጥረቶችን ማድረጉን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ ለውይይትና ንግግር በራችንን ክፍት ብናደርግም ህውሃት በተቃራኒው በመላ ሃገሪቱ የእርስ በእርስ ግጭቶችን ሲያነሳሳና ራሱ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆነባቸው የንፁሃን ግድያዎችን ሲያስፈጽም ቆይቷል” ብለዋል።
መንግስታቸው  ከዚያም ባለፈ እርቅና ውይይትን ፍለጋ ወደ መቀሌ ከአንድም ሁለት ጊዜ ሽማግሌዎች መላኩን፤ ነገር ግን ህውኃት የተላኩትን ሽማግሌዎች አልቀበልም ብሎ መመለሱንና በሃገር ውስጥ እየተከሰቱ ከነበሩ የንጹሃን ሞትና የሽብር ተግባራት ጀርባ አድፍጦ መቀጠል መምረጡን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ለህገ-መንግስቱ አልገዛም በማለት በትግራይ ያካሄደውን ምርጫ ተከትሎም ራሱን እንደ ወሳኝ ሃይል በመቁጠር፣ የክልሉን ልዩ ሃይልና ሚሊሻ የማስታጠቅና የማጠናከር እንዲሁም ለጦርነት የማዘጋጀት ተግባር ላይ ተጠምዶ መቆየቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአፍሪካ ህብረት በፃፉት መልዕክት አስገንዝበዋል።
ለጦርነት ራሱን ሲያዘጋጅ የነበረው ህውኃት ባልታሰበ ሰዓት በሰሜን እዝ ሃይል ላይ ጥቃት በመፈፀም ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል መፈፀሙን ጠቅሰው በዚህም ላይ ጦርነት መክፈቱን አስረድተዋል።
በኋላም በጦርነቱ እየተሸነፈ መሆኑን ሲረዳ የህዝብ መሰረተ-ልማቶችን ወደ ማውደምና ፣  ወደ ዘረፋ መግባቱን እንዲሁም በአደገኛ ወንጀል  ታስረው የነበሩ ከ10ሺ በላይ እስረኞችን በመልቀቅ በህዝቡ ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዲፈፅሙ ማድረጉን በፅሁፋቸው አብራርተዋል።
ከእስር በተለቀቁ ወንጀለኞችና በራሱ ታጣቂ ሃይሎች በህዝብ ላይ ዘረፋና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን በአጽንኦት ያስገነዘቡት ጠ/ሚኒስትሩ ይህን በተመለከተም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ምርመራ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የህግ ማስከበሩን ሂደት ተከትሎ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች መንግስታቸው ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም በዝርዝር ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ትግራይን የማረጋጋት ተግባር በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና በፌደራል መንግስት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ሃገሪቱን ወደ ዘላቂ የእኩልነትና ዲሞክራሲ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን በፅሁፋቸው አመልክተዋል፡፡
ህውኃት ላለፉት 30 ዓመታት ለከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲው እንዲመቸው ብሎ በኢትዮጵያውያን መካከል የዘራውን የብሔርና ሃይማኖት ክፍፍል ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ከስር መሰረቱ ለመንቀል መንግስታቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው አስገንዝበዋል፡፡

Read 12516 times