Saturday, 13 March 2021 13:17

ኮሮና በ70 አገራት ብቻ ከ17 ሺህ በላይ የጤና ሰራተኞችን ለሞት መዳረጉ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

        የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 70 አገራት ውስጥ ብቻ ለሞት የዳረጋቸው የጤና ሰራተኞች ከ17 ሺህ ማለፉንና ትክክለኛው የሟቾች ቁጥር ከዚህም በእጅጉ ሊልቅ እንደሚችል ሶስት አለማቀፍ ተቋማት ከሰሞኑ ባወጡት ሪፖርት ማስታወቃቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ፐብሊክ ሰርቪስስ ኢንተርናሽናል እና ዩኤንአይ የተባሉት ተቋማት በጋራ ያወጡትን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ባለፉት 12 ወራት በአለማችን በየግማሽ ሰዓቱ በአማካይ አንድ የጤና ሰራተኛ በኮሮና ሳቢያ ለሞት ተዳርጓል፡፡
መንግስታት ለጤና ሰራተኞች በአስቸኳይ የኮሮና ክትባቶችን መስጠት ካልጀመሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጤና ሰራተኞች ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ ሲሉ ያስጠነቀቁት ተቋማቱ፤ ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ህሙማንን ለመታደግ ህይወታቸውን በመስጠት ላይ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጤና ሰራተኞች ህልውናም አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ጥናት ካደረጉባቸው 70 የአለማችን አገራት መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸው የጤና ሰራተኞች ለሞት የተዳረጉባት ቀዳሚዋ አገር አሜሪካ መሆኗንና በአገሪቱ በኮሮና ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት የጤና ሰራተኞች ከ3 ሺህ 507 በላይ እንደሚደርስም በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
በሜክሲኮ 3 ሺህ 371፣ በብራዚል 1 ሺህ 143፣ በሩስያ 1 ሺህ 131 እንዲሁም በብሪታኒያ 931 የጤና ሰራተኞች በኮሮና ተጠቅተው ለሞት መዳረጋቸውንም ሪፖርቱ ያብራራል።
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ፤ ለድሃ አገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለማቅረብ የየያዘውን ዕቅድ ለማሳካት 1 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፣ የበለጸጉ አገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉለት መጠየቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ድርጅቱ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2021 ለአለማችን አገራት በድምሩ 2 ቢሊዮን የኮሮና ክትባቶችን ለድሃ አገራት ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚህም ውስጥ 1.3 ቢሊዮን የሚሆነውን ለድሃ አገራት ለማቅረብ ማቀዱንም አክሎ ገልጧል፡፡ ወደ አፍሪካ ስናቀና ደግሞ፣ ኮሮናን በማናናቅና ለወረርሽኙ ተገቢ ትኩረት ባለመስጠት የሚወቀሱት የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ከሰሞኑ በቫይረሱ ተጠቅተው ሆስፒታል መግባታቸውን የዘገበው አልጀዚራ፤ በከፋ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡
ከአንድ ሳምንት በላይ ከአደባባይ ርቀው በመቆየታቸው ብዙ ነገር ሲወራባቸው የሰነበተው ማጉፉሊ፣ በናቁት ቫይረስ ተይዘው ኬንያ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው፣ ወደ ህንድ መወሰዳቸውንና  ህመሙ ጸንቶባቸው እንደሚገኙ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቱንዱ ሊሱ ቢናገሩም፣ የአገሪቱ መንግስት ግን በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ አለመስጠቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡


Read 3184 times