Monday, 15 March 2021 00:00

ፓርቲዎች ቃል ይግቡ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  “የዋጋ ንረት አልፈጥርም። አለቅጥ ገንዘብ አላትምም”!
                   
               - በ4 ዓመት ውስጥ፣ የሸቀጦች ዋጋ እጥፍ ሆኗል::
- በ2009 ዓ.ም አጋማሽ ላይ፣ በ1000 ብር ስትገዙት የነበረ አስቤዛ፣ ዛሬ 2000 ብር ይፈጅባችኋል።
“ዋጋ ናረ፤ ኑሮ ተወደደ” የሚባለው አለምክንያት አይደለም፡፡ በእጥፍ ዋጋ ሲንር፣ ወጪ እጥፍ ይበዛና፤ ኑሮ ተወደደ ይባላል።  በሌላ በኩል፣ዋጋ ሲንር፣ገንዘብ ረክሷል ማለት አይደል?  ኪስ የገባ ብር፣በደመወዝ ማግስት ብን ብሎ ይጠፋል፡፡ ኪስ ሲራቆት፣ አስቤዛ በግማሽ ስለሚቀንስ፣ ኑሮ ተጎሳቆለ፤ ተናጋ  ይባላል።
ምን ይሔ ብቻ! የዋጋ ንረት፣ የቁጠባ ገንዘብን ያሟሟል። ከአራት ዓመት በፊት በባንክ የቆጠባችሁት ገንዘብ ፣ ዛሬ በግማሽ ረክሷል። ከመኖሪያ ቤትና ከመኪና ጀምሮ፣ እስከ አስበቤዛና ፍጆታ ድረስ፣ የአብዛኛው ነገር የገበያ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል። ብዙ ሰው፣ በባንክ ገንዘብ ከመቆጠብ ይልቅ፣እንደምንም ተጣጥሮ መኪና ገዝቶ ለማስቀመጥ የሚሟሟተው ወዶ አይደለም። ባንክ ካስቀመጠ፣ አይኑ እያየ ገንዘቡ እየረከሰ፣ መኪና ለመግዛት ይቅርና የመኪና መለዋወጫ ለመግዛትም አቅም ያጣል፡፡
 የዋጋ ንረት፣ ልላም ጣጣ ያመጣል። ጅምር ስራዎቻችንና የግንባታ እቅዶችን ያደናቅፋል፣ ከንቱ ያስቀራል- የዋጋ ንረት። “በመቶ ሺብር እሰራዋለሁ” ብለው የጀመሩት ውጥን፣ ሁለት መቶ ሺብር የሚፈጅ ይሆናል። በ5 መቶ ሚሊዮን ብር የታቀደው ፕሮጀክት፣ ወደ ቢሊዮን ብር ያሻቅባል። በጊዜ ካልተጠናቀቀ ደግሞ፣ እየባሰበት ፣ ተጨማሪ ብክነት ይገጥመዋል።
የስራ ጅምርና የኤንቨስትመንት ውጥን፣ በዋጋ ንረት ሲመሳቀል፤ ኪሳራው ሲደማመር፣  የአገርን ኢኮኖሚ ለቀውስ ይዳርጋል፡፡  በአንድ በኩል ኪሳራ ነው። ብረታ ብረት ሁሉ፤ ከአርማታ እስከ በር እጀታ ድረስ፤ ወጪው እየተቆለለ ጥሪትን ያሟጥጣል፡፡ የባንክ እዳና ወለድ ይከማቻል።
በሌላ በኩል ግንባታው ሳይጠናቀቅ፣ ወደ ስራ ሳይገባ፣ የታቀደው ምርት በሃሳብ ብቻ ይቀራል፤ሃብትና ንብረት የፈሰሰበት ፋብሪካ ለፍሬ አይበቃም። የስራ እድልም ፣ ከተስፋ ሳይሻገር፣ ሳይፈጠር ይመክናል። ይሄ፣ ቀላል ችግር፣ በዋዛ ተጠቅሶ የሚታለፍ ፈተና አይደለም።
የስራ እድል እጥረትና እጦት፣ የአገራችንን የኢኮኖሚ ቀውሶችን በሙሉና የኑሮ መከራዎችን ሁሉ ጠቅልሎ የሚያሳይ ፣ ከዓመት ዓመት የሚጋሽብ፣ እጅግ ክፉ  አደጋ ነው። የዋጋ ንረት፣ የስራና የኢንቨስትመንት ጅምርን እያመሳቀለ፣ የስራ እድል እጦትን እያከበደ፣ የኑሮ ምሬትን ያባብሳል፡፡  በሌላ አነጋገር፣ የዋጋ ንረት፣ “ጎጂ” ብቻ ሳይሆን፣ “አደገኛ”  እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ይህም ብቻ አይደለም።
ከአዲሱ ሚሊንየም ዋዜማ ወዲህ፣ ለበርካታ ዓመታት እየተደጋገመ፣ ከዋጋ ንረት ጎን ለጎን ምን ሲፈጠር እንደነበር አስታውሱ።
የዋጋ ንረትን በየአቅጣጫው ወደዚያና ወደዚህ የማላከክ የፕሮፖጋንዳ ሩጫ ይጀመራል፡፡
“አጭበርባሪ ደላሎች”፣ ”ስግብግብ ነጋዴዎች፣ “አሻጥረኞች የጅምላ አከፋፋዮች”፣ “ስርዓት አልበኛ ቸርቻሪዎች”፣ የሚሉ ውንጀላዎች ሌት ተቀን ይራገባሉ።  ወሎ ሳያድር፣የመንግስት የዋጋ ተመን፣ ከዚያም “የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ” ይጧጧፋል።
“ከድስቱ ወደ እሳቱ” ነው ነገሩ፡፡  ጥፋትን የማላከክና የጅምላ ውንጀላ፣ ችግርን ያባብሳል እንጂ፣ ችግርን አይፈታም፡፡
የዋጋ ተመንና የቁጥጥር ዘመቻ፣ የዋጋ ንረትን ከማቃለል ይልቅ፣ የገበያ ሽሚያንና የሸቀጥ እጥረትን ያስከትላል፡፡ ይሄኔ፣ አገርና መንግስት ወደ ህሊና ቢመለሱ ደግ ነበር፡፡
የዋጋ ቁጥጥር ዘመቻ ችግርን እንደሚያወሳስብ እየታየም፣ ዘመቻውን ያቀጣጥሉታል፡፡ እንዴት? የአምራቾችና የነጋዴዎች መጋዘን ይበረበራል፡፡” ስንዴ አከማቸ፣ዘይት አጓጓዘ” እየተባለ፣ንብረት ይታገታል፤ በመንግስት ሚዲያ “እየተወነጀለ በቲቪ ይፈረድበታል”፡፡ መታሰርም ይመጣል፡፡ ንግድ ቤቶች ይታሸጋሉ፤ እንዳይሰሩ ይታገዳሉ፡፡
“የንግድ ፈቃድ” ይነጥቃሉ
የንግድ ፈቃድ?
የስራ ፈቃድ?
 ሰርቶ መኖር፤ ፈቃድ ያስፈልገዋል ማለት ነው? ሰርቶ መኖር፣ ….በህዝብ ይሁንታ ወይም  በመንግስት ፈቃድ የሚገኝ መብት ይመስል! የንግድ ስራ ምዝገባ “ማለት፣ “የንግድ ስራ ፈቃድ” እንደማለት መቆጠሩ፣ ቅንጣት አይገርመንም?
የልደት ወይም የጋብቻ ምዝገባ፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ፣ ”የልደት ፈቃድ”፣ “የጋብቻ ፈቃድ” የሚል ትርጉም ቢይዝ ግን ይገርመናል? ምን ልዩነት አለው? አምርቶ ጋግሮ፣ ሸጦ ገዝቶ የመኖር መብት፣….. በጋብቻ ቤተሰብ ከመመስረትና ልጅ ከመውለድ መብት በምን ያንሳል? እንደሚያንስ ብናስብ ነው ወይም እንደችሮታ እንጂ እንደ መብት ባይቆጠር ነው፤ “የስራ ፈቃድ”፣ “የንግድ ፍቃድ” ተሰጠ፣ ተነጠቀ፣ታደሰለት ተሰረዘበት የምንለው፡፡
 የጥፋት ማላከኪያ፣ የጥፋት ማሳበቢያ ስንፈልግ ደግሞ፣ “ስግብግብ ነጋዴ” እያልን  እንዘምትበታለን - ማሸግ፣ መቅጣት፣ መሰረዝ፣ ማሰር፣ …. ከዚያስ?
 እጥፍ ድርብ ጥፋትና ኪሳራ በሉት፡፡
እህል አምራችም ሆነ ባለ ፋብሪካ፣ ጅምላ አከፋፋይም ሆነ የችርቻሮ ነጋዴ፣ …..እንደማንኛውም ሰው፣ በግል ተግባሩ በህግ መዳኘት እንዳለበት ማሰብ  አንድ ነገር ነው፡፡ “ስግብግብ ነጋዴ” እያል መዝመት ግን ሌላ ነገር ነው፡፡ ሰርቶ የመኖር፣ መብትን ያጥሳል፡፡ ይሔ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ምን ይሔ ብቻ!
ነጋዴ ላይ መዝመት፣ በሰው ላይ የሚፈፀም ጥቃት የመሆኑ ያህል፣ በራሱም ላይ  ኪሳራ ነው፡፡ ከመነሻው በነጋዴ ሳቢያ የሚከሰት የዋጋ ንረት የለማ፡፡ የዋጋ ንረትን በነጋዴ ላይ ማላከክ፣ የዋጋ ተመንና ቁጥጥር ማወጅ፣ መጋዘኖችን መበርበርና መደብሮችን ማሸግ፣ ገበያን ያመሰቃቅላል፣ ኢኮኖሚን ያቃውሳል እንጂ፣ የዋጋ ንረትን አያስወግድልንም፤ አያቃልልንም፡፡ በሌላ አነጋገር ሰርቶ የመኖር መብት መጣስ ትልቅ ጥፋት ከመሆን አልፎ፣ ኪሳራም ነው፡፡
የዚህ ሁሉ መድሃኒቱ፣ የዋጋ ንረት ከስረ መሰረቱ መፈወስና መንቀል ነው፡፡ ይህን የምንፈልግ ከሆነ፣ ከምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች፣ቃል እንዲገቡ እንዲጠይቃቸው። “የዋጋ ንረትን አልፈጥርም፤አለቅጥ ገንዘብ አላትምም” ብለው ምለው ይገዘቱ ስልጣን የያዘ ፓርቲ፣ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ በየአመቱ በገፍ ካላሳተመ፣ የዋጋ ንረት አይፈጠርም ከጊዜያዊ ጥቃቅን የዋጋ ውጣ ውረድ በስተቀር፣ የዜጎችን ሕይወት የሚያጎሳቁል የኑሮ ውድነት አይከሰትም፡፡

Read 9483 times