Monday, 15 March 2021 07:57

የቆሻሻ ጀልባው ካፒቴን - (ወግ)

Written by  ሌሲሳ
Rate this item
(2 votes)


          ቆሻሻ ያው ቆሻሻ ነው፤ ይጣላል።
እኔ ግን ቆሻሻ ህይወቴ ነው። ስራ ነው። ቀደም ሲል ጎዳና ተዳዳሪ ነበርኩኝ፤ የሱስ ብዛት ነው ጎዳና ያወጣኝ። በመሰረቱ የክፍለ ሀገር ልጅ ነኝ። መቼ አዲስ አበባ እንደመጣሁ ሁሉ ትዝ አይለኝም። በየጫት ቤቱ እየዞርኩ ገረባ ከሰው እግር ስር እለቅም ነበር። በኋላ ጫት ቤቶቹ መሀል ከተማ ላይ ተዘጉ። ገራባውና ጫት ቃሚው ወደ ከተማ ዳር ተገፋ፤ እኔም ሳላስበው ወደ ሀያት አካባቢ ራሴን አገኘሁ።
ከዚህኛው ቀይ የቆሻሻ ገንዳ ጋር ያለኝ ቁርኝት እንደዚሁ በአንድ ቀን የጀመረ አይደለም። ገንዳው ራሱ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ገና አዲስ ነበረ። ኮንዶሚኒየሞቹ ተሰርተው እንዳለቁ የገንዳው ስራም ተሟሟቀና ቆሻሻን ሰው ቢጠየፈውም ለኔ ግን ህይወቴ ነው።
እኔና ጡሩቄ ነበርን ገንዳውን ቤታችን መጀመሪያ ያደረግነው። በኋላ እነ ከርትስ …እነ ጠንበለል… እነ ቲንቦና ቀፋይ መጡ። እንደ በኩረትነታችን ሳንደራጅ ጋውን የለበስነውም እኔ እና ከርትስ ነን። ከተማ ሳለሁ ገራባ በመቃም ብዛት እንደ እብድ ነበር የምቆጠረው፡፡ እኔም ሰው እንደሚያየኝ ራሴን ማየት ጀምሬ ነበር። ቀዩ ገንዳ ላይ ስራ ስጀምር እየነቃሁ መጣሁ። ጥሩ ጫት መቃም ጀመርኩኝ። አቅሜ ሲፈቅድ ደህና መጠጥም እቀማምሳለሁኝ። የአካባቢው ሰው ያውቀኛል። እኔም ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁኝ። ገንዳው ያስተዋወቀኝ ጓደኞቼ ካፒቴን ይሉኛል። ጓደኞቼ በሚጠሩኝ ስም የአካባቢው ሰው ይጠራኛል።  እኔም ገንዳውን እንደ መርከብ ቆጥሬ ያወጡልኝን ስም እወደዋለሁኝ።
ከእያንዳንዱ ቤት የሚወጣው ቆሻሻ እንደ እንደ ነዋሪዎቹና አኗኗራቸው ይለያያል። ሼክስፒር መቼም ያላለው ነገር የለም፤ ምናልባት “ቆሻሻህን አሳየኝና ማን እንደሆንክ እነግርሃለሁኝ” ያለው እሱ ሊሆን ይችላል። ጭንቅላቴ ራሴ በምፈጥራቸው ጥቅሶች የተጨናነቀ ነው። ግን ጥቅሶቼን በእኔ ስም ማቅረብ ስለምፈራ ለማውቃቸውና አንቱታ ላተረፉ ሰዎች እሰጣለሁኝ። ወይ… አባባ ተስፋዬ የተናገሩት--  ነው እላለሁኝ….  ካልሆነ ሼክስፒር---ብቻ እንደመጣልኝ። የጋሽ አበራ ሞላን ስም ከተጠቀምኩኝ ግን የእውነት የማምንበት  ጉዳይ ነው ማለት ነው። ሰው በአባትና እናቱ ስም እንደሚማማለው፣ እኛ የቀዮ ገንዳ አባላት ደግሞ በጋሽ አበራ ሞላ ስም  ማልን ማለት፣ በማተባችን እንደማልን እንቆጥራለን። አሁን ቤተሰባችን እኛው እርስ በራሳችን ሆነናል። ገንዳው ደግሞ እንደ ሀገራችን ነው። ሀገራችን የምትተዳደርበትን በጀት የሚሰጡን በቆሻሻ መልክ ነው። እነሱ ተርፏቸው የሚወረውሩት ሁሉ ለእኛ የማይታወቅ ገፀ በረከት ይዞልን ይመጣል።
ትንሽ ትምህርት ቀምሻለሁ መሰለኝ ቆሻሻን የምመለከተው በተለየ አኳኋን ነው። የቆሻሻው ገንዳ የሚሞላበት ወቅት ደንበኞቼ ደሞዝ ወይንም አንዳች ምርት እንደሚሰበስቡበት የመኸር ወቅት ተመስሎ ይታየኛል። በገንዳው አጠገብ የሚያልፉ ሰዎች፣ አፍንጫቸውን ይዘው ወይም ምራቃቸውን እየተፉ ሲያልፉ፣ እነሱ መመማረራቸው ይገባኛል። እነሱ የማይገባቸው በእኛ በኩል ያለው ግልባጭ ነው። እነሱ ከተለያየ አቅጣጫ አዋጥተው ያመጡት ቆሻሻ እንደተከመረና መልሶ እየሸተታቸው እንደሆነ አያስቡም። የቆሻሻ አለም አስተሳሰብ በንፅህና ከተያዘው ዓለም ይለያል። ንፁህ የሆነው ዓለም ውስጥ የሚኖሩት ግን ይኼንን ማሰብ አይችሉም። ቆሻሻ ባይኖር ንፅህና እንደማይገኝ አይታያቸውም።
የዓመት በዓል ወቅት ስጋው፣ ቅንጥብጣቢው፣ አጥንቱና ቆዳው መጥቶ ይከመራል። የእነሱ ጥጋብ እኛ ዘንድ ሲመጣ የሚከረፋ ሽታ ሆኖ ነው። እያንዳንዱን የፌስታ ቋጠሮ እየፈታን ያወጣነውን ገፀ ቆሻሻ በጥንቃቄ  እንለየዋለን። ቆሻሻም ልክ እንደ ሰዎች በሁለት ይከፈላል።  የተማረ እና ያልተማረ። ወይንም የሚጠቅም እና ዋጋ የሌለው …ወይንም ደረቅ እና ርጥብ።
በንፁሁ የዓለም ክፍል የሚኖሩ  ብዙሃንን…ቆሻሻን ደረቅ እና ርጥብ ብለው ነው የሚፈርጁት። ርጥቡ ከደረቁ የበለጠ ያፀይፋቸዋል። በፌስታል ይዘውት መጥተው ቆሻሻ መጣያው ጋር ማድረስ ሰንፈው፣ ከገንዳው ከንፈር ውጭ ጥለውት ይመለሳሉ። ራቅ ካለ ቦታ ቆሻሻ በጋሪ ይዘው የሚመጡም እኛ ዘንድ ያራግፋሉ።
እኔ ግን እያንዳንዱን የቆሻሻ ቋጠሮ በብልጭልጭ ወረቀት እንደተሸፈነ ስጦታ ነው በጉጉት የምከፍተው። ስጦታው ከማን እንደመጣ ባላውቅም… በውስጡ የያዘውን መርምሬ እገምታለሁኝ። ልክ ሀኪም ሰገራና ሽንት መርምሮ የታካሚውን በሽታ እንደሚያውቀው፣ እኛም የገንዳው አባላት ቆሻሻውን በአጠቃላይ ገልብጠን የጣዩ ማንነት ይገባናል። የጠገበ ወይንም በመጥገብ ላይ ያለ ብለን፣ ምቾትንም በንዑስ ክፍል እንመድበዋለን። አንዳንድ የሚጣሉ ነገሮች ተስፈኛ… በማደግ ላይ ያሉ ድሆች---ገንዘብ አውጥተው ለመግዛት አቅም የማይኖራቸው ይሆናሉ። ለዚህ ነው… ቆሻሻ እንደ ስጦታ እሽግ ነው የምለው።
የውስኪ ጠርሙስና የተበላሹ ስልኮች፣ የተሰበሩ ቴሌቪዥኖች እስከ ሚሞሪ ካርዶች፣… ዝርዝሩ ማለቂያ የለውም። የተሻለ ሶፋ ሲገዛ … የድሮውን ቆሻሻ መጣያው አጠገብ እንደ ሌባ ሰው ሳያየው አውርዶ የሚሄድም አለ። እኛ በፈረቃ ነው የምንተኛው እና የምንነቃው። መታየት የማይፈልግ ቆሻሻ አምጭን አናስጨንቀውም። እንዳላየን ሆነን እናልፈዋለን። ሰው የተመገበው ነገር  በሚጥለው ቅሪት እንደሚታየው፣ ቆሻሻም የጣዩን ማንነት ይገልፀዋል። ቆሻሻውን በሁለተኛ አካል በሰራተኛቸው አማካኝነት ቢጥሉም፣ የሰራተኛዋ አሳዳሪ ማን እንደሆነ አይታወቅም ማለት አይደለም።
አንዳንዴ እንደ ሰላይ ያደርገኛል። በተደጋጋሚ ስልኩን ጨፍጭፎ ሰብሮ የሚወጣ ሰውዬ ነበረ። ግን ከስልኩ ጋር ብዙ የጂን ጠርሙሶች ተሰባብረው ስለሚገኙ ማን ሰውየውን አዞት ስልኩን እንደሚያሰብረው ለማወቅ አልቸገረም። ስንት ሴቶች ለአቅመ ሄዋን እንደደረሱ በሚጣለው የንፅህና መጠበቂያ አማካኝነት … ወይንም ስንት ህፃናት ተወልደው በማደግ ላይ እንደሆኑ በዳይፐሩ ምጣኔ ማወቅ ይቻላል። ግን እዛ ደረጃ መውረድ አልፈልግም፡፡ መውረድ አልፈልግም ማለት… ከምንም አይነት ድብቅ ቆሻሻ መወገድ በኋላ ንፅህና እውን እንደሚሆን አይገባኝም፤ አልያም አላውቅም ማለት አይደለም።
አንዳንድ ደንበኞች ቤታቸው ድረስ ወስደውኝ እንዲወገድ የሚፈገልጉትን ነገር ወደ መርከቡ መውጣት ሳያስፈልጋቸው አነሳላቸዋለሁኝ። እነሱ ማየት የማይፈልጉት ወይንም የሚፀየፉትን እቃ የሌላ ሰው አይን ማረፊያ ሊሆን እንደሚችል ባይገባቸው ነው ብዬ አዝንላቸዋለሁኝና፡፡
ሌሎች ደግሞ ፈጽሞ እቃ መጣል የማይወዱ አይነቶች አሉ። ግን የሰበሰቡትን ቆሻሻ መኖሪያ ሲቀይሩ የግድ መጣል ሲኖርባቸው፣ እነሱም ወደ እኛ ጎራ ይላሉ። የፕላስቲክ ውሃ ምን ያህል እንደተሸጠ አምራቹ ቢያጭበረብር እንኳን ቆሻሻ ሆኖ ሲመጣ ስሌቱ ይታወቃል፡፡ ምንም አይነት መረጃ አይጠፋም።  የማህበረሰቡ ገቢ፣ ቆሻሻ ገንዳ ላይ ወጪ ሆኖ ይወጣል፡፡
ጋዜጣና መፅሔት እንደ እኔ የሚያነብ የለም። ገዝቼ ሳይሆን ቆሻሻ ተብሎ የተጣለውን ሰብስቤ ነው፣ የራሴን መጠነኛ  ሼልፍ ከወዳደቀ ብሎኬት መደርደሪያ ሰርቼ ያነፅኩት። አንዳንዴ ጥሩ የአማርኛ መጻህፍት ይገኛሉ። ገጻቸው ተሟልቶ ባያውቁም፣ የተገነጣጠለው ብቻ ራሱ መጠነኛ የእውቀት ረሀቤን ያረካኛል፡፡ ተሰባስቦ የተገጣጠመውን አንብቤ… የጎደለውን ደግሞ ከራሴ ህልም እሞላበታለሁኝ፡፡
በቀዩ ቆሻሻ ገንዳ ሁሉም ነገር ሙሉ ነው። ሰውን የሚረብሸው ጠረን ለእኛ በሂደት ጥሩ መዐዛ ተደርጎ ተቀባይነት አግኝቷል። “ሰው በኪሱ ይዞ ከሚዞረው ብር የበለጠ አይሸትም” ብዬ አፌን ሞልቼ ከገንዳው ጓደኛዬ ጋር ተከራክሬያለሁ። ዋናው የሚሰጠው ጥቅም ነው፡፡ ጥቅም የሚሰጥ ነገር ቢሸትም ሽታው ከጥቅሙ ጋር ተወራርዶ የበለጠ ዋጋ ያለው… ዋጋ ቢሱን ጠረን ይውጠዋል፡፡
ግን ልብ በሉልኝ፤ መጥፎ ሽታን ከጥሩ ሽታ መለየት አንችልም ማለቴ አይደለም፡፡ ጥሩ ሽታ የመጥፎውን ያህል ለቆሻሻ ባለሙያ ዋጋ አያወጣም ማለቴ ነው፡፡ ጥሩ ጠረንንም ሆነ መልካም ነገርን ማየት ይወድልኛል። መልካም ጠረን የሚመጣው ግን መጥፎ ተወገዶ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ማስወገዱ የኔ ስራ ነው፡፡ ማስወገድ ደግሞ ስራ ይፈልጋል፤ ትጋት ይፈልጋል፡፡ ስራን በፍቅር መውደድ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን  ሳያቸው ንፁህ ሰዎች ላይ የእኔም አሻራ እንዳለ አስብና እኮራለሁኝ፡፡
አንዳንዴ የሚጠቅም ነገር ይዘው ወጥተው በነፃ የሚሰጡኝ  ጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ እጃችውን ዘርግተው ሊጨብጡኝ ይሞክራሉ፡፡ እንደ ሰው ስለቆጠሩኝ ደስ እያለኝ፣ የእጄን አንጓ ወደ ላይኛው ክንዴ አካባቢ እሰጣቸዋለሁ፡፡ በጣም ያልቆሸሸ የመሰለኝን የጋወኔን እጅጌ ክፍል፡፡ ብዙ ጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ ባለጌዎችም እንደዚሁ፡፡ የቆሸሸ ሽንት ቤታቸውን ጓሮ አርቀው ቀብረው፣ ሳሎናቸውን የሚያቆነጁ ሰዎች በእኔ ዘንድ ከባለጌዎቹ ተርታ ነው የሚመደቡት፡፡
 ቆሻሻውን በደንብ ይዞ የማይመጣ … ንፁህ ነኝ ለማለት ሲውተረተር እስቅበታለሁኝ። ማስቲሽ ማሽተትን አውግዘን በገንዳው ቤተሰብ በመሃላ አፅድቀናል፡፡ ግን አንዳንዴ እሱም ሲያምረኝ… ከጫማ ቤት የሚመጣውን ቆርቆሮ እንደ ጥንቱ የጎዳና ህይወቴ ማስታወሻ ደብተር፣ ቆርቆሮውን ከፍቼ እወጋለሁኝ፡፡ በተረፈ አረቄ መጠጣትም  በመጠኑ ካደረግን ቆይተናል፡፡ ደስተኛ ስለሆንን ብዙ መስከር አንፈልግም፡፡
ከሆቴሎች የሚመጣ ምግብን ቀይጠን ተሰብስብን እንበላለን፡፡ ልክ እኛ ከተለያየ አቅጣጫ እንደተሰባሰብነው ሁሉ… ከተለያየ አቅጣጫ የተሰባሰቡ ውሾችም እንደ እኛው ገንዳውን ቤታቸው አድርገዋል። የአመት በዓል ሽታን በገንዳው የሚያልፍ ሰው ሲያማርር፣ ውሾቹ ግን በአጥንት ተከበው፣ ፋፍተው እንቅልፋቸውን የሚያጣጥሙበት ወቅት ነው፡፡ ከእኛ ጋር ብዙ ነገራቸው ስለሚመሳሰል እኛም ውሾቻችንን እንወዳቸዋለን፡፡ እንደ ቤት ውሻ ገንዳውን ከበው ይጠብቃሉ፡፡ የሚጠብቁትን ግን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በማናቸውም ሰዓት ቆሻሻ ለመጣል የሚመጣ ሰውን ፈፅሞ እንዳይተናኮሱ ሆነው በደመ ነፍሳቸው ሰልጥነዋል፡፡ ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ ከገንዳው ላይ የሆነ ነገር ሲያተረማምስ ያገኙትን ሰው፤ እስከ አስፋልቱ ጫፍ አሳደውት ተመልሰዋል፡፡ ወደ ገንዳው ቆሻሻ ይዞ የሚመጣ አይነካም፤ ምንም ሳይዝ የሚመጣ ግን የሆነ ነገር ይዞ ለመመለስ የሚታክርን ነው የማይወዱት፤ እንደ ቆዳ ቀለማቸው ስም ሰይመንላቸዋል፤ ከእኛው ጎን ይተኛሉ፡፡ ሴቶቹ ውሾች ምንም ሳይሠስቱና ሳይሳቀቁ በገንዳው ዙሪያ ይወልዳሉ፡፡ ቡችሎቹንም ምንም ሳንሰስት እኛም እናሳድጋለን፤ የሚገዛ ከተገኘም እንሸጣለን፡፡
በቀዩ ገንዳ ዙሪያ ብቻ ህይወት ሙሉ ነው። ምናልባት ክርስቶስ፤ “የሰማይ አእዋፋት አይዘሩም አያጭዱም” ያለው በቆሻሻ አንፃር ሲተረጎም፣ ስለ እኛ እየተናገረ ሊሆን ይችላል ብዬ ስመረቅን እጠራጠራለሁ፡፡ አንዘራም አናጭድም ግን ሌላው አጭዶ ዘርቶ ያመጣውን ግርድ እንሰበስባለን፤ የተዘራና የታጨደ ብቻ አይደለም፤ ቆሻሻ ተብሎ የተጣለም ዋጋ እንዳለው ከራሴ ህይወትና ከመሰሎቼ አይቻለሁ፡፡
መጠነኛ እቁብ አለን፡፡ ሁላችንም ያጠራቀምነው ተቀማጭ ገንዘብ አለን። ወደፊት ህልማችን ንፁህ ሆኖ፣ በንፁህ ቤት ውስጥ መኖር ግን አይደለም፡፡ ማደግ እንፈልጋለን ግን ከቆሻሻ ርቀን አይደለም፤ ከቆሻሻ ተራርቆ ንፅህና የለም፡፡ እና ሼክስፒር፤ “ከቆሻሻ  ተራርቆ ንጽህና ቅዠት ነው” የሚል ጥቅስ እንዲጽፍልኝ እፈልጋለሁ፡፡ የእኛ ገንዳ አንድ ቦታ ላይ የምትገኝ ገፅታ ናት፤ ገንዳው ሲሞላ ይወሰዳል፡፡ ከተማው ጫፍ ላይ ትልቁ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ አለ፡፡ ትልቁ ህልሜ፤ ትልቁ… የቆሻሻ ማከማቻ ላይ መስራት ነው፡፡ ይሄ  ትልቅ ደስታ ያጎናጽፋል ብዬ አምናለሁኝ፡፡ ግን ለትልቁ አለም እስክታጭ ድረስ እዚሁ ባለሁበት ስፍራ ላይ መኖሬን እቀጥላለሁኝ፡፡




Read 2120 times