Monday, 15 March 2021 08:04

የአዲስ ዘመን ቀለማት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዘመን መልኩን ቀይሮ አዲስ ቀለም ለብሶ፣ አሻራውን በትዝታ ትቶ ሲሄድ፣ የሰው ልጅ የአዲሱን ተስፋ ጭራ እየተከተለ ይዘምራል። ምድር እንኳ ያለፈ ዐመት ቀለሟን ቀይራ፣ ለዛዛና ደረቅ አትክልቷ በአረንጓዴ ቀለም ነጥራ በቢጫ አበቦች ሸልማ ትመጣለች፡፡
ሰው ሕይወት እንዳይሠለቸው የራራች ይመስል ተፈጥሮ አዲስ ጐፈሬ አበጥራ፣ በወንዞችዋ መዝሙር ከበሮ እየደለቀች፣ ተስፋውን ታነቃቃለች፤ በክረምቱ ዶፍ የጨለሙ ሠማያት በብርሃን ፀዳል አሮጌ ሽርጣቸውን አውልቀው፣ ዐይኖቻቸው በርቶ ሲመጡ፤… አድማሳት በአዲስ ምኞት ሠክረው ይደንሳሉ፡፡
በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን መስከረም ወር ስትመጣ ክረምቱ እንዲሁ አይሸኝም፤ ጭጋጉ በመዘውር አይሸሽም።… በቡሄ፣ በእንቁጣጣሽና በመስቀል ችቦ ነበልባል እየተቀጣ ይመጣል፡፡
የመስከረም መስክ በውበት የሚወሰውሰው ተፈጥሮን ብቻ አይደለም፤ ለጥበብ የተቀቡ ከያንያን ብዕርም ቅኔ አምጦ ይወልዳል፡፡ ሣቅና ተስፋን በአየሩ ላይ ይረጫል! አዳዲስ መዝሙሮች በምድሩ ላይ ይናኛሉ፡፡
በሃገራችን ለዚህ ሞገሣዊ ጥበብ እማኝ የሚሆኑ ሕሩያን በርካታ ናቸው፡፡ በተለይ የቀደመው ዘመን አንጋፋ ከያንያን በርካታ አሻራዎቻቸውን አስቀምጠው በማለፋቸው፣ ሁሌም ትዝ ይሉናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ገጣሚና ሰዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን፣ ከበደ ሚካኤልና ሌሎችንም መጥቀስ እንችላለን፡፡
ስለ መስከረም ጥባት ስንኝ ከቋጠሩት ውስጥ አንዱ የሆኑት ከበደ ሚካኤል፤ “መስከረም ጠባ” በሚለው ግጥማቸው እንዲህ አሥፍረዋል፡-
ዐቧራው ተነሳ ነፋሱ ነፈሰ፤
ደመና እየሸሸ ሰማዩ ሲጣራ፣
ስንዴው ጨበጨበ እሸቱ ደረሰ፣
ዝናቡም ሲፈፀም ተከተለ ብራ፣
ደመናው ሲሸሽ ሰማዩ መጥራቱን፣ እርጥበቱ ሲሄድ አቧራና ንፋስ መተካቱን በዜማ ይነግሩናል፡፡… ስንዴውና እሸቱ ያበለፀገው ዝናም ሲሄድ፣ ብራው በእግሩ መተካቱን ሲያሳየን፣ በውስጣችን የሁለቱ ወቅቶች ፍርርቅ ድንበር ይታየናል፡፡
እኛ ደግሞ በዚህ መካከል የክረምቱን ማለፍ አማካሪ ችቦዎቻችንን ጨብጠን፣ በየደጃችን ብቻ ሣይሆን በልባችን ላይ እንሰበስባለን፡፡ ሴቶች አበባየሁ ወይ በሚል ዜማ በሚጥሙ ስንኞች ስሜታችንን ሲበረብሩት ውስጣችን ሀሴት ያደርጋል፡፡… ነፍሳችን ለአዲስ ጉዞ ክንፎችዋን ትዘረጋለች።
ከበደ ሚካኤል ደግሞ በግጥሞቻቸው ስንኞች የተፈጥሮን ምሥል እንዲህ ያሳየናል፡፡
ክፈፍ ላይ ሲያስተውሉት አገሩን በሰፊ
መሬት ትታያለች የክት ልብሷን ለብሳ
ለምለሙ ውበቷ አይመስልም አላፊ
ከአረንጓዴ ቀለም ማማር የተነሳ
ይህ ግጥም የመስከረሙን ዋዜማ፣ የምድር ገጽ ብሩህነትና ውበት ያሣየናል፡፡… አረንጓዴ ቀለም ተሸልማ ልብ የምትማልልበት ወር ወደ ልባችን ያቀርባል፡፡… ያም ውበት ቀኑ ደርሶ ማለፉ ባይቀርም ደግሞ የሚያልፍ  አይመስለንም ብለው አድናቆቱን ከፍ ያደርግልናል፡፡ ይህ የመስከረም ሠሞን ውበትና ዝማሬ በኢትዮጵያውያን ሕይወትና ዐለም፣ አሻራው ታላቅ መሆኑን የምናውቀው፣ የግጥም ቤት አመታታችን ሣይቀር ከዚህ የሆያሆዬ እታበባሽ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ የከበደ ሚካኤል ይህ ግጥም ቤት አመታቱ፣ ከቡሄ በሉና ከአበባየሁ ሆይ ጋር የተያያዘ መሆኑ ይደንቃል፡፡
አበባየሁ ወይ
ለምለም
አበባየሁ ወይ
ለምለም
ባልንጀሮቼ
ለምለም
ግቡ በተራ
እንጨት ሰብሬ
ለምለም
ቤት እስክሰራ
ለምለም
ሲል በአማርኛ የግጥም ቤት አመታት ስለት ውስጥ የተመረጠና የተወደደውን የሀለ ሀለ ቤት ያሣየናል፡፡ የእኛ ነገር ከአውዳመታችንና ከአሥራ ሦስት ወራት የፀሐይ ብርሃን ጋር መዛመዱ ልዩ ያደርገናል።
ለዐይን የሚታዩ ብቻ ሣይሆኑ መዐዛቸውን በአፍንጫ ቆንጥጦ የሚይዝና ነፍስን የሚማርክ ዕጽዋት አብረው ብቅ ማለታቸውም ሌላው የአዲስ ዘመን ዋዜማ ፀጋ ነው፡፡ የከበደ ሚካኤል ግጥም እንዲህ ይላል፡-
እንግጫ ሰንበሌጥ ሰርዶና ቄጠማ
አክርማና ጦስኝ ደግሞም እነ ሙጃ
አበቃቀላቸው ሕቡር የተስማማ
መስኩ ላይ ተቀምጧል ያበባ ስጋጃ
ይህ ማራኪ ውበትና ውብ መዐዛን በአንድ ያጣመሩ፣ የጥቢ የደስታ ስሜት ዝማሬዎችን፣ የአዲስ ዐመት ሥጦታዎችን የያዘ ነው፡፡ ያምራል፤ ይጣፍጣል፤ ወረድ ብሎ ያሉት ስንኞች ደግሞ ሌላ ውበት ፈጣሪ ፍጡር ይዘው ይመጣሉ፡-
ቀለሙ ወይን ጠጅ የስጋጃው መልኩ
ቁጭ ብድግ እያለች ስትጫመት ወፏ
ሕይወት አገኘና ደስ ደስ አለው መልኩ
እጅግ ያማረ ነው ጥቁር ቢጫ ክንፏ፡፡
ይህ አንጓ የመንግሥት ለማን
የመስቀል ወፍና የአደይን አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?
ማን ያውቃል?
የሚለውን አዝማች ያስታውሰናል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት ብዙዎች የሀገራችን ከያንያን የአዲስ ዐመትን ውበትና ተምሳሌት በአብዛኛው ዘምረውታል፡፡ ለምሳሌ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ የወቅቱን ለውጥ እንደ ንጋት ያየዋል፤ በችቦ ብርሃን ይመሥለዋል፡፡
ነጋ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ ፀደይ አረብቦ
በራ የመስቀል ደመራ

Read 588 times