Monday, 15 March 2021 08:06

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡- ሶስት ጓደኛሞች መንገድ ዳር ባለ ካፍቴሪያ በረንዳ ላይ ተቀምጠው ቡና እየጠጡ ይጨዋወታሉ። ሶስቱም ሃኪሞች ናቸው። በጨዋታቸው መሃል አንደኛው እግሮቹን ፈርከክ፣ ፈርከክ እያደረገ፣ በጎዳናው ላይ በጥንቃቄ ወደሚራመደው መንገደኛ እየጠቆመ፡-
“ያንን ሰው አያችሁ? የጉኖሪያ በሽታ ህመምተኛ መሆን አለበት” ሲል አስታወቃቸው። ሌላኛው ጓደኛቸው ደግሞ የሰውየውን አካሄድ ለጥቂት ደቂቃዎች ከተመለከተ በሁዋላ….
“ጎኖሪያ ሳይሆን ቂጢኝ ነው እንዲህ የሚያደርገው” አለ። በሁለቱ ጓደኛሞች “ግምት” ያልተስማማው ሶስተኛው ሃኪምም፤ የሰውየው ህመም ሌላ ዓይነት የአባላዘር በሽታ መሆኑን በመግለፅ ተከራከረ። ባለሙያዎቹ በየራሳቸው “የኔ ግምት ትክክል ነው” በሚል ስሜት ስለተዋጡ አልተግባቡም። ሶስቱም ግን የህመሙን ምንነት ለማወቅና ለመማር እንደሚፈልጉ ለመናገር አላቅማሙም። ወደ ሰውየው በመሄድም የከበረ ሰላምታ አቅርበው፣ ሃኪሞች እንደሆኑ በመግለፅ ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ፣ ሊረዱት እንደሚፈልጉና የሙያ ግዴታም እንዳለባቸው አስረድተው….
“ኧረ ማበድህን ዓይተን ህመምህ ምን እንደሆነ ለመገመት ሞከርን። ነገር ግን ሶስታችንም መግባባት አልቻንም” በማለት የእያንዳንዳቸውን ግምት በመናገር ማንኛቸው “ልክ” እንደሆኑ ሳይደብቅ እንዲያሳውቃቸው አግባቡት።… ሰውየው ሃኪሞቹ የነገሩትን እንደሰማ ሳቅ፣ ሳቅ አለው።
“ምነው?” ብለው ጠየቁት።
“የአራታችሁንም ግምት ተሳስቷል” አላቸው። … ያልጠበቁት መልስ ነበር።
“እንዴት?” ሲባል…. ዕውነቱን አልደበቃቸውም። ….. ሳቁ በነሱ ባሰ።…. ምን ይሆን ዕውነቱ?.... መጨረሻ ላይ እነግራችኋለሁ።
*   *   *
ወዳጄ፡-  ኑሯችን በግምት፣ በይመሰላልና በጥርጣሬ  የተሞላ ነው። በርግጥ ሳይንስና ጥበብ፣ እምነትና ፍልስፍና ውስጥ አያሌ የግምት ጥልፎች አሉ። አውሮፕላን፣ ስልክ፣ ሬዲዮና መሰል ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ሌሎች መገልገያዎቻችን አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት በግምት ቁጥሮችና የሂሳብ ስሌቶች ወጣ ገባ ቀመር ነው።
ወዳጄ፡- ግምት የሙከራ ሃሳብ ነው። አንዳንዴ ትክክል፣ አንዳንዴ ስህተት ሊሆን ይችላል። መገመት ባይችል ኖሮ የእነኤዲሰንና የእነማርኮኒ የቴክኖሎጂ ሙከራዎች እየታረሙ ወደ ትክክለኛው መስመር ሳይገቡ ይመክኑ ነበር። እውነተኛ መረጃን ያልተንተራሰና ቅንነት የጎደለው ግምት ግን ከልማቱ ጥፋቱ ሊያይል ይችላል።
ለምሳሌ  “የማያድግ ልጅ እንትን ይበዛበታል” ሲባል የሚታይን ነገር መሰረት ያደረገ ግምት ተብሎ ሊቆጠር ይችላል። ፍፁም ትክክል ነው ብሎ መደምደም ግን ስህተት ነው።  “እግረ ቀጭን እያለ እግረ ወፍራም…” እንደሚባለው።
ወዳጄ፡- አንድን ነገር ከሚገባው በላይ ከፍ ወይ ዝቅ አድርጎ መገመት (Under/ over estimate) ገማቹን እራሱን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊመራው ወይም ከአሰበው ዓላማ እንዳይደርስ ሊያደናቅፈው የሚችልበት ዕድል አለ።
እንደ አኪለስ እየፎከረ ሂዶ እንደወጣ የቀረ ወይም አስክሬኑ በለቅሶ የተመለሰ የብዙ ጀብደኛ ታሪክ ተፅፎ አንብበናል።
በዓድዋ ጦርነት ጣሊያን የተዋረደችው አገራችንንና ህዝባችንን በመናቋ ነበር። ንቀት አንድን ህዝብ፣ አንድን አገር፣ ግለሰብን፣ ተፎካካሪን ወይም ጉዳይን አሳንሶ መገመት ወይም በተቃራኒው ራስን ከተገቢው በላይ መቆለል እንደሚባለው ነው። ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ኖሮ  ወደ ፍርድ ቤት አይሄድም የሚባለውን ቁም ነገር ማሰብ አንዳንዴም ቢሆን ይጠቅማል።
ወዳጄ፡- “ትልቅ ጋን በትንሽ ጠጠር ይደገፋል” እንደሚባለው፤ ትንሽም ቢሆን እውነትና ቅንነት የደገፏቸው ግምቶች ከሞላ ጎደል ተሳክተው ገንቢ ውጤት ሲያመጡ ተመልክተና፣ የዕውነትና የቅንነት ትንሽ የለውም እንጂ። በነገራችን ላይ ከፍ ላለ አእምሮ ወይም ከተቆለፈ ሳጥን ውጭ ማሰብ ለሚችል ሰው ካልሆነ በቀር አብዛኛዎቻችን ስለተለያዩ ጉዳዮች የምንሰጣቸው ግምቶች ካለንበት ህብረተሰብ ባህል፣ ዕምነትና ስነ-ልቦና ወይ አጠቃላይ አኗኗርን መሰረት ያደረገ ወይም ከአካባቢያችን (Enviroment) ጋር የተዛመዱ ነፀብራቅ፤ ከሱም ውጭ ሊሆን እንደማይል ጥናቶች ያሳያሉ።….. እዚች ጋ አረፍ በሚያደርገን  ጨዋታ እንቆይ።
ሰውየው የከብት ስጋ ቁርጥ የሚሸጥበት ቤት በረንዳ ላይ እየተመገበ ሲዝናና፣ አንዲት ድመት ዓይን ዓይኑን እያየች “ ሚያው!” ማለት ስታበዛ ተናዶ ከማባረሩ አሮጌ ውሻ መጥቶ አጠገቡ ቁጢጥ አለና ዓይን ዓይኑን ይመለከት ጀመር። እሱንም አባሮ አንድ ሁለቴ እንደጎረሰ ደግሞ ቡቱቷም ለማኝ ከፊት ለፊቱ ተገተረበት። እየተነጫነጨ ሰሃን ይዞ ወደ ውስጥ ገባ። ከዓመታት በሁዋላ አጋጣሚ ሆኖ ሰውዬአችን ከመኖር ጋር ተኳረፈ። ክፉኛ  ደኸየ።… “አጣ ነጣ” እንደሚሉት ሆነ።
ከእለታት አንዱ ቀን ታዲያ በያኔው ስጋ ቤት ደጃፍ ቆሞ ሲለምን በረንዳው ላይ ተቀምጦ ሲበላ የነበረ ሽማግሌ የተረፈውን ምግብ ኮሮጆው ውስጥ እየጨመረለት፡-
“ረስተኸኛል መሰለኝ” አለው
“ማነህ?”
“ከሁለት ዓመት በፊት እዚህ ቦታ ሆነህ ስትመገብ አንዴ ድመት፣ አንዴ ቡቱቷም እየሆንኩ ብለምንህ አባረኸኝ ነበር። ስስታም ነህ እንዴ?” እያለ ሲስቅ … ሰውየው ነቃና…
“እግዜር እንዲያ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም ነበር” አለው።… እሱ የሚያውቀው እግዜር “ሰማይ ቤት” ነው።
ወዳጄ፡ አንዳንድ ፀሃፊዎች እንደሚሉት፤ ሰዎች እርስ በራሳቸውና ከሌሎች ፍጥረታት ጋር የሚቆራኙበትን መንፈሳዊ ፀጋ ወይም የጠፋቸውን የህይወት ሚስጢር ቁልፍ ሲያገኙ ብቻ ዕውነተኛ ደስታን ያገኛሉ። “THe missing link” የሚሉትን።
ወዳጄ፡- እኛ በዕለት ተዕለት ኑሯችን ስለ ሹሮና በርበሬ፣ ስለ ስኳር ዘይት በማሰብ ስራ ተጠምደን ስንንደፋደፍ አጠገባችን ውርውር ከሚሉት እንስሳት ጋር ያለንን ቁርኝት እንኳ ተገንዝበን ተፈጥሮን  ለማገዝ አቅም ባነሰን ቁጥር የሚስጢሩ ቁልፍ ይበልጥ እየራቀና እየደበዘዘ ይሄዳል። ታላቁ ሾፐን ሃወር፤ በኛና የአእምሮ ከፍታ ባላቸው ሰዎች መሃከል ያለውን ልዩነት…. “ genius is simply the completest objecetivity, the power of leaving  one’s own interest, thinking the fundamental, the universal, the eternal while others think the temporary, the specific, the immediate, his mind and cheins have no common ground and never meet” በማለት ፅፎልናል።
ወዳጄ፡- Where is the missing link?... ገምት!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሃኪሞቹ ለሰውየው ስለህመሙ ዓይነት ያላቸውን ግምት በመግለፅ ሊግባቡ እንዳልቻሉ ሲያስረዱት፤ አጅሬው የነሱም ሆነ የሱ ግምት ትክክል እንዳልሆነ እንደነገራቸው ተጨዋውተናል።
“እንዴት?” ብለው ሲጠይቁት
“እኔም ´ፈስ´ መስሎኝ ነበር” ያላቸው።
ሠላም!

Read 979 times