Saturday, 20 March 2021 11:25

ፓርቲዎች በምርጫው የፀጥታ ስጋት አለብን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከእጩ ምዝገባ ጋር በተያያዘ 149 ቅሬታዎች ቀርበዋል
                 
             ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከእጩዎች ምዝገባ ሂደት ጋር በተገናኘ 149 የቅሬታ አቤቱታዎችን ተቀብሎ እንደየመልካቸው መፍትሔ ማበጀቱን ያስታወቀ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ምርጫ ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት ተጋርጦብናል ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ከትናንት በስቲያ በእጩዎች ምዝገባ ሂደትና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ባደረገው ውይይት ላይ፤ በእጩ ምዝገባ ወቅት ከተለያዩ ፓርቲዎች 149 ቅሬታዎችን ተቀብሎ መፍትሔ ማበጀቱን ጠቁሟል፡፡
በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ከፓርቲዎች ከቀረቡ አቤቱታዎች መካከል፣ በየክልሉ የሚገኙ የምርጫ ቢሮዎች “እጩ አንመዝግብም አሉን”፣ “ቢሮ ዝግ ሆኖብናል”፣ “የገደቡ ጊዜ ሳያልቅ አልቋል ተብለን ተመለስን”፣ “ኔትወርክ የለም ተባልን”፣ “ሲስተም የለም ብለው መለሱን” የሚሉት በርከት ያለውን ድርሻ ሲይዙ፤ ቦርዱም ለቅሬታዎቹ በሙሉ ፈጣን መፍትሔ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ፓርቲዎቹ ስጋቶቻቸውን ያነሱ ሲሆን እጩ ከማስመዝገብ ጋር በተያያዘ ተፈናቃዮች ባሉባቸው ቦታዎች ምርጫ እንዴት ይሆናል? ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለበት መተከልና ቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባቢ እጩ ማስመዝገብ አልቻልንም፤ በምርጫው የፀጥታ ስጋት ተጋርጦብናል የሚሉ አቤቱታዎች ቀርበዋል።
በርካታ ፓርቲዎች በተለይ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉምዝ በምርጫው ሰላማዊነትና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ስጋት እንዳለባቸው  ያንፀባረቁ ሲሆን ቦርዱም “የፀጥታ ስጋትን በተመለከተ ከፀጥታ አካላት ጋር የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ሁኔታው በፀጥታ ሃይሎች መረጃ የሚወሰን ነው” ብሏል፡፡
ኢዜማ ብቻውን በ144 የምርጫ ወረዳዎች ላይ ከእጩ ምዝገባ ጋር በተያያዘ አቤቱታ ማቅረቡን ያመለከተው ቦርዱ፤ መፍትሔ ያላገኙ አቤቱታዎች አሁንም አሉ፤ መፍትሔ እንዲያገኙ እንደገና እናያቸዋለን” ብሏል- በተለያየ ሁኔታ ቅሬታዎችን አይቶ እጩዎች የሚመዘገቡበት ሁኔታ እንዳለ በመጠቆም፡፡

Read 1043 times