Saturday, 20 March 2021 12:05

“ለበጎ ነው፣”... ያድርግልና!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ... አሁን ያለንበትን አይነት ምኑን እንደምንጨብጥ፣ ምኑን እንደምንይዝ ግራ የተጋባንበት የቅርብ የሆነ ጊዜ ማሰቡ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉ ነገር እንዲህ መላ ቅጡን ያጣል እንዴ! እናላችሁ...“ለበጎ ነው፣” “ሊነጋ ሲል ይጨልማል...” ምናምን መባባሉ አሪፍ ነው፡፡ ለጊዜው ቢሆን ያረጋጋላ! አሁን እኮ “ቴሌቪዥንም አላይ፣ ሬድዮም አልሰማ፣ ማህበራዊ ሚዲያ የሚባለውንም አጠገቡ አልደርስ...” ምናምን ቢባል የፈራችሁት ነገር ድሆ ድሆ፣ እቤታችሁ ዘው! በር ይቆረቆራል፡፡
“ማነው?”
“እኔ ነኛ! ማን ሊሆንልሽ ነው!”  ጉድ እኮ ነው....የምንቆጣባቸው ነገሮች ሁሉ እኮ ግራ እያጋቡን ነው፡፡ ስንትና ስንት ሰው የሚቆረቁረውን በር ያንኳኩት እሳቸው መሆናቸውን የምትለየው ኮድ አለው እንዴ! እናላችሁ... ኑሮ ብግን ሲያደርገን እኛ ራሳችን ብግነ የምናደርገው ምስኪን የምንፈልግ ነው የምንመስለው!
“እርስዎ ነዎት እንዴ! እኔ እኮ ገና ሳይነጋ ማን መጣ ብዬ ነው፡፡”
“ዘይት ስንት እንደገባ ሰማሽ?” “እንደምን አደርሽ...” የለ! “በህልምሽ እየመጣ የሚያስቸግርሽ የድሮ ባልሽ አሁንም እንቅልፍ እየነሳሽ ነው ወይ?” ብሎ ነገር የለ... ቀጥታ ወደ ጉዳዩ፡፡
“በዛ ሰሞን እዛ ሸማቾች ሰዎች አምስት ሊትሩ ከአራት መቶ ብር አልፏል እያሉ ሲያወሩ ሰምቼ ነበር፡፡”
“አንቺ ምን አለብሽ...አምስት ሊትሩ አምስት መቶ ሀምሳና ስድስት መቶ ብር ደርሶልሻል!”
“ጉድ! ጉድ! ጉድ! አፈር በበላሁ!” (ለነገሩ የኑሮ መወደዱ አሁን ባለው በሁሴን ቦልት ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ...“አፈር በበላሁ!” የምትለዋ ነገር ቅርብ መሆኗ አይቀርም፡፡) እናላችሁ...“ጉድ! ጉድ! ጉድ!” ከሚለው ጋር እኩል ‘ዜማ ተከትሎ የሚሄድ፣ የአግራሞት ጭብጫቦ እንዳለ ልብ ይባልማ!
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እግረ መንገድ ምን በዛ አትሉኝም...ጭብጫቦ! ዘንድሮ እኮ የማይጨበጨብለት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው! እና ጭብጫቦ ብዙዎችን እያሳሳታቸው ነው፡፡ ልክ ነዋ... የዘመድ ጉባኤም፣ አብሮ አደጉም፣ የ‘ሲፕ’ አጋሩም ስላጨበጨበ፣ ዘጠነኛው ደመና ላይ ወጥቶ ጉብ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡
‘ቢት’ እየጠበቀ የሚደረገው ጭብጫቦማ ምን አለፋችሁ አሁን፣ አሁን የተሰብሳቢ ሁሉ ግዴታ የሆነ ነው የሚመስለው። በተለይ የቴሌቪዥን ካሜራ ምናምን ነገር ካለማ ጨዋታው ... አለ አይደል... “እስኪጣራ ማን ይጉላላል...” ነው የሚሆነው፡፡ ያው በየስብሰባው ‘ቺርሊደርስ’ አለን አይደል... ብቻ አንዱ ‘ጨብ’ ያድርግ...ድፍን አዳራሽ ተከትሎ...ከሰውየው ኮቴ እኩል በሚሄድ ‘ጨብ፣’ ‘ጨብ’ ከአዳራሹ ኋላ ተነስቶ መድረክ እስኪደርስ ይታጀባል። የጭብጫቦውን ውጤትም ወዲያውኑ ነው የምታዩት፡፡ “ሰው ቀና ብሎ አያይም፣” “ጮክ ብሎ አይናገርም፣” የተባለው ሰውዬ፣ ደረቱን ‘አገር’ ያሳክልባችኋል! (እድሜ ‘ቢት’ ላለው ጭብጫቦ!) እኔ የምለው ግን... የሰው ልጅ ሳምባ በአንድ ጊዜ ይህን ያህል አየር ማጠራቀም ይችላል እንዴ! የተጨራመተ ኳስ የምትመስል ደረት የያዝነው ሁሉ እኮ ‘ቢት’ ባለው ጭብጫቦ ከታጀብን፣ የራሳችንን ብቻ ሳይሆን የሌላ ሰዉንም የኦክሲጅን ድርሻ ነው የምንወስደው፡፡   
እናላችሁ... “ለበጎ ነው፣” “ሊነጋ ሲል ይጨልማል...” የምንለው ነገር እንደ ጊዜያዊ ‘አኔሽቴዚያ’ ነገር ቢያገለግልም ነገሩ ምን መሰላችሁ... እኛ ነገሮች ‘ለበጎ እንዲሆኑ’ የእውነት እየሞከርን ነው ወይ? ጨለማው በእርግጠኝነት እንዲነጋ የበኩላችንን እያደረግን ነው ወይ...ነው፡፡
 ስሙኛማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... የኑሮውም ክብደትም ይሁን፣ ሳናውቀው የተረጨብን ዱቄት ነገርም ኖሮም ይሁን ብቻ በሚጢጢዋ ነገር ሆድ ይብሰናል፣ እንቆጣለን፡፡ ደግሞላችሁ ምንም ነገርን በጥሬ ትርጉሙ ከመውሰድ ይልቅ ብቻ ፈልፍለንም፣ ጠምዝዘንም የሆነ የተደበቀ ስውር ነገር እንፈልጋለን። 
ሰላምታ እንኳን ነገር ሊያመጣ ይችላል።  ልክ ነዋ... ለምሳሌ ሰላምታ ይሁን፣ የቃለ መጠይቅ የመጀመሪያው ጥያቄ ይሁን የማይለየው “ምን አዲስ ነገር አለ?” የሚለው አባባል፣ ‘ነገር፣ ነገር’ ለሚለን ሰዎች...ምቹ ነው፡፡ አሀ ልክ ነዋ...ዘንድሮ አንድን ነገር እንደ ብዙ ሰው ባህሪይ ወዲያውኑ መጠምዘዝን የመሰለ ቀላል ነገር የለም፡፡ ችግሩ እዛው ቦታ አጉረምርሞ ቢበቃ መልካም፤፡ “ይሄ ሰውዬ ምን አዲስ ነገር አለ ነው የሚለኝ፣ አሁን እኔ የምጎርሳት እንጀራ፣ እንጀራ ሆነችና ሰላይ ይላክብኛል! የእነሱን ጥሬ ሥጋ በቆጭቆጫ አልተሸማኋቸው!” ምናምን አስብሎ ቢበቃ ጥሩ! ዘንድሮ ምን የማይጎተት ነገር አለና!  እና በንጹህ ልብ ሰላም የሚለውን ሰው፣ እንደ አዶልፍ ሂትለር ገንዘብ ቤት ማስመሰል ጊዜ ያመጣብን ነገር ይመስላል፡፡ (አሁን ካልጠፋ ምሳሌ ‘ገንዘብ’ ላይ ምን አንጠለጠለኝ፡፡)
ስሙኝማ...መቼ እንደ ዘንድሮዋ አዲስ አበባ በአንድ ጊዜ በስልጣኔ ተስፈንጥረው ጫፍ ላይ ጉብ የሚሉ ስንት ቦታዎች ይኖሩ ይሆን! ግራ ገባና... ይህ ድሮ የሀገር ምስጢር ይመስል የምንሾካሾክበት የ‘ሹገር ምናምኖች’ ነገር አደባባይ ወጣና አረፈው! በየቀኑ የምንሰማቸው ነገሮች እኮ...አለ አይደል የምር ሳናውቀው የሆነ ነገር በትነውብን ይሆናል እንጂ ድፍን ሀገር፣ ሰፈር እንዳስቸገረ ‘ቲንኤጀር’ ይሆናል እንዴ! ስንት ሪቮልዩሽን እያለ የእሱ ነገርዬ ‘ሪቮሊዩሽን’ ብዙ ተከታይ ያለው ነው የሚመስለው! ቂ...ቂ...ቂ...
በአንድ ጊዜ ብረት የሚያነሳና ከዱባይም ከምንም የሚመጣ  ጡንቻ ማፈርጠሚያ ኪኒን የሚውጠው ሰው መብዛቱ እንቆቅልሽ ከሆነባችሁ ማንን ጠይቁ መሰላችሁ...ሹገር ማሚዎችን! (ቂ...ቂ...ቂ...) በአንድ ጊዜ ‘ናይን ታውዘንዷን’ ቁጭ እያደረጉ የሥራ አጥነት መከራ የሆነበት ወጣት አይደለም በቀን ሁለትና ሶስት ሰዐት ሀያ አራት ሰዓት ብረት ቢያነሳ ምን ይገርማል! ያውም እኮ ‘ናይን ታውዘንዷ መደበኛ ነገር መሰለችኝ፡፡ ‘ለእያንዳንዱዋ እንደ ፍላጎቷ፣ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው’ አይነት ነዋ! (እነ እንትና ሄይሩ ምናምኑን፣ እድሜ ለቀለም፣ በእሱ ይስተካከላል፡፡ ግን እነዚህ ስቲኪኒ የሚያካክሉ ክንድና እግርን ምን እናድርጋቸው? አሀ...ግራ ይገባላ! የፈለገውን ያህል በልብስ ቢሸፋፈኑ፣ ‘ግጥሚያው የሚካሄድበት ስታዲየም’ ሲደርሱ መጋለጣቸው ይቀራል! ቂ...ቂ...ቂ... (እነ እንትና... ቸኩላችሁ እንትና ጋራዥ ጥግ የተወሸቁትን ሚሊቼንቶዎች መስላችሁ፣ አሁን ያመለጣችሁ ነገር ገባችሁ!)
ለነገሩማ...አለ አይደል፣ የሹገር ምናምኖች አይነት ነገር አዲስ አይደለም፡፡ ግን አንደኛ ነገር እንዲህ መስፋፋቱ፣ ሌላ ደግሞ በአደባባይና በግላጭ ሲሆን...ከማስፈገግ አልፎ ብዙ ነገሮች ላይ እንደምንለው፣ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡ (እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል... ቀደም ሲል ባለፉት ዓመታት እኮ “ወዴት እየሄድን ነው?” ስንልባቸው የነበሩ ነገሮች ሄደን፣ ሄደን የምንደርስበት ደረስንና አሁን እንደውም እንኳን ሊያስገርሙ ‘ኖርማል’ እየሆኑ ነው መሰለኝ!) 
እናላችሁ፣ ‘ሴንሲቲቭ’ ከመሆናችን የተነሳና፣ አብዛኞቻችን በምናያቸውና በምንሰማቸው በርካታ ነገሮች ሆድ እየባሰን በመሆኑ ትንሽ ነገር ሊበቃን ይችላል፡፡
በተለይ ‘ኦልዲሶች’... እንደው “ኖስታሊጂያ...” “ትዝ አለኝ የጥንቱ...” ቅብጥርስዮ እያላችሁ፣ ‘አውት ኦፍ ሰርቪስ’ የሆኑ ልማዶችን እቤት እየቆለፋችሁባቸው ውጡማ! አሀ... በእናንተ ጦስ የምን ሁሉንም በአንድ ሙቀጫ ማስወቀጥ ነው፡፡ አሁን በዚህ ዘመን በዚች ግራ በምታጋባ ከተማ “ለመሆኑ ለጤናሽ እንደምን ከረምሽ...” ብሎ ሰላምታ ምንድነው! አሀ... የነገሮች ቅደም ተከተል ይጠበቃ! “እንደዛ አይነት ሰላምታ ለመስጠት ያስቻለህ ‘ሶርሱ’ ምንድነው የሚል ሙግት ቢመጣብንስ! በቃ...የመጠምዘዝና መጠመዛዝ ዘመን ነው!
እናማ የ‘ኦልዲስ’ ነገሮች አልለቅ ያሉት እሱዬ፣ እሷን መንገድ ላይ አገኛት፡፡
“አንቺ አለሽ እንዴ! ለመሆኑ ለጤናሽ እንደምን ነሽ?”
ደንገጥ ልትል ትችላለች...ለጤናሽ! ለጤናሽ! ብሎ አማርኛ ምንድነው?
“ለጤናሽ እንደምን ነሽ የምትለኝ እኔ...ቆረጥኝ አላልኩ፣ ፈለጠኝ አላልኩ፣ ቡአ ወረደኝ አላልኩ!” ምናምን  ብትል ምን ተብሎ መልስ ሊሰጥ ነው!...እንደዛ ሽንቅጥ ብላ “ምድረ ምናምን ‘ሂፕ’ ምናምን ለማየት ራስሽን አስሬ ስታዞሪ አንገትሽ እንዳይቀጭ!” እያለች መንገዱ ላይ ‘እየተነሰነሰችበት’... ለጤናሽ!
“አንቺ ፊትሽን አጨማደሽ እንዴት እንደምታስጠይ ባየሽ!”
“በቃ... እዚህ ሀገር መኖር አንችልም ማለት ነው!”
“ደግሞ ምን ሆንሽ? ፖለቲከኛ ሆንሽ እንዴ!”
“ማነው የሚሉት ደባሪ፣ ሀርድ አይለቅብኝ መሰለሽ!”
“ማን?”
“ያ ሲራመድ እንኳን ተሳቢ የሚጎትት የሚመስለው...”
“ምን ቢል ነው? ልጎትትሽ አለሽ እንዴ!”
“የሚጎትት ይጎትትሽ! ለጤናሽ እንደምን ከረምሽ...አይለኝ መሰለሽ!”
“ምን! ምን ሆንሽና ነው ደግሞ ለጤናሽ እንዴት ነሽ የሚልሽ!”
“እኔ ምን አውቄለት! እንዴት ሙዴን እንዳበላሸው አልነግርሽም!”
“ኸረ የራሱን ጤና ያሳጣው!”
ለክፉም፣ ለደጉም... ቢሆንም፣ ባይሆንም ... ለደቂቃዎችም ቢሆን ህመሙን እስካስታገሰ ድረስ “ለበጎ ነው!” ማለቱ አይከፋም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!



Read 1511 times