Tuesday, 23 March 2021 00:00

ገራሚ ወሬዎች - “ግራሚ” እና “ኦስካር”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   አቫታር ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዟል

            የዘንድሮው ታላቁ የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት ባለፈው እሁድ በተለያዩ አስገራሚ ክስተቶች ታጅቦ የተከናወነ ሲሆን፣ በነጋታው ደግሞ የታላቁ ኦስካር ሽልማት የዘንድሮ ዕጩዎች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል፡፡
በአለማችን ታላቁ የሙዚቃ ሽልማት እንደሆነ የሚነገርለትና ባለፈው እሁድ ለ63ኛ ጊዜ በሎሳንጀለስ በተከናወነው የግራሚ ሽልማት ስነስርዓት፣ አሜሪካዊቷ ተወዳጅ ድምጻዊት ቢዮንሴ ኖውልስ፣ ለ28ኛ ጊዜ ግራሚን የተሸለመች የመጀመሪያዋ ሴት ሙዚቀኛ በመሆን ታሪክ የሰራች ሲሆን፣ 79 ጊዜ ለግራሚ የታጨች ቀዳሚዋ ሴት ሆናም በግራሚ ታሪክ ተመዝግባለች፡፡
በዘመነ ኮሮና የቤት ውስጥ እገታዋ በሰራችው “ፎክሎር” የተሰኘ አልበም የተሸለመችው ሌላኛዋ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት በበኩሏ፤ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት የአመቱ ምርጥ አልበም ሽልማትን የወሰደች ሴት በመሆን ሌላ ታሪክ ሰርታለች።
ሰኞ ዕለት ይፋ ወደተደረገው የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ስንዞር ደግሞ፣ በ10 ዘርፎች ለሽልማት የታጨው “ማንክ” የተሰኘው የዴቪድ ፊንቸር ፊልም፣ በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዞ እናገኘዋለን፡፡
በ83 ዘርፎች የሽልማት ዕጩዎች ይፋ በተደረጉበት የ2021 ኦስካር ሽልማት፣ ጁዳስ ኤንድ ዘ ብላክ ሚሳህ፣ ሚናሪ፣ ዘ ፋዘር፣ ኖማድላንድ፣ ትሪያል ኦፍ ዘ ቺካጎ 7 እና ሳውንድ ኦፍ ሜታል በተመሳሳይ በ6 ዘርፎች በመታጨት ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል። በኦስካር ታሪክ 70 የፊልሙ ኢንዱስትሪ ሴቶች 76 ጊዜ በመታጨት ታሪክ የሰሩበት የዘንድሮው ኦስካር አሸናፊዎች፣ በመጪው ሚያዝያ ወር መጨረሻ ሎሳንጀለስ በሚገኘው ዶልቢ ቲያትር በሚካሄደው ደማቅ ስነስርዓት ይፋ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
በሌላ የመዝናኛው መስክ ዜና ደግሞ፣ በታዋቂው ዳይሬክተር ጄምስ ካሜሩን የተሰራውና እ.ኤ.አ በ2009 ለመጀመሪያ ጊዜ ለእይታ የበቃው “አቫታር” ፊልም ባለፈው ሳምንት በቻይና በድጋሚ ለእይታ በቅቶ በአለማቀፍ ደረጃ ያገኘውን ገቢ ወደ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማሳደጉን ተከትሎ፣ በአለማችን ታሪክ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘ ቁጥር አንድ ፊልም ለመሆን መብቃቱ ተነግሯል፡፡ ለእይታ ከበቃበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2019 በነበሩት 10 ተከታታይ አመታት በገቢ ቀዳሚው የአለማችን ፊልም ሆኖ የቆየው “አቫታር”፤ በዚያው አመት በአቬንጀርስ ኢንድጌም ክብሩን ተነጥቆ እንደነበርም ያሁ ኒውስ አስታውሷል፡፡

Read 2914 times